ወዳጄ ሆይ!
የተገፉ ነገሥታት ፣ ያጽናኑ ወዳጆች ፣ የተዳፈነ ፍትሕ ፣ የሰዎች መልካምነት ፣ የወላጆች ደግነት ተደብቀው የማይቀሩ ሐቆች ናቸው ። በህልውናቸው የተወቀሱ በሞታቸው የተመሰገኑ መሪዎች ብዙ ናቸው ። በቍስላችን ስፌት የሚለማመዱትን ስናይ ያጽናኑንን ነገር ግን የረሳናቸውን እነዚያን የጨለማ መብራቶች እናስባለን ። ለጊዜው ሐሰት ያሸነፈ ቢመስልም ለዘላለም የሚያሸንፈው እውነት መሆኑን በግፈኞች ውርደት እንማራለን ። መልካሞችን የምናውቃቸው ካለፉ በኋላ መሆኑ የዓለምን ስቃይ በእጥፍ እንዲጨምር አድርጎታል ። ወላጆችንም ምን ያህል እንዳሰቃየናቸው ስንወልድ ይገባናል ፣ ውለታ ለመክፈል ስንዘጋጅ ግን እነርሱ አልፈው ይሆናል ። እግዚአብሔር በዚህ ብሩህ ሰማይ ላይ የተቀመጠው የተደበቀውን እውነት ሊያወጣ ነው ።
ወዳጄ ሆይ!
ዛሬ ላይ የተደላደሉ ፣ ለዘላለም የሚኖሩ መስሎህ አትፍራ ፣ ፀሐይም ትጠልቃለችና ። ጨርሶ አይጨልምምና ባጣኸው ነገር ውስጥ ያገኘኸው አስብ ። ክፉዎች ከሚወስዱብህ የሚሰጡህ ትምህርት ይበልጣል ። ከደጎች ይልቅ ጨካኞች ጉዞህን በማስተዋልና በጥንቃቄ እንድታደርግ ያስተምሩሃል ። የምቾት ቀጠናህ ሲነካ መብረር ትጀምራለህ ፣ ገፊ አድራሽ ነው ። እውነት ማር አይደለችምና አትጣፍጥም ፣ እየመረረች ግን ታድናለች ።
ወዳጄ ሆይ!
ያለ እውነት ፍቅር ሽንገላ ፣ ደግነት ማስታወቂያ ፣ ንግግር ቅጥፈት ፣ ትምህርት የተሳሳተ መረጃ ፣ ጥበብ ዝሙት ፣ ጉዞ ግብ የለሽ ፣ ጾም ረሀብ ፣ የሃይማኖት ልብስ ግብዝነት ነው ። የእግዚአብሔር ዙፋን እውነት ነውና ሥራህን በእውነት ሥራ ። በመጀመሪያ ቀን ግንኙነት የሰውን ጨዋነትና ደግነት አወቅሁ አትበል ። ሰው እንደ መጽሐፍ ነው ። ቀጣዩን ገጽ ካልገለጥከው መጽሐፍን አታውቀውም ፣ እያንዳንዱ ቀንና አጋጣሚም ሰውን በጥቂቱ የሚገልጠው አደባባይ ነው ። እስክትሞት ድረስ እንኳን የሰውን የራስህንም የማታውቀው ጠባይ አለ ። ሰው ታውቆ የማይጨረስ ፍጡር ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
በፍቅር የጀመረው የሰው የሕይወት ጉዞ የሚጠናቀቀውም በፍቅር ነው ። ፍቅር ትግሎችን ያቀላል ። እግዚአብሔር የጻፈው ሕይወትህ ርእሱ “መልኬ” የሚል ነው ። መቅድሙ ትእዛዜን ጠብቅ ፣ መግቢያው ኅብረት አስፈላጊ ነው የሚል ነው ። ምዕራፉ ለሌሎች ኑር ፣ ማጠቃለያው የዘላለም ቤት ደርሰሃል የሚል ነው ። እንዲህ የጻፈልህን አምላክህን አመስግን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 26 ቀን 2017 ዓ.ም.