ወዳጄ ሆይ !
አብረኸው ያደግኸውን ሰው አትርሳ ፣ የመጀመሪያው ንስሐ አባትህ እርሱ ነው ። አብረህ ጉዞ የጀመርከውን ሰው ታግሠህ ፈጽም ፣ የማትታገሠው ወገን የለምና ። አብረህ ያገለገልከውን ሰው አክብር ፣ በከበረው እርሻ ላይ ቆማችኋልና ። አብረህ የዘራኸውን በኅብረት እጨድ ፣ ሲካፈል የሚጣላ ሌባ ነውና ።
ወዳጄ ሆይ !
የቻለ ሰው ስታይ ያስቻለውን ጌታ አስብ ። ባቃተህ ነገር ላይም ክርስቶስ የበላይ መሆኑን እመን ። እንደ እመቤታችን መጠየቅ ተገቢ ሲሆን ለእግዚአብሔር የሚሳነው ነገር የለም ብሎ ማረፍ ደግሞ እምነት ነው ። ጠይቆ ብቻ መቅረት ፣ አምናለሁና ጥያቄ ኃጢአት ነው ብሎ መፍራት ተገቢ አይደለም ።
ወዳጄ ሆይ !
በብርቱ ጥረህ ያገኘኸውን ነገር አትተወዉም ። በቀላሉ ያገኘኸው በቀላሉ ይባክናልና ልፋትህን ውደደው ። ጣዖት እንዳይሆንብህ እግዚአብሔር የሰጠህ ነገር ቢጠፋ ምን እሆናለሁ አትበል ። ጸጋው ቢሄድ ባለጸጋው አለና ። መንገድ በመራህ ሰው ላይ መንገድ አትዝጋ ። ባስጠለለህ ሰው ላይ በሩን ቆልፈህ አትቀመጥ ። እኔ ተሻግሬአለሁ ብለህ እየመጣ ባለው ትውልድ ላይ ድልድይ አታፍርስ ። ብርሃንህ ጨለማ እንዳይሆን ከእኔነት ተላቀቅ ። ተመልክተህ እርገጥ እንጂ ረግጠህ አትመልከት ። ምንም ደፋር ብትሆን እግዚአብሔር ያከበራቸውን አታቃልል ። ያልገባህ ነገር ውሸት እንደሆነ አታስብ ።
ወዳጄ ሆይ !
የዓለም ታሪክ ሁሉ ጥሩ ስትሆን ክፉ ምላሽ እንደሚገጥምህ የሚናገር ነው ። ጥሩነትህ በሰዎቹ ሳይሆን በምክንያትህ ላይ የተመሠረተ ይሁን ። ከምክንያትም እምነት ጥሩ ሲያሠራህ ዋጋህን በሰማይ ትጠብቃለህ ። ያጽናናኸው ቢያቆስልህ የክርስቶስን የተቸነከሩ እጆች አስብ ። ያረጋጋኸው እንደ ሳኦል ጦር ቢወረውርብህ ዳዊት ልብህን ጎንበስ በል በለው ። ዝቅ ብለህ ጦሩን የምታልፈው ከሆነ ደረትን መስጠት ጀግንነት አይደለም ። ዘወር ስትልም ሰውዬውን ከገዳይነት ታድነዋለህ ። እችለዋለሁ የምትለው ሰው ሲበረታብህ አትደነቅ ። ትላንት ጊዜው ያንተ ነበረ ፣ ዛሬ ደግሞ የእርሱ ሁኗልና ዓለም ተራ መሆኑን ተረዳ ። ከሁሉ በላይ “የናቁት ያደርጋል ዕራቁት” የተባለውን አትርሳ።
ወዳጄ ሆይ !
በንጉሥ ፊት ባዶ እጅ መቅረብ ነውር ነውና ወደ ሰማይ ስትሄድ መክሊትህን እንዳተረፍህ አረጋግጥ ። ሕይወት ገበያ ናትና ለማግኘትም ለማጣትም ተዘጋጅ ። በምትሠራበት ዕድሜ ተቀምጠህ ፣ በማትሠራበት ዕድሜ መውጣት ፤ በሚቻልበት ጊዜ ተኝተህ በማይቻልበት ሰዓት መንቃት ትርፉ ቁጭት ብቻ ነው ። እግዚአብሔርን ቅጥር ሳታደርግ ከሰው ጋር አትጣላ ። በክንዱ የዘመተ በእግዚአብሔር ይሸነፋል ፣ በእግዚአብሔር ኃይል የወጣ ግን ማንም አያሸንፈውም ።
ወዳጄ ሆይ !
ዕፀ በለስ ለሞት በቂ ነበረ ብለህ ካመንህ ፣ ሥጋ ወደሙ ለሕይወት በቂ መሆኑን እመን ። እንዴት በሥጋ ወደሙ አትበል ፤ እንዴት በዕፀ በለስ አላልህምና ። መናፍቅነት አንዱን ጥሎ አንዱን አንጠልጥሎ ነው ። በአዳም መሞትህን ተቀብለህ በክርስቶስ መዳንህን ካልተቀበልህ እምነትህ ሙሉ አይደለም ። ለበደለ አዳም የካሰ መድኃኔ ዓለም ሊያስደንቅህ ይገባል ። ከፊት ለፊት ያለው ዘመን ክርስቶስ የሚመጣበት ፣ የመንግሥተ ሰማያት ርስት የሚከፈትበት ነውና የሚመጣውን አትፍራ ። ሁሉም የእኔ መድኃኔ ዓለም ሲለው ለሁሉ የሚበቃ ጌታ አለህና ደስ ይበልህ !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 14 ቀን 2014 ዓ.ም.