የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ረቡዕ ሚያዝያ ፲፭፣ ፳፻፮ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን፳
መግቢያ
በመጽሐፍ ቅዱስ ውስጥ ለእግዚአብሔር ያላቸውን ጥልቅ ፍቅር የገለጡ ብዙ የእግዚአብሔር ሰዎችን እናገኛለን፡፡ እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች እግዚአብሔር እንዴት እንደወደዳቸው ተረድተው እነርሱም ወደውታል፡፡ ፍቅራቸውንም በኑሮና በሕይወታቸው መስክረዋል፡፡ ብዙዎቻችን እግዚአብሔርን፡– የመውደድ ዕዳ ያለበት፣ መጥላት ስለማይችል የወደደን፣ የእኛን ፍቅር ግን ለመስማት የማይፈልግ አድርገን እናስበዋለን፡፡ ነገር ግን አፍቃሪ ፍቅር ይፈልጋል፡፡ እግዚአብሔርም ፍቅራችንን መስማትና ማየት ይሻል፡፡ በእርግጥ እግዚአብሔርን በማስመሰል ፍቅር ልንወደው አንችልም፡፡ እርሱ የተሰወረውን የውስጥ አሳብ ያውቃልና፡፡ በእውነተኛ ፍቅር ግን እንድንወደው ይፈልጋል፡፡
እግዚአብሔር እንዴት እንደወደዳቸው የተረዱ እነዚህ የእግዚአብሔር ሰዎች እርሱን መውደድ ብቻ ሳይሆን መውደድ የሚያስከፍለውንም ዋጋ በመክፈል በኑሮና በሞታቸው አስከብረውታል፡፡ ከእነዚህ ዕድለኞች አንዷ መግደላዊት ማርያም ናት፡፡ ታሪኳ የተዋበ፣ የመጣችበት መንገድም የቀና ባይሆንም ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ስምና ታሪኳን በመለወጥ ከሰው ቍጥር ደምሯታል፡፡ ከታላቅ ስቃይ ወደ ታላቅ ዕረፍት መልሷታል፣ ለአንድ ቀን እንኳ ማዕበል ካልተለየው ኑሮ አውጥቶ በታላቅ ፀጥታ አሳርፏታል፡፡ ታዲያ ለሰላሟና ለሕይወቷ ጌታ ፍቅሯን የምትገልጥበት ሁነኛ ሰዓት ደረሰ፡፡ ያ ጊዜ ፍቅሯ የሚመዘንበትም ጊዜ ነበረ፡፡ ጌታችን ሲሰቃይ ከመስቀሉ አጠገብ አልተለየችም፡፡ ሞቶም አልረሳችውም፡፡ ቅዱስ ሥጋውን ሽቱ ልትቀባ ወደ መቃብሩ ገሰገሰች፡፡ እርሱ ግን ሕያው ነውና የሙታንን ሽቱ አልተቀባም፡፡
መግደላዊት ማርያም ያንን ደግ መምህር ለዘላለም ያጣችው መስሏት ልቧ በሀዘን ተሰብሯል፡፡ ቢያንስ ቅዱስ ሥጋውን ሽቱ ቀብታ ለመሰናበት ብትመጣም ሥጋውንም በማጣቷ ሀዘኗ ወደር የሌለው ሆነ፡፡ የተሰረቀ ስለመሰላት መሰረቁን ለደቀ መዛሙርቱ ነገረች፡፡ የተሳሳተ ምስክርነት ቢሆንም ጌታዋ ሲገለጥላት ግን እውነተኛ ምስክርነት ይዛ ወጥታለች፡፡ መላእክት ቢገለጹላትም መረጋጋት አልቻለችም፡፡ ነፍሷ የሻተችውን እስክታገኝ ዕረፍት አልነበራትም፡፡ ቅዱስ ሥጋውን ባገኘው እወስደዋለሁ የሚል ቍርጥ አሳብ ያዘች፡፡ ይህ ከባድ ነው፡፡ የት ታደርገዋለች? ፍቅሯ ግን ይህን ለማድረግ ጨክኗል፡፡ በዚህ ጊዜ ጌታችን ተገለፀላት፡፡ እርሱም በስሟ ሲጠራት «ረቡኒ» አለችው፡፡ መምህር ሆይ ማለቷ ነው፡፡ ዛሬም የምትማረው፣ ገና ያልገባት ነገር ስላለ መምህር ሆይ ብላ ያስተምራት ዘንድ ፈለገችው፡፡
በዘመናት ሁሉ ሕዝቦች መምህር ይፈልጋሉ፡፡ የመምህር ፍላጎታቸው ግን የጨው ውሃ እንደጠጣ መልሶ ያስጠማቸዋል እንጂ እንደ ልባቸው የሚሆን መምህር አላገኙም፡፡ መምህራን ነን ብለው የተነሡም በየዘመናቱ ተረኛ ተመጋቢዎች እንጂ መጋቢዎች ስላልሆኑ እልፍ ይላሉ፡፡ እነርሱ ፌርማታውን ያውቁታልና ያለይሉኝታ ሲወርዱ እስከ መጨረሻው የተሳፈራቸው ሕዝብ ግን መድረሻው ግራ ገብቶት ይቅበዘበዛል፡፡ አሁንም እውነተኛውን መምህር ክርስቶስን ከመፈለግ ሌላ መምህር ከሰማችሁ አፋልጉኝ እያለ ገና ለመንከራተት ይኖራል፡፡ መምህር ፍለጋ ከአንዱ እምነት ወደ አንዱ እምነት ሲንከራተቱ በየዱሩ የቀሩ፣ የጨካኝ መምህራን ነን ባዮች የግፍ ማርኪያ የሆኑ ብዙዎች ናቸው፡፡ ይህ ሁሉ ለልባችን የቀረበውን እውነተኛውን መምህር «ረቡኒ» ያለማለታችን ቅጣት ነው፡፡ መምህሩን «መምህር ሆይ» ብለን ስንቀርበው እውነተኛ እረኞችን ይሰጠናል፡፡ እረኞች ሁሉ በግ ያሰማራሉ፡፡ እውነተኛው መምህር ክርስቶስ ግን በግ ያደርገናል፡፡
ነቢዩ፡– «ልጆችሽም ሁሉ ከእግዚአብሔር የተማሩ ይሆናሉ. የልጆችሽም ሰላም ብዙ ይሆናል» (ኢሳ. 54.13) በማለት ተናግሯል፡፡ እግዚአብሔርን መምህር አድርገን ባልተመላለስንበት ዘመን ሁሉ ብንማርም ሰላም አልነበረንም፡፡ ከእርሱ ለመማር ስንቀርብ ግን ሰላሙን አብዝቶልናል፡፡ታዲያ የእኛስ መምህራችን ማን ነው? ከፍ ያሉትና ትልቅ ተስፋ የጣልንባቸው ሲሰወሩብን እጃችንን ይዞ የሚመራን መምህራችን ማን ነው? አዎ ከሰው የታጣ የሚገኝበትታላቅ መምህር አለ፡፡ እርሱም የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
ይህች አነስተኛ መጽሐፍ ለፍቅሩና ለመምህርነቱ የማትመጥን፣ የመግደላዊት ማርያም ፍቅሯ፣ ፍቅራችንን ቢታዘበው ለማረፍ ተብሎ የተጻፈ ነው፡፡ የሚያጽናናና የሚመክር መምህር ለተራበው ለዛሬው ትውልዳችን ይህች መጽሐፍ መቅረዝ እንደምትሆን እናምናለን፡፡ ለወደደን ከኃጢአታችንም በደሙ ላጠበን ለጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የከበረ አምልኮት ይሁን፤ አሜን፡፡
ረቡኒ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2002 ዓ/ም
አድራሻ – 0911 39 35 21/0911 67 82 51
ፖ.ሳ.ቁ. 62552
አ.አ. ኢትዮጵያ