የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /28

ወዳጄ ሆይ !

ቤትህ መሰወሪያህ ፣ ቤትህ ከድካም ማረፊያህ ፣ ቤትህ እንግዳ መቀበያህ ፣ ቤትህ ገመና ሸፋኝህ ናት ።

“ቤቴ ፣ ቤቴ ገመና ከታቼ ፣
የቤት ገመና መክተት ምንድነው ምሥጢሩ ?
ወደ ጓዳ ገብተው ዱቄትስ ቢቅሙ”

እንዲሉ ቤትህን ጽዱ ፣ ሰላማዊና ተናፋቂ አድርጋት ። ከሰዎች ትልቅ ቤት ያንተ ትንሽ ቤት ያንተ ናት ። ቤትህ እውነተኛ ማረፊያህና መደበቂያህ የምትሆነው ከሥራህ ስፍራ የራቀች ስትሆን ነው ። ሰው ቤቱ ሲታወክ ወደ ሥራ በመሄድ አየር ይቀይራል ። የሥራው ስፍራ ሲከፋ ወደ ቤቱ ሂዶ ያርፋል ። እንደ ገና ዳቦ ከላይና ከታች እሳት እንዳይነድብህ ቤትህን ልዩ ግዛትህ አድርጋት ።

ወዳጄ ሆይ !

ሰውን ልብስ ፣ ቤት ፣ ትዳር ፣ የንስሐ አባት ፣ ልጅ ፣ ወገኑ ይሸፍነዋል ። ዘመን ሲከፋ ልብስ ይቀደዳል ፣ ክብርም ይገፈፋል ። የተራቆቱለት ትዳርም በአደባባይ ያዋርዳል ። ንስሐ አባትም ምሥጢርን ያወጣል ። ልጅም ጠቋሚ ይሆናል ። ወገንም አሳልፎ ይሰጣል ። ሰባራ ዘመን በጸሎትና በእንባ ይታለፋልና ተግተህ ጸልይ ።

ወዳጄ ሆይ !

እግዚአብሔር ብዙ የማዳኛ መንገዶች አሉት ። በማጣትም ከመጥፋት ፣ በሕመምም ከሞት ፣ በእስራትም ከርኵሰት ይጠብቃል ። ለአንዳንዱ ማጣቱ ነፍሱን ማትረፊያ ፣ ለሌላው ሕመሙ ከሞት መዳኛ ፣ ለቀረው እስር ቤቱ ገዳም ይሆንለታል ። ሞት ወዳጆችህን ሲወስድብህ አንተንም እየታከከህ ነውና ኑሮህን በጥንቃቄ አድርግ ። ሞትህ ሞት እንዳይሆን የበደለህን ክሰህ ፣ የቀማኸውን መልሰህ በሰላም ዕረፍ ። በሰላም ማረፍ በምርቃት ሳይሆን በተግባር የሚገኝ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የሁሉም ሰው ኑሮ ቢለያይም የነፍስ ዋጋ ግን እኩል ነው ። የነፍሳቸውን ሀብት እውቀትን ለሰጡህ መምህራን ፣ ነፍሳቸውን ለመሥዋዕትነት ለሚሰጡ የአገር ጠባቂዎች ክብር ይኑርህ ። ነጻ አእምሮ የንጹሕ ኑሮ ውጤት ነው ። መልእክትህን መስማት ከቻልህ እግዚአብሔር ዛሬም ይናገራል ። የተቀደሰ ኑሮ ዓለምን ያስንቃል ። ባሕርይህን ሳይሆን ጠባይህን ለውጥ ። ጾታህን መለወጥ አትችልም ፣ መጥፎ ጠባይህን ግን መለወጥ ትችላለህ ። የሥጋት ዘመን ሲመጣ እንቅልፍ እንዳበዛህ ምልክት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ወዳንተ የመጣው ወንጌል በቀላሉ ሳይሆን በዋጋ ነው ። ወዳንተ የመጡ ወዳጆችም ብዙ መሥዋዕትነት ከፍለዋል ። ለዛሬ ማንነትህ ማንነታቸውን ያጡ አሉ ። አገር እንዲኖርህ አፈር የሆኑልህ አያሌዎች ናቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

ቤተሰብ ሳለህ ሌጣ ፣ ሀብት ሳለህ ድሀ ፣ ወገን ሳለህ ብቸኛ ፣ ነጻነት ሳለህ ባሪያ ፣ አልጋ ሳለህ እንቅልፍ አልባ የሚያደርግህ ሰላም ማጣት ነውና ለሰላም ዋጋ ክፈል ። ስለ ጤናህ ለማመስገን እስክትታመም አትጠብቅ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ