የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ምክር ለሰሚው /7

ወዳጄ ሆይ !

የምድር ኑሮህ ሲኦል ሆነ ማለት ሲኦል አይገጥምህም ማለት አይደለም ። ወደ ሰማይ መንግሥት የምትገባው በኑሮህ ጎስቁልናና ድሎት ሳይሆን በሃይማኖትህ ነው ። የሰማይ ዋስትና ድህነት ሳይሆን የክርስቶስ ጸጋ ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

አንሥተው ሲጥሉህ ላይለቅ የያዘህን እግዚአብሔር አስብ ። አክብረው ሲያዋርዱህ ስላንተ የተራቆተውን ክርስቶስ በዓይነ ልቡናህ ተመልከተው ። አድምቀው ሲሰርዙህ በሕይወት መጽሐፍ የጻፈህን አምላክ ተመስገን በለው ። በመሳሳትህ አትፈር ። መሳሳት የሥራው መጀመር ምልክት ነውና ። ሌሎችም ከስህተታቸው እንዲማሩ እንጂ እንዳይሳሳቱ አትጠብቅ ። ተሳስተውም ተስፋ ስናደርጋቸው ከበደሉት በላይ የሚክሱ ይሆናሉ ። በጥፋቴ እንዲህ ያበረታኝ በልማቴ የበለጠ ይደሰትብኛል ብለው ትንሣኤ ልቡና ያገኛሉ ። ምንም የለኝም አትበል ። ይህች ቀን ያንተ ስጦታ ናት ። ምንም አልሰጥም አትበል ፣ ፈገግታም ልባቸው ላዘነባቸው ብርሃን ሰጪ ጨረር ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ሥራህን አጥብቀህ ያዘው ፣ ጭንቀትህን ግን ቀለል አድርገህ ሸክፈው ። የምትፈልገውን ነገር ለማግኘት በበሽታና በእብደት ተጽእኖ አትፍጠር ። የምትፈልገውን ብታገኝም ሰዎች ግን እንደ ተበላሸ ሰው ይቆጥሩሃል ። አሳብህን በግልጥ የመናገር ልምድ ይኑርህ ። ታውከህ ሰውን አታውክ ። ወዳጅህን አጥብቀህ ምከረው እንጂ እኔ ልራመድልህ አትበለው ። ማስተማርህ ጊዜህን እንጂ ሰላምህን የምትሠዋበት አይሁን ። ብርሃንህን ውደደው ፣ አለማወቅን ግን አታድንቅ ። ያለህ ነገር ያልነበረህ ነበርና አመስግንበት ፤ ያለህ ነገር ላይኖርህ ይችላልና አክብረህ ያዘው ። በስስት የምትመራው ቤትህ ብሽሽቅን እየወለደ ይመጣል ። ሚስትህን እንደ ገረድ ፣ ልጆችህን እንደ ልዑልና ልዕልት መያዝ ትልቅ ውርደት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

የሰብዊነት ሥራ ለሰው ሁሉ የሚደረግ ፣ የዜግነት ሥራ ለተወለዱበት አገር አንድ ጠጠር መጣል ፣ የመንፈሳዊነት ሥራ ለሰው ነፍስና ሥጋ ማሰብ ነው ። ደስተኛ ያልሆንከው የሚያስደስቱ ሰዎችና ሁኔታዎች ስለሌሉ ሳይሆን ማየት የሚገባህን ነገር ማየት ባለመቻልህ ነው ። ስብሰባዎች ውስጥን ያክማሉ ፣ የታመመ አገር ግን በስብሰባ ብቻ አይድንም ። ቤቶች ማደሪያ የሚሆኑት አገር ሲኖር ብቻ ነው ። ሰላም በሌለበት ከተማ መሶብህ ሙሉ ቢሆንም የመብላት ዕድል የለህም ። ቅድሚያ መስጠት ያለብህ አንተን ለመቀበል ለፈቀዱ ወገኖች ነው ። “ለገቢህ ተንገብገብ” ነውና ። ጠላትህን ውደድ ማለት ወዳጅህን አቃልል ማለት አይደለም ። በጎ ማድረግ እነ እገሌ እስኪጀምሩ የሚባልበት ሳይሆን ግላዊ ኃላፊነት ነው ።

ወዳጄ ሆይ !

ካሉበት ድረስ ሂዶ ክርስቲያኖችን መጎብኘት ለእነርሱ ትልቅ መነሣሣት ፣ ላንተ ትልቅ ደስታ የሚያስገኝ ነው ። ነፍስህ ያገኘችውን በረከት ለሌላው መመኘት የመባረክህ ምልክት ነው ። እግዚአብሔር የነገረ መለኮት እውቀት ባላቸው ብቻ ሳይሆን ቀናዒነት ባላቸው የዋሃንም ይጠቀማል ። መዘግየትህ ብዙ አደጋ እንዳያስከትልብህ ሥራህንና ኃላፊነትህን በጊዜው ተወጣ ። “የጠላቴ ጠላት ፣ ወዳጄ ነው” የሚለው ስልት የሚጠቅመው ለጥቂት ጊዜ ነው ። የጠላትህ ጠላት አንድ ቀን ያንተ ጠላት ይሆናል ። ፍቅር በፍቅር ላይ ብቻ ይመሠረታል ። አንተም የአደባባይ መራቆት እንዳያገኝህ ሰውን ሲራቆት አልብስ ፣ ከሚያራቁቱ ሰዎች ጋር በአሳብም ቢሆን አትተባበር ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ