ወዳጄ ሆይ !
የውስጥህን ለውስጥህ አምላክ ንገረው ። የውስጥህን ከአንተ የበለጠ እግዚአብሔር ያውቀዋልና ለራስህም ለሰዎችም ለማስረዳት ቃላት ብታጣ አትጨነቅ ። የውስጥህን ለሰዎች ማስረዳት ከባድ ትግል ነው ። ሰዎች የራሳቸው ውስጣዊ ችግር አለባቸውና የውስጤን አላወቁልኝም ብለህ አትዘንባቸው ። ትልቁ እብደትም የውስጥህን አደባባይ ማስጣት መሆኑን አትዘንጋ ። ለንስሐ አባትህ ፣ ለአማካሪህ ፣ ለወዳጅህ መናገር ያለብህን “የኢትዮጵያ ሕዝብ ይፍረደኝ” ብለህ አታውጅ ። ፍቅርህን የግልህ አድርገህ ጠብህን የአገር አታድርገው ። ገመናህን ለማይመለከተው ስታወራ መሳለቂያ ሆነህ ትቀራለህ ። ፍቅርህ ካለቀ በዝምታ ቅበረው ። ትዳርህ መቀጠል ካልቻለ መልካሙን ጊዜ ብቻ አስብ ። ሚስትህን አንተ ብታኮርፋት ልጆችዋ ይፈልጓታልና ስለ እርስዋ ክፉ አታውራ ። የቀድሞ ባልሽ ለልጆችሽ የቀድሞ አባታቸው አይደለምና ቂምን አታውርሺ ።
ወዳጄ ሆይ !
የውስጥህን ለውስጥህ ሰው ማዋየት እሳቱን ያበርድልሃል ። ጊዜና ዕድል እስኪገኝም የውስጥህን በውስጥህ መያዝ ክብር ነው ። ጊዜና ዕድል የተባሉትም ክፉ ላደረጉብህ መልካም የምታደርግበት መድረክ ነው ። ክፉ በማድረግ ሰይጣን ያስደሰቱ ናቸውና አንተ መልካም በማድረግ እግዚአብሔርን አክብር ።
ወዳጄ ሆይ !
አንተ ራስህን ሳታውቀው ገና በማኅፀን ሳለህ ፣ እኔ ነኝ ማለት ሳትጀምር ገና በለጋነትህ የሚያውቅህ እግዚአብሔር ነው ። እግዚአብሔር ሰው እንድትሆን ፈቀደ ፣ ቤተሰቦችህ ደግሞ የእኛ ነው ብለው ስም አወጡልህ ። ራስህን መፍጠር አልቻልህምና አትጨነቅ ። ነገ ምን እሆናለሁ አትበል ፣ ከመፈጠርህ በፊት ምን ነበርሁ ? ብለህ አስብ ። የገዛ ስምህን የማውጣት ሥልጣን አልነበረህምና አንተ ያንተ ከመሆንህ ይልቅ አንተ የእግዚአብሔርና የሰዎች ነህ ።
ወዳጄ ሆይ !
ሳትጸድቅ የምታጸድቅ ፈሪሳዊ ፣ ትምህርት የጠላህ አስተማሪ ፣ ምቾት የምታመልክ ሰዱቃዊ ፣ ክርስቲያናዊ ኑሮህን ጠልተህ አለባበሱን የያዝህ አስመሳይ ፣ የሰማይን ሳይሆን የምድርን ሙገሳ የምትናፍቅ ግብዝ ፣ የበሬ ሥጋን እየጾምህ የሰው ሥጋ የምትበላ ሐሜተኛ አትሁን ።
ወዳጄ ሆይ !
አገርን ከአገር የሚያስተካክለው የጦርነት አቻነት አይደለም ። ጦርነት ተባብሮ ወደ ሲኦል መውረድ ነው ። አገርህ ከሌሎች አገሮች ተርታ የምትሰለፈው በሥራ እንጂ በፉከራ አይደለም ። ለሰልፍ የወጣ ሕዝብ አንድ አንድ ድንጋይ ይዞ ቢመለስ ብዙ ሕንፃ ይሠራ ነበር ። አንድ አንድ ቆሻሻ ቢያነሣ ከተማ ይጸዳ ነበር ። አገር አልባ ስትሆን ያስጠጉህ አገሮች እየረዱህ እንጂ እየሠራህ መሆኑን አይቀበሉም ። ሠርተህ ለመከበርም አገር ያስፈልግሃል ። አገርህን አፍርሰህ የሰው አገር ስትሄድ አንተን ማስጠጋት ይፈራሉ ። አገሩን ያፈረሰ አገራችንን ያፈርሳል ፣ በወገኑ የጨከነ በወገናችን ይጨክናል ብለው ይጠሉሃል ። አገርህን በአገርህ ለመኖር ብቻ ሳይሆን በሰው አገር ለመኖርም ስትል አሳድጋት ።
ወዳጄ ሆይ !
በአንድ ቀን ትውውቅ ሰዎችን አትገምት ። በፈገግታቸው ብቻ የቅዱስነት ማዕረግ አትስጣቸው ። በቁንጽል ደግነትም ፍጽምናን አታጎናጽፋቸው ። ቤተ ክርስቲያን አንድን ሰው ቅዱስ ብላ ለመሰየም ከሞተ በኋላ ከሃምሳ ዓመት በላይ ትቆያለች ። ሰውን ሙሉ ቅዱስ ለማለት ከሞተ በኋላ ሃምሳ ዓመት ያስፈልጋል ። የሰው አካሉ እንደ ስልክ ቀፎ ፣ ውስጡ ግን እንደ ሲም ካርዱ ነው ። አካሉ ይጨበጣል ፣ ውስጡ ግን ረቂቅ ነው ።
ወዳጄ ሆይ !
የበላይ እግዚአብሔርን ሳትይዝ በሰዎች ላይ የበላይ አትሁን ። ጌታ የሌለው ጌታኬሰው ቄራ ያዘጋጃል ። መንፈሰ እግዚአብሔር የማይመራው ሰውን ለአጋንንት መሥዋዕት አድርጎ ያቀርባል ። ባዕድ አምልኮ ሲወገዝ የኖረው ልጅን ሳይቀር ለአጋንንት ስለሚሠዋ ነው ። ልጁን የሰጠህን እግዚአብሔር ማምለክ ካልቻልህ ልጅህን የሚነጥቅ ሰይጣንንና ርእዮተ ዓለምን ለማምለክ ትዳረጋለህ ። የምትችለውን ሳታደርግ የማትችለውን አትመኝ ። በጥቂቱ ሳትጀምር ስለ ትልቅ ዕቅዶችህ ሐተታ አታብዛ ። ያንተ ፀሐይ እንድታረፍድ ፀሐይ ላዘቀዘቀችባቸው ራራ ። “እሾሁ ከወጋህ ጽጌረዳዋ ጋ ተቃርበሃል ማለት ነው” የሚባለውንም አትርሳ ።
የሰማነውን በልቡናችን ያሳድርብን !