የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /33

ወዳጄ ሆይ !

ጥበብ ስትጠራህ አትዘግይ ፤ ዕድል ከጊዜ ጋር በማይፈታ ቋጠሮ ታስሯል ። ያልያዝከውን ለመጨበጥ ፣ የጨበጥከውን መልቀቅ አስፈላጊ የሆንበት ጊዜ አለ ። የማያዩ የሚያዩትን ፣ አላዋቂዎች አዋቂዎችን ሲተቹ ያ ዘመን ግልብጥ ዘመን ነው ። ጥሩ ሥራን ለሕሊና ምግብነቱ እንጂ ለሰማይ ሽልማቱ ብቻ አትሥራው ። የመልካም ነገር ዋጋ ከፋይ እግዚአብሔር መኖሩንም እመን ። ሁለት ጊዜ ደውለህ ፣ ሦስት ጊዜ ፈልገህ ሊያገኝህ ያልፈለገውን ሰው ፍላጎቱን አክብርለት።

ወዳጄ ሆይ !

ወንድምህ ሲጠቃ ቀጥሎ አንተም ተጠቂ ነህና በወንድምህ ክፉ ቀን ለራስህ ጩኽ ። ልጅህን በመንፈሳዊ ድፍረት ፣ በእውቀትና በእግዚአብሔር በመተማመን አንጸው ። መስበክ ማለት ወደ እሳት እየጨፈሩ የሚሄዱትን መመለስ ፣ ቀድሞ አይቶ ሰውን ማስጠንቀቅ ነው ፤ ስብከት እስትንፋስ ነው ። በመንፈሳዊ አንድነት ያለውን ክፍተት ቶሎ ካልዘጋኸው ፣ እንደ ሁለት የሸለቆ ግድግዳ እየተያዩ እንደማይገናኙ መሆን ነው ። ወደ ኋላ ያለውን ሰው ወደፊት አምጥተህ አለማምደው ። ጊዜና መድረክ የተሰወረ ጥበብን ይገልጻሉ ።

ወዳጄ ሆይ !

የተቀበለችህ አገር ላይ የአደጋ ስጋት አትሁን ። በብዙ መገኘት ቢያቅትህ ለወዳጅህ በጥቂቱ እንኳ ድረስለት ። መስጠት ባትችል አብረኸው መቆም ትልቅ ዋጋ አለው ። ሞልቶ የተረፈውን ክብርህን በሆዳምነትህ አታጕድለው ። ያለፈውን ጊዜ ለትምህርት ብቻ አስታውሰው ። ባለፈው ሲጸጸቱ መኖር መመጻደቅ ፣ ባለፈው መልካም ነገር ብቻ መኩራት መኖርን ማቆም ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

አንተም አንድ ቀን በሌላው አገርና ቤት እንግዳ ትሆናለህና ለእንግዶች ቅድሚያ ስጥ ። ንግግርህ ካስናቀህ ዝምታን ገንዘብ አድርግ ። ብዙዎችን ከማሸነፍ ራስን ማሸነፍ ይበልጣል ። ላንተ ቦታ የሌላቸውን ሰዎች ስታሳድድ አክባሪዎችህን እንዳታጣ ተጠንቀቅ ። ዱር የሚያስፈራህ ሰዎች ስለሌሉበት ነው ። ሰው የሌለበት ከተማ ከሲዖል በላይ ያስጨንቃል ። ስለ ጎረቤቶችህና ስለ ከተማው ሰው እግዚአብሔርን አመስግን ። ይህ ሁሉ ወገን የማትከፍለው ጠባቂህ ነው ።

ምክር ለሰሚው 33

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሰኔ 14 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ