የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው/30

ወዳጄ ሆይ !

ታላላቅ የተባሉ ሲወድቁ ፣ አገር ይነሡ የነበሩ አገር ሲያጡ ፣ ይታዩ የነበሩ ሲደበዝዙ ፣ የደመቁ ጥርኝ አፈር ሲሆኑ እያየህ ይህን ዓለም አትውደደው ። ማዳን የእግዚአብሔር መለኮታዊ ገንዘብ ነውና ያድንህ ዘንድ ተጠጋው ። ክርስቲያንነት ደስ የሚያሰኘው ሁነህ ስትገኝ ብቻ ነው ። ሁሉ ያንተ እንዲሆን አትፈልግ ፣ ሁሉ ያንተ ቢሆን ማስተናገድ አትችልምና ። ሰዎች መልካም ብለው ለመናገር ፈልገው ቋንቋቸው ሰባራ ቢሆን ፣ ክፉ ብለህ አታስበው ። ጥቅም የምታገኝበትን ብቻ ሳይሆን ደስታ የምታገኝበትን ነገር ፈልገው ። በሆኑልህ ነገሮች ካላመሰገንህ በሚሆኑልህ ነገሮች አታመሰግንም ።

ወዳጄ ሆይ !

ለእግዚአብሔር የሰጠኸውን መልሰህ አትቀበል ። የተሠዋ ነገር በመሞቱ እንጂ በመነሣቱ አይከብርምና ። ሰጥቶ አምጣ የሚል ልጅ ፣ አሳይቶ የሚነሣ ዱርዬ ነውና ። ቅን ልብ የጨለማ ዘመን መብራት ነውና ቅንነት ይኑርህ ። ማስተዋል የሌለበትን ዓይናማነትን አትውደደው ። በልጆችህ መካከል አድልኦ ማድረግ መጨረሻህን ማበላሸት ፣ በትውልድ መካከልም ጦርነት መክፈት ነው ። ፍቅርህን በስውር ፣ ጥላቻህን በግልጽ አታድርገው ። ሰውን በፍቅር እንጂ በኃይል አትሳበው ። የሰው ወኪል ሁነህ አትዋሽለት ፣ የእግዚአብሔር ወኪል ሁነህ እውነት ተናገር ። የሚያደምጡህን አድምጣቸው ። ራስህ የሠራኸውን ራስህ እንዳታፈርሰው ሥራህን በችኩልነት አትፈጽመው ። የረዳሃቸው ሲረዱ ለማየት ናፍቆት ይደርብህ ። ትዕግሥት የጎደለው ቤት በተገነባ ቍጥር መፍረሱ ይፈጥናል ። በሽተኛን ከሚፈውስ ባለ ስጦታ ፣ የተከዘን ልብ የሚያጽናና ወዳጅ ይበልጣል ።

ወዳጄ ሆይ !

ሰዎችን “በጨለማ ናቸው” ብለህ ለመፈረጅ አትነሣ ፣ አንተ ጋ ያለውን ብርሃን በሕይወትህ አሳያቸው ። የመስማት ዕድል ሳያመልጥህ ቃለ እግዚአብሔርን ስማ ። የኖርክላቸው በሚገድሉህ ዓለም ላይ ነህና ልብህን ሰፊ አድርገው ። የተስፋ መሠረት እግዚአብሔር ብቻ ነው ። የወደቀው ሊነሣ ይችላልና እርግጫህን ቀንሰው ። የመሸባቸውን ስታይ ትላንት ለእነርሱ ቀን እንደ ነበረ አስታውስ ። እግዚአብሔርን በስሜት ሕዋሳቶችህ አረጋግጠው ። እዩት ፣ ስሙት ፣ ቅመሱት ፣ ዳስሱት የተባለው ለአማንያን ነውና ። ቶሎ ካልተወሰኑ የሚጎዱ ጉዳዮች አሉና ፈጣን ውሳኔ የሚያስፈልጋቸው ነገሮች ላይ ፍጠን ። ከምትወስንባቸው የምትታገሣቸው ነገሮች አሉና ጊዜ ስጣቸው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሰው በማጣት ብቻ ሳይሆን አግኝቶ ባለመርካትም ይቀጣልና “ጠላቴ ለምን አገኘ?” ብለህ አትዘን ። ከፊል ደስታ ከሙሉ ኀዘን በላይ ልብን ይጎዳል ። አጋር ከሌለው ደስታ አጽናኝ ያለው ልቅሶ ይበልጣል ። በድርጊትህ የምታድነውን በአንደበትህ ላትጋርደው ትችላለህና የተግባር ሰው መሆንን አትርሳ ። መጠላትን ተቋቋም ። በሚጠሉህ መሐል በመኖርህ እግዚአብሔርን አድንቅ ። ተቃውሞ ሲነሣብህ አትደንግጥ ። ሰይጣን እንደ አንበሳ በድምፅ ማሸበር ይወዳልና ። ምድራዊ መንግሥትን ስትደግፍ “መንግሥትህ ትምጣ” የምትለውን ጸሎት አትርሳ ። ስቅለትና ትንሣኤ ተናባቢ መሆናቸውን አስብ ። ስቅለት ባይኖር ትንሣኤ አይናፈቅም ፣ ሞትም ባይኖር ትንሣኤ አይነገርም ። ሞተህ ከሆነ ትንሣኤ አለህ ። ተነሥተህ ከሆነ ሞተህ ነበረ ። የመልፋት ግቡ በውጤት መደሰት ነውና ሁልጊዜ ባካና አትሁን ። ሰላምታና ፈገግታ አይከፈልበትም ። ለሁሉ ሰው ሰላምታ መስጠትን ፈገግ ማለትን አትርሳ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ