የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /29

ወዳጄ ሆይ !

ሰዎችን የምታሸንፋቸው በፍቅር ፣ የሚያሸንፉህ በክብር ነው ። እውነተኛ ፍቅር መስጠት ካልቻልህ በሽንገላ ራስህን ማድከም ፣ ትዝብት ላይ መውደቅ አያስፈልግህም ፤ ፍቅር የሆነውን እግዚአብሔር “ሰውን በመውደድ ባርከኝ” ብለህ ለምነው ። የጎላ ታይታ መውደድ ወደ ብዙ መሰወር ይለወጣል ። “እዩኝ ፣ እዩኝ ያለ ገላ ፣ ደብቁኝ ደብቁኝ ይላል” እንዲሉ ። አማኝነት ላመኑበት ነገር መገዛት ነው ። ምሳሌ የሚያደርጉህ ታናናሾች አሉና ለሕይወትህ ጠንቃቃ ሁን ። ያገለገሉህን ወላጆች ፣ መምህራንና ወዳጆች የምታገለግልበት ዘመን እንዲሰጥህ በብርቱ ጸልይ ። በቁም አበባ መስጠት ፣ በቁም ፍቅርን መግለጥ ቀኑ ዛሬ ሳለ ሬሳው ላይ አበባ ለማስቀመጥ ፣ ፍቅርን ለመግለጥ መሞከር ከጊዜ ጋር መተላለፍ ነው ። የረፈደ ፍቅር ከጥላቻ በላይ ይጎዳል ።

ወዳጄ ሆይ !

የክርስቲያን ሰንደቅ ዓላማው ፍቅር መሆኑን አትርሳ ። የተዋቀረና በትእዛዝ ዕዝ ሥር ያለ አካል ይዘህ ያልተዋቀረ ውሎ አትዋል ። በሁሉም ስፍራ ለመገኘት እግዚብሔርነት ያሻሃል ። ብዙ ነገሮችን በአንድ ጊዜ አደርጋለሁ ብለህ ስትነሣ ለጭንቀት ትዳረጋለህ ።

ወዳጄ ሆይ !

ሥርዓት ኑሮን ውብ ፣ አምልኮትን ተወዳጅ ያደርገዋል ። ለቤታቸው ሥርዓት ያላቸው የቤተ ክርስቲያንን ሥርዓት ከተቃወሙ የአምልኮ መንፈስ ስለሌላቸው ነው ። የቡድንተኝነት ስሜት አንድ ቀን በመጠፋፋት ያበቃል ። ቆየት ያሉ ሰዎችን ፣ ቆየት ያሉ ቦታዎችን ፣ ቆየት ያሉ ዕቃዎችን ለማየት ሞክር ። አሁን ባለው ነገር የማይደሰት ሰው ወደፊት በሚኖረው አይደሰትም ። ሰዎች ገለልተኛ ሲያደርጉህ “የእኛ ስብስብ ላንተ አይመጥንህም” ማለታቸው ነው ። የታመመ ሰው “እግዚአብሔር ይማርህ” ብቻ ሳይሆን “እግዚአብሔር ይግደልህ” የሚለውንም ይናፍቃልና ሕመምተኛን ጠይቅ ።

ወዳጄ ሆይ !

የተለወጡ ሰዎች ያልበደሉ ያህል ናቸው ። “ሰው ለምን በደልህ ?” ሳይሆን “ለምን አልተመለስክም?” የሚባል ፍጡር ነው ። አዳዲስ ነገሮች እስኪታወቁ ጊዜ ይበላሉ ። ከአዲስ ወዳጅህ የቆየ ጠላትህ ስላንተ ደግነት መናገር ይችላል ። የእውነት መልእክተኛ መሆን ትልቅ ዕድለኛነት ነው ። ወታደር ራሱን ሳይገዛ አገር አያስከብርም ። አዛዡን የማያከብር ወታደር ቀጥሎ ሟች ነው ። መቆየት ጥላቻን እየሸረሸረ ይመጣል ። መተማመንህ በእግዚአብሔር ላይ ብቻ ይሁን ። ያመለከው ሰውና ነገር ሳያጠፋህ አይቀርም ።

ወዳጄ ሆይ !

ሕይወት በእንግዳ ክስተት የተሞላች ናት ። በብዙ ጠብቀህ ጉዳቱ ትንሽ ከሆነ ልብህ አይሰበርም ። የታወከ ሌሊት ሲገጥምህ በሰላም ስላደርክባቸው ሌሊቶች አለማመስገንህን አስብ ። ወዳጅና ወዳጅን አቆላልፎ አንዱን የአንዱ ጠባቂ ማድረግ የሴራ እንጂ የፍቅር መንገድ አይደለም ። ዛሬ በእጅህ ላይ የምታየው ነገ የሌላው ንብረት ነውና አትመካ ። ጉድጓድ መጀመሪያ የሚቀብረው ቆፋሪውን ነውና ክፋትን አታስብ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ