የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/25

ወዳጄ ሆይ !

ሥር የሰደዱ ዛፎች ነፋስን ይቋቋማሉ ፣ ወደ ታች የጠለቁ መሠረቶች ብዙ ፎቅ ይሸከማሉ ። ሰውም በሳል ሲሆን በፈተና ይጸናል ፣ ፈተናና ነፋስ ያልፋሉና ። ነፋሱ ዘንበል ቢያደርግህም እንዲሰብርህ መፍቀድ የለብህም ። ብዙ ጫናዎችን ለመሸከም እውቀትና ማስተዋልን ገንዘብ አድርግ ። ከአገሬ በቀር አገር የለም ፣ ከእናቴ በቀር እናት የለም ፣ ከእኔ በቀር ሰው የለም ፣ ከእገሌ በቀር አገልጋይ የለም አትበል ። ጨርሶ መናገር ለዚህ ዓለም ነዋሪ ትዝብት ያተርፍለታል ። በክረምት ለመዝራት ዝናቡን የተሰቀቁ የአጨዳ ዘመን የላቸውም ። ሌላው ሲያለቅስ የሳቁ በኀዘናቸው አጋር አያገኙም ። ካልገዛ በቀር ስጦታውን የሚያቃልል የእግዚአብሔርና የሰው ወዳጅ መሆን አይችልም ። ፍላጎት መልካም ነው ፣ ከልክ ያለፈ መሻት ግን በቀን ሰላም ፣ በሌሊት እንቅልፍ የሚነሣ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሲሰበክ እየተኛህ ፣ ሲወራ የምትነቃ ከሆነ አእምሮህን ጠላት እያደባበት ነውና በስመ እግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ ተዋጋ ። የዛፍ የመጀመሪያ አካሉ ለስላሳ ነው ። የመጀመሪያ ግንኙነትህም ዕድገት እንዲኖረው በመልካም ፍቅርና ትሕትና ወጥነው ። ሀብታቸውን ሊያሳዩህ ለሚሹ እዘንላቸው ። ከእነርሱ ይልቅ የሠሩት ቤት ዕድሜ አለውና ። አንተም ተመክተህ ያለህን ለማሳየት በተነሣህ ቀን መጀመሪያ መቃብርህን ቆፍረህ ሂድ ።

ወዳጄ ሆይ !

የታረሰ መሬት የዘር ሞትና ትንሣኤ ነው ። የተከፈቱ ልቦችም የቃሉን ዘር ሲያገኙ እኔነትን ቀብረው ፣ አዲስ ሕይወትን ያወጣሉ ። የግል ንግግርን አደባባይ ላይ አታውለው ። ስሜትህን ለማያውቁህ አታስነብበው ። ጥረትህ ኪሣራ ቢያመጣም በዚህ ዓለም እስካለህ ጣር ። የጉባዔ ታላቅነት የሚለካው በሰው ብዛት ሳይሆን በእግዚአብሔር መገኘት ፣ በታላላቆች መታደም ሳይሆን በእውነተኛ አምልኮ ነው ። የሚወጥኑ ፣ የሚገነቡ ብቻ ሳይሆን የሚተቹም ያስፈልጉሃል ። ተቺዎች በነጻ የሚያገለግሉህ የጥራትና ደረጃ ባለሙያዎች ናቸው ። ችላ ተብለህ አድገህ ከሆነ ችላ የተባሉትን አስባቸው ። የእምነት ሰዎች ሲወድቁ ብታይ በጣም አትፍረድ ፣ የመነሻውን ምሥጢርም ያውቁታልና ። ያሉ የመሰሉ ነገር ግን የሌሉ ፣ የሌሉ የመሰሉ ነገር ግን ያሉ ብዙ ሰዎች ናቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሙሴን ሰው እንዳልቀበረው አስታውሰህ ፣ ጌታችንን ዮሴፍና ኒቆዲሞስ እንደገነዙት አስበህ ሞትህ ሰርግ እንዲመስል አትጓጓ ። ክፉ ሰዎችን እየተመለከትህ ታዝናለህና ለሚመለከቱህ ኀዘን ላለመሆን ፈሪሀ እግዚአብሔር ይኑርህ ። እግዚአብሔር ለሁሉም ጾታና ወገን ክብር እንዳለው አስብ ። በወንዱም በሴቱም ላይ ይሠራልና ምሉዕ እግዚአብሔርን አታጥብበው ። ሕይወቴ እግዚአብሔር ነው ማለት ቀርቶ ሕይወቴ ሌላ ነው የሚል ሰው ፣ ለመግደል የማይመለስ ጨካኝ ነው ። አንተ የምታስፈልገው ለጠወለጉ ሰዎች ፣ ለተጎሳቆሉ ነፍሶች ነው ። ቃላትህ የድምፅህ አቅም ከሞት የሚመልስ እንጂ ወደ ሞት የሚሰድድ አይሁን ።

ወዳጄ ሆይ !

የጠነከሩ ልቦችን እንደ ወርቅ የሚያቀልጥ የፍቅር እሳት ነው ። ልትደርስበት ያቃተህን ነገር ባዶ ነው ብለህ አትናቀው ። ሲኖርህ ድሀን ካላሰብህ ሳይኖርህ ልታስብ አትችልም ። ስለማንም ሰው ክፉም ደግም በእርግጠኝነት መናገር አትችልም ። የመናገር ብቻ ሳይሆን የመኖር ድፍረትህ እግዚአብሔር ነው ። አንድ የካደ ሰውን ስታሳምን የክርስቶስን መስቀል አገዝከው ማለት ነው ። ንግግር ማብዛት በራስ ላይ ወጥመድ መታታት ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ