የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሞት

  

ሞት መለየት ነው ። ሞት ከሥጋ መለየት ነው ። ሞት ከወዳጅ መለየት ነው ። ሞት ከዚህ ዓለም መለየት ነው ። ትልቁ ሞት ግን ከእግዚአብሔር መለየት ነው ። ሰው በሥጋው ሲሞት ዘመድ ያለቅስለታል ፣ በሕሊናው ሲሞት ምሁር ያለቅስለታል ፣ በመንፈስ ሲሞት ካህን ያለቅስለታል ። ሞት የዚህ ዓለም ጉዞ ምዕራፍ እንጂ የሕይወት የመጨረሻ ምዕራፍ አይደለም ። ሞት ፈራጅ ነው ፣ መኰንኑንም ይወስደዋል ። ሞት ጠባቂ አይፈራም ፣ ንጉሡንም ከቤተ መንግሥት አውጥቶ ጭቃ ላይ ይጥለዋል ። ሞት ለመባላታችንና ለመነካከሳችን መግቻ ነው ። “እግዚአብሔር ትክክለኛውን የፍርድ ሚዛን ለሞት አስጨብጦታል ።” 

ሀብት ያለው እየሞተ ፣ የሌለው ይኖራል ። ሞት የእግዚአብሔር ጥሪ ነውና ሰው ራሱን መጥራትም ፣ ለምን እገሌ ተጠራ ማለትም አይችልም ። እግዚአብሔር ወዳጆቻችንን በሞት የሚወስደው ከዚህ በኋላ የሚያዩትንና የሚሰሙትን አይቋቋሙትም ብሎ ነው ። ዐረፉ ብሎ ማዘን ፣ ወደ አባታቸው ሄዱ ብሎ መበሳጨት ፍትሐ አምላክን መቃወም ፣ ደግሞም ምቀኝነት ነው ። የአባት ሞት በዕለቱ ፣ የእናት ሞት በዓመቱ ይቆረቁራል ። የሞቱት ወገኖች መማሪያችን እንጂ ማዘኛችን አይደሉም ። ታክቶ ቶሎ ውሰደኝ ቢሉት ፣ ዕድሜ ረዝሞም ሞት የቀረ ቢመስልም ሞት ግን ይመጣል ። ሞት የዚህች ዓለም ጉብኝት ማብቂያ ነው ። ሞት የዘላለም ኑሮ መክፈቻ ነው ። 

ባንወደውም ዕለት ዕለት የምንጓዘው ወደ ሞት ነው ። ጥርስ ሲሰበር ፣ ዓይን ሲፈዝዝ በትንሹ እየሞትን ነው ። ዕለት ዕለት ወደ ሞት ብንጓዝም መሞታችንን ግን አናምንም ። ምክንያቱም አስቀድሞ ስንፈጠር ለሕይወት እንጂ ለሞት አልተፈጠርንምና ነው ። ሞት የኋላ ዕዳ ነው ። የሚገርመው ሟች ሰው ፣ ሰውን መግደሉ ነው ። ከቃሉ ያልተማረ ከሞትም አይማርም ። ለእነ እገሌ ያልሆነ ዓለም ለእኔ ይሆናል ብሎ ማሰብ ሞኝነት ነው ። የፍርድ ቤት ጥሪ ከአገር ቢወጡ ያመልጡታል ፣ የምርቃት ጥሪ ካልፈለጉ ይቀሩበታል ፤ የሞት ጥሪ ግን ያለ ምክንያት ይሄዱበታል ። ያን ቀን እንቢ ላንል ዛሬ ለንስሐ እንቢ ማለታችን ይገርማል ። ሞት እያንዣበበን ንስሐ ካልገባን መቼ ልንገባ ነው ? እነ እገሌ በሞኝነት ሞተው እኛ በብልጠት አልቀረንምና ንስሐ እንግባ ፣ እንታረቅ ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ሐምሌ 22 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 2

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ