በሽታ ሩቅ አይደለም፣ የተዘረጋው እጅ አሁን መታጠፍ ሊቸግረው ይችላል። የዘረጋነውን የምናጥፈው በሥላሴ ቸርነት ነው። በድንገት ዓይናቸው ማየት እንቢ ያለው፣ ለምሳ ገብተው በዚያው ሳይወጡ የቀሩ ብዙ ዓይናማዎችን እናውቃለን። ሞትም ቅርብ ነው። ሞት ከፈለገ በሰበብ ካልፈለገ ያለ ምክንያት ይወስደናል። የሌሎች ሞት የእኛን ሞት የምናይበት መስተዋት ነ ው። ሕይወት በምድር ላይ አጭር ናት፣ በሰማይ ግን ረጅም ከ እስከ የሌላት ናት። ተወርዋሪ ኮከብ በፍጥነት ታይቶ ይጠፋል ። የሰውም ዕድሜ እንዲሁ ታይቶ ጠፊ ነው ።
“ሕይወታችሁ ምንድር ነው? ጥቂት ጊዜ ታይቶ ኋላ እንደሚጠፋ እንፍዋለት ናችሁና።” (ያዕ. 4:14)።
የሰው ሕይወት እንደ እንፍዋለት ናት ። እንፍዋለት ክዳኑን ይሰቀስቃል፣ በኃይል ያንኳኳል፣ ይፍለቀለቃል፣ የተጣደበትን ዕቃ ያንቀጨቅጨዋል ፣ ድምፁ ያስገመግማል ፤ የሰማውን ሁሉ ቶሎ በሉ ያሰኛል ። ሲከፍቱት ግን ወዲያው ይተነፍሳል፣ ፀጥታው ለዘላለም፣ ሙቀቱ ለበረዶ ተላልፎ ይሰጣል።
የሰው ሕይወት እንደ እንፍዋለት ናት። ቤቱንና አገሩን ያስጨነቀው፣ እየመጣሁ ነው መንገድ ልቀቁል በር ክፈቱልኝ የሚለው ፣ አገሩን ያወከው፣ መሬት የጠበበው፣ ሁሉን ላፌ ያለው፣ ድምፁ የሚያስደነብረው ያ ሰው እስከ ወዲያኛው ዝም ይላል። በምድር ላይ ዳግም ላይባርቅ ፀጥታን ይዛመዳል። የሰው ሕይወት እንደ እንፍዋለት ነው። ይተናል፣ ይጠፋል። ሰው ለቀጠሮ የማይሆን፣ ቆይ ሌላ ጊዜ የማይሉት ባካና ፣ ታይቶ ለመጥፋት ሰከንድ የሚበቃው ነው።
ጎረቤታችን ታሞ ለመጠየቅ አንድ እርምጃ ይርቀናል። ሲሞት ግን ሺህ ኪ.ሜ ሄደን እንቀብራለን። በሕይወት ካለ አይመቸንም፣ ሲሞት ግን ይመቸናል። ሰውን መርዳት በቁመና፣ መጠየቅ እስትንፋሱ በአፍንጫው ሳለች ነው።
ለአንዳንድ ወዳጆቻችን ትልቅ ነገር ለማድረግ እናስባለን። ከምንሠራው ፎቅ አንዱን ወለል ለእነርሱ ለማድረግ እንፈልጋለን። ዛሬ ግን የቤት ኪራይ ቸግሯቸዋል። ቁርስ በልተው ምሳ መድገም አይችሉም። በችግር ቀን የተገኘ ትንሽ ስጦታ ትልቅ ነው። እነዚህ ሰዎች ያሰብንላቸውን ትልቅ ስጦታ ልንሰጣቸው ስንል በሕይወት የሉም። ለሰው ትልቅ ነገር ማሰብ ጥሩ ነው፣ ለዛሬ የሚያስፈልገው ግን ትንሹ ስጦታ ነው። የስጦታ መልካምነቱ አነሰ በዛ ሳይሉ የሚሰጡት ነው። አዎ “እኔ የምሞተው ዛሬ ማታ ገብሱ የሚደርሰው ለፍልሰታ” ይባላል።
ጠቢቡ ከፀሐይ በታች ሁሉ ከንቱ መሆኑን፣ ተናግሯል። ከፀሐይ በላይ ግን እውነቱ አለ። ዛሬ ወደህዋ ስለ መምጠቅ ፣ ስለ ተራቀቀ የጦር መሣሪያ ኃይላን አገራት የደረሱበት ቴክኖሎጂ እየተመለከ ነው። ግን ይህም ከንቱ ነው። ከንቱ ማለት ውሸት፣ ባዶ ፣ የማይጨበጥ፣ አለኝ ብለው ሊያሳዩት ሲሉ እንደ ወፍ የሚበርር ነው።
ሞትን በዓይናችን ያየንበት ቅጽበት ብዙ ነው። ቆመንበት የነበረው ቦታ ላይ በአምስት ደቂቃ ልዩነት አደጋ ሲከሰት ያ ሞት የእኛ ነበር። ከባድ መሳሪያ አጠገባችን ወድቆ ሌላው ሞቶ እኛ ስንተርፍ ያ ሞት የእኛ ነበር። ሞትን ግን በዓይናችን አይተነዋል። በታላቅ ሰመመን ውስጥ ገብተን አበቃላቸው ስንባል እግዚአብሔር በፈውስ ጎብኝቶናል። ሞትን ዓይተን ሕይወት ተመርቆልናል። በዚህ ጊዜ የሚሰማን ነገር አንድ ነው :- እርሱም ቅዱስ ፍርሃት ይባላል።
ሞትን ዓይተን በሕይወት ስለ ኖርን ጌታችን ሆይ ተመስገን! ላኖረን ችሎታህ መገዛትን ስጠን!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 8 ቀን 2017 ዓ.ም.