ወዳጄ ሆይ !
አባቶችህ የሠሩትን ጨምርበት ፣ መጨመር ካቃተህ ያለውን ጠብቅ ። መጠየቅን ከፈራህ እውቀትህ ትንሽ ፣ እርግጠኛነትህም ጎዶሎ ይሆናል ። የነፍስህ መዝገብ ሙሉ የሚሆነው የእግዚአብሔርን ቃል ስትፈጽም ነው ። በእግዚአብሔር ፊት መቆም ከቻልህ በንጉሥ ፊት መቆም አያስፈራህም ። መሠረቱን አልመሠረትኩትም ብለህ የበጎ ነገር ሕንፃን ለመገንባት ዳተኛ አትሁን ። ንጉሥን ስትነቅፍ ልማቱን ከጥፋቱ ለይተህ ይሁን ። ስብከቱ የጣፈጠ ሰባኪን ስታደንቅ መልእክቱን የላከልህን እግዚአብሔር አመስግን ።
ወዳጄ ሆይ !
ከአንጀታቸው አምጣ በሚሉህ ምጽዋተኞችህ ደስ እንደሚልህ እግዚአብሔርም በቁርጥ ልመና በሚቀርቡት ልጆቹ ደስ ይለዋል ። ሙሉ ጌትነት ሲያምርህ ሙሉ ታዛዥ መሆንን አትርሳ ። መሄድ አለመቻል ማሰብ አለመቻል ፣ ማድረግ አለመቻል ማቀድ አለመቻል ፣ መስጠት አለመቻል መጸለይ አለመቻል አይደለም ። ጥርስ እንጎቻው እንዳይሉህ ከጥሩ ፈገግታና ቃል ጋር ቸርነትን ጨምርበት ። አእምሮህ እንዳይጎዳብህ ከዓለም ብዙ አትጠብቅ ፣ የሚመለከትህን መስማትና መኖርን አትርሳ ። ከባለቤቱ በላይ አልቃሽ ፣ ከጳጳሱ በላይ ኦርቶዶክስ አትሁን ።
ወዳጄ ሆይ !
ጥረትህ እብቅ ገለባ ካወጣ በጥረትህ አትዘን ። ዓለምን በታገሠው እግዚአብሔር ፣ ስንዴ ዘርቶ እንክርዳድ ስንሆንበት ባላጠፋን ጌታ ተጽናና ። በየትም ዓለም ብቻውን የሚለማመድ ሯጭ ይኖራል ፣ ብቻውን የሚወዳደር ግን የለም ። አንተ ግን ልምምድህም ሩጫህም ብቸኛ መስሎ ሲሰማህ ዳኛህ እግዚአብሔር ፣ ደጋፊዎችህ ቅዱሳን እንደሆኑ አስብ ። ሕዝብ ከቦህ ኖረህ አንድ ሰው አጠገብህ የምታጣበት ዘመን አለ ። እንዲደረግልህ ቀርቶ ያደረከው መልካም ላይመሰገን ይችላል ። እምነት ማለት የሰውን ምላሽ ሳይሆን የእግዚአብሔርን ዋጋ እያሰቡ መሮጥ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
በጥር ለመዝራት ፣ በሰኔ ለማጨድ አትውጣ ። እውነትህ ሰዎችን ከሚሰብር ዝምታህ ቢያድን ይሻላል ። ፍቅር የሌለው ደረቅ እውነት ከእግዚአብሔር አይደለም ። እውነት የሌለው ዝልፍልፍ ፍቅር የአጋፔ ፍቅር አይደለም ። ቤትህ የጦር ሜዳ ሲሆን ደጁ ዕረፍትህ ይሆናል ፣ ደጁ ሰልፍ ሲሆን ቤትህ መጽናኛ ይሆናል ። ሁሉ አይከፋምና በርታ ። ሁሉ የሚከፋበት ፣ ደጁም ቤቱም የሚያሳድድህ ዘመን አለ ፤ ያ ዘመን እግዚአብሔርን ብቻ የምታይበት ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
የተከታተልከው ልጅህ የልብ ኀዘን ፣ የለፋህለት አገር ወቃሽ ከሳሽ ፣ የጣርህለት ትዳር አፍራሽ ፣ ገመድ ያስጣልከው ትኩዝ መቃብርህን ቆፋሪ ቢሆኑ ጌታ በጴጥሮስ እንደ ተከዳ ፣ በይሁዳ እንደ ተሸጠ አስብ ። ነገር ሁሉ አዲስ የመሰለህ እውቀትህ ትንሽ ስለሆነ ነው ። ባለፍህበት መንገድ ክርስቶስ ቀድሞ በማለፉ ፣ በዓለም ላይ የሚደገም እንጂ የሚጀመር ነገር ባለመኖሩ በእነዚህ ሁለት ነገሮች ተጽናና ። ምንም ብትታክት በሰዓቱ መሆኑ አይቀርም ፣ ምንም ብትቸኩል ያለ ሰዓቱ አይሆንም ።
ወዳጄ ሆይ !
በመስኩ ስትደሰት የተሻገርህበትን ድልድይ አትርሳ ። ሰውነትህ መቅደሱ ፣ ልብህ ዙፋኑ ነውና ለእግዚአብሔር ተቀደስ ። የተቋረጠው ሲቀጠል ፣ የተቀጠለው ይቋረጣል ። ጠላትህ ይቅርታ ሲጠይቅህ ፣ ወዳጅህ እስከ ጊዜው ጠላት ይሆናል ። ቋሚ ነገር በዓለም ላይ የለምና በአንድ ዓይንህ ስትተኛ ፣ በአንድ ዓይንህ ንቃ ። ቋሚ ያልሆነ ሕይወት ይዘህ ቋሚ ሥራ አትፈልግ ። በዕድሜ ውስጥ የተገነዘብኩት እግዚአብሔር ብርቱ ፣ ዓለም ከንቱ መሆኑን ነው ።