ወዳጄ ሆይ!
እውነተኝነት ማለት ዓለም ሁሉ እየዋሸ እውነትን መናገር ነው ። ጥርጥር ሲያንገላታህ ማረፊያው ወደብ እምነት መሆኑን አስተውል ። ያለ ብርሃን መሰማራት ፣ ያለ እውነት ማወቅ የለም ። ብዙ መገለጫዎች ቢኖሩትም እግዚአብሔር አንድ ነው ። እግዚአብሔር አንድ በመሆኑ ለሚያምኑት አንድ ልብን ይሰጣል ። አምላክ ሁለት ቢሆን አንዱን ስታስደስት አንዱን ያስከፋህ እየመሰለህ ትሰቃይ ነበር ።
ወዳጄ ሆይ !
ዝና ያለ ደስታ ፣ ፍቅር ያለ ክብር ፣ ገንዘብ ያለ ቸርነት ፣ ትዳር ያለ መተዛዘን ፣ ልጅ ያለ ሥነ ምግባር ፣ ጉርብትና ያለ መረዳዳት ፣ ሕግ ያለ ተፈጻሚነት ፣ መንግሥት ያለ ሰላም ፣ ኢኮኖሚ ያለ ሞራል ፣ እውነት ያለ አስተማሪ ፣ መንገድ ያለ መሪ ፣ መንፈሳዊነት ያለ ትሕትና ፣ ክህነት ያለ ከባቴ አበሳነት ፣ ስብከት ያለ ጥበብ ፣ እረኝነት ያለ ትጋት ፣ ጌጥ ያለ ወገን ፣ ሀብት ያለ አገር ከንቱ ነው ።
ወዳጄ ሆይ!
የሰጠኸውን እርሳው ፣ የተቀበልከውን አትርሳ ። የመረጥከው ቀርቶ የተመረጠልህን ስትቀበል ሕይወት ካንተ ቁጥጥር ውጭ እንደሆነችም ተረዳ ። ማግኘትህን የምታውቀው የምትፈልገውን ስታውቅ ነው ። ለሕፃናት ውሸት ፣ ለወጣቶች ፍርሃት ፣ ለጎልማሶች ጥርጣሬ ፣ ለሽማግሌዎች ጭንቀት የምትሰጥ ዓለም ውስጥ መኖር ያሳዝናል ። ስለሚሰጥህ ነገር ሳይሆን ስለ ተሰጠህ ነገር አስብ ። ከሚሰጥህ የተሰጠህ ይበልጣልና ። እግዚአብሔር አብ አንድ ልጁን ሰጥቶሃልና ። በዚህ ዓለም ላይ ጭንቀትህን ወስደው አዲስ አየር የሚሰጡህ ድሆች ፣ ሕፃናትና እንስሳት ናቸው ። በሩጫህ ለመርካት አታስብ ፣ የሚያረካው ምንጭ ክርስቶስ ብቻ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
ሰዎችን የማስደሰት ጥረትህ ሰዎቹን በማስከፋት ይጠናቀቃልና ዝም ብለህ ለእግዚአብሔር ክብር ኑር ። ዓለምን የምታሸንፍበት ፣ ሰዎችን የምታስታግሥበት ምሥጢር በጊዜው የሆነ ዝምታ ነውና ይህን አትርሳ ። ወደ መጣህበት ብትመለስ ሕፃንና ፅንስ ነህ ፤ ወደ እውነቱ ብትገሰግስ የሰማይ ዜጋ ነህ ። ከዛሬ የትላንት ይሻል ነበር አትበል ፣ ከእግዚአብሔር እጅ የተቀበልከው ምንም ክፉ ነገር የለም ። መኖርህን በመወደድህ ሳይሆን ሰዎችን በመውደድህ ለካው ። የጥያቄህን መልስ ስታገኝ መልሱ ጥያቄ ይሆንብሃል ።
ወዳጄ ሆይ !
ያጠለቅኸው ጫማ ባዶ እግርህን ፣ የለበስከው ልብስ ዕራቁት መወለድህን ካስረሳህ ሞኝ ነህ ። በባዶነት ጀምረህ በባዶነት በምትጨርስበት ዓለም ሁሉ የእኔ ካልሆነ ብለህ አትታክት ። በድብቅ እየወደቅህ በገሀድ የወደቁት ላይ አትዘባበት ። ትምህርትህ ያልተማሩትን ካልረዳ አለማወቅ ነው ። ያንተን ትምህርት ዋጋ ያለው ያደረጉት ያልተማሩት ናቸው ። ጨለማን የማያስወግድ ብርሃን ራሱ ጨለማ ነው ። ፍላጎትህን ባለማወቅ የሰውን ድንበር አትግፋ ። በክብር ለመኖር ልክን ማወቅ መሠረት ነው ። ሐሰትን ከፈጠራት ያሰራጫት የከፋ ነውና የማታውቀውንም የምታውቀውንም ከመናገርህ በፊት አስብ ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 27 ቀን 2017 ዓ.ም.