የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቡኒ መጽሐፍ – ድንጋዩን ተፈንቅሎ አየች

የዲ/ን አሸናፊ መኰንን ገጽ
ረቡዕ  ሚያዝያ ፳፱፣  ፳፻፮ ዓ/ም
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ አሜን
                                          
ተፈንቅሎ አየች
ወንጌላዊው ማርቆስ፡- «እርስ በርሳቸውም፡- ድንጋዩን ከመቃብር ደጃፍ ማን ያንከባልልልናል? ይባባሉ ነበር» (ማር. 16፣3) በማለት ጽፎልናል፡፡ መግደላዊት ማርያም በእርሷና በክርስቶስ መካከል ጋሬጣ የሆነው ትልቅ ቋጥኝ በመንገዷ ሁሉ ያሳስባት ነበር፡፡ ዛሬም ጌታችንን እንዳናገኝ ብዙ ቋጥኞች አስጨንቀውን ይሆናል፡፡ መግደላዊት ማርያም ግን ቋጥኙን ባትችለውም አለመቻሏ ጉዞዋን አላደናቀፈውም፡፡ ጥያቄና ስጋት የሆነባት ነገር ሕያው ቢሆንም ወደኋላ አልተመለሰችም፡፡ ውጤቱ ግን ሕያው የሆነው ቋጥኙ ሳይሆን ኢየሱስ ክርስቶስ ነበር፡፡ «ድንጋዩ ተፈንቅሎ አየች» ( ዮሐ. 20፣1 )፡ ዛሬም ክርስቶስን ለማየት የሚከለክሉ ብዙ ቋጥኞች አሉ፡፡ ከክርስቶስ በላይ መከበር የሚፈልጉ፣ የስም ቁልል እንደ ተራራ የተጫናቸው፣ ሰው ሳይሆኑ መልአክ ተብሎ እንዲነገርላቸው የሚሹ ትልልቅ ቋጥኞች ዛሬም አሉ፡፡ እነዚህ ቋጥኞች ልባቸው ሳይሰበር እናገለግላለን የሚሉ አገልጋዮች ናቸው፡፡ እግዚአብሔርን ለሚፈልግ ለዛሬው ትውልድ እነዚህ ቋጥኞች ስጋት ቢሆኑም እግዚአብሔርን ፈላጊ ትውልድ በስጋቶች አይቆምምና ወደ ክርስቶስ መገስገስ ያስፈልጋል፡፡ ያን ጊዜ ቋጥኙ ተንከባሎ የተነሣውን ጌታ የምሥራች እንሰማለን፡፡
ዛሬስ ክርስቶስን እንዳናይ ጋሬጣ የሆነብን ነገር ምንድነው? ኃጢአትና ሱስ ይሆን? በእምነት እንጓዝ ቋጥኙ ይንከባለላል፡፡ ክርስቶስን ለምትፈልግ ነፍስ ትልቅ ሆኖ የሚያስፈራት ችግር የለም፡፡ ከትልቅ ችግራችን ይልቅ ክርስቶስ ትልቅ ነው፡፡ ከፍ ካለው ነገር በላይ ከፍ ያለ የሞት መድኃኒት ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፡፡
የምንፈልጋቸውና እንዲሆኑልን የምንመኛቸው ብዙ መልካም ነገሮች ቢኖሩም «ድንጋዩን ማን ያንከባልልልናል?» የሚል ስጋት ግን አለብን፡፡ ራእያችን፣ ትዳራችን፣ ወዳጅነታችን የራሱ የሆነ የፈተና ቋጥኝ አለው፡፡ የማይቀር ሆኖብን ብንጀምረው እንኳ ልባችን ግን ይፈራል፡፡ በእምነት ብንጓዝ ግን ድንጋዩ ተፈንቅሎ እናይ ነበር፡፡ የእስራኤል ልጆች ባሕር የተከፈለላቸው በመጓዛቸው ነው፡፡ እግዚአብሔር ወደፊት ለሚሉ ባሕር መክፈል፣ ቋጥኝ ማንከባለል ልማዱ ነው፡፡ ሕይወት በእኛ መቻል ላይ የተመሠረተች አይደለችም፡፡ እኛ ምንም የማንችል ደካሞች ነን፡፡ ሕይወት ሂደት ብቻ ሳይሆን ተአምራዊ ድልም የሚያስፈልጋት ናት፡፡ እግዚአብሔር ወደፊት በእምነት ለሚገሰግሱ ባሕር የመክፈል፣ ድንጋይ የማንከባለል ኃይሉን ያሳያቸዋል፡፡ እየተጓዝን ነው ወይስ ፍርሃታችንን ከቃሉ ይልቅ አምነን ቆመናል?

ለማንም ሰው መቃብር ቋጥኝ አይገጠምም፡፡ የኢየሱስ ክርስቶስ መቃብር ግን ቋጥኝ ተደርጎበታል፡፡ ዓለም ገድላም የፈራችው ቢኖር ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ አስቸጋሪ የተባሉ ሰዎች ሁሉ ከሞቱ በኋላ አስጊነታቸው ያበቃል፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ሞቶም ያስፈራል፡፡ በእርሱ ላይ እንደሆነው በተከታዮቹ ላይም ይሆናል፡፡ ሞተንም የምናስፈራበት ጊዜ ብዙ ነው፡፡ ደክሞኛል፣ ብዙ ማገልገል አቅም የለኝም እያልን ጠላት ግን ከባድ ሥራ ሊሠራ አድፍጧል እያለ መከራ ያውጅብናል፡፡ በብርታታችን ዘመን ያልተወለዱ ሰዎችንም በድካማችን ዘመን ሲወለዱ እናያለን፡፡ ቃሉ፡- «ምንም እንኳ ቢደክሙ ያሳድዱ ነበር» (መሳፍ. 8፣4) የሚለው ለእኛም ሲፈጸም አይተናል፡፡ ለጳውሎስም የተነገረው፡- «ጸጋዬ ይበቃሃል ኃይሌ በድካም ይፈጸማልና» (2ቆሮ. 12፣9) የሚለው ዛሬም ይሠራል፡፡ የሚሠራው ብርታታችን ሳይሆን ጸጋው ነው፡፡ ጸጋው ደግሞ ለመሥራት የሚመቸው ስንደክም ነው፡፡ እግዚአብሔር በዘመናት ሁሉ ከሥጋ ጋር በሽርክና ሠርቶ አያውቅም፡፡ አካላችን በደዌ ሲጠወልግ አገልግሎታችን በጸጋ መለምለም ይጀምራል፡፡
ትንሣኤውን አላመነችም
መግደላዊት ማርያም ሞቶም ትፈልገዋለች፡፡ የፈለገችው የገደሉትን የአይሁድ ካህናት፣ «የዓርብ ገዳይ ነን» ብለው ለራሳቸው የሚፎክሩትን  ሳይሆን ስለ ፍቅር የሞተውን ኢየሱስ ክርስቶስን ነው፡፡ ሞቱን እንደ መረታት አልቆጠረችውም፡፡ ስለ ፍቅር የሚሞት ከገዳዮች ይልቅ እርሱ ጀግና ነውና፡፡ ሞቱ እንድትረሳው አላደረጋትም፡፡ ፍቅሯን እንድትገልጥለት ውለታው አስገደዳት፡፡ ሞቱ የቅርብ ደቀ መዛሙርቱን ሳይቀር ያስበረገገ ቢሆንም እርሷ ግን ከጊዜ ጋር አልተለወጠችም፡፡ ከራሷ ይልቅ ስለ ክርስቶስ ፍቅር አሰበች፡፡ ፍጹሙ ፍቅር ራስን በመርሳት ስለ ክርስቶስ ማሰብ መሆኑን አሳየች፡፡ ሞቶም ፈለገችው፡፡ የፈለገችው ተአምር እንዲያደርግላት፣ ከደዌ እንዲፈውሳት፣ አበርክቶ እንዲመግባት አልነበረም፡፡ ስለ ራሱ ስለ ጌታ፣ ስለ ፍቅሩ፣ ስለ ማንነቱ ፈለገችው፡፡ የምታመልከው እርሱን እንጂ ጥቅሟን አልነበረም፡፡ ከጉድለት በላይ ኢየሱስ ክርስቶስን ማጣት ትልቅ ጉዳት ሆኖ ተሰማት፡፡
የክርስቶስ የሆነውን መውደድና ራሱን ክርስቶስን መውደድ የተለያየ እንደሆነ ይህች ሴት ትመሰክራለች፡፡ የዚህች ሴት ፍቅር ፍቅራችንን ይታዘበዋል፡፡ ሁላችንም አምላካችን ገዳይ እንጂ ሟች እንዲሆን አንፈልግም፡፡ ጠላቶቻችንን የሚበቀል፣ በተነሡብን ላይ ፈጥኖ የሚፈርድ እንዲሆን እንፈልጋለን፡፡ እኛን አስከብሮ ራሱን ተፈሪ የሚያደርግ አምላክ እንሻለን፡፡ በድካም የሞተውን ወይም ዝም ያለውን ክርስቶስ እንደዚህች ሴት ለመፈለግ ፍቅራችን ምን ያህል የፀና ይሆን?
  መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ የገሰገሰችው የመጨረሻውን ስንብት ለማድረግ፣ ሀዘኗን ለመግለጥና ቅዱስ ሥጋውን ሽቱ ለመቀባት ነው፡፡ ክርስቶስን በሕይወት አገኘዋለሁ የሚል እምነት አልነበራትም፡፡ ቢሆንም ግን ትፈልገዋለች፡፡ መግደላዊት ማርያም ትንሣኤውን እንዳላመነች፡-
1.     ሽቱ ይዛ መምጣቷ ይገልጣል፡፡ ለሙታን የሚሆን የመሰናበቻ ሽቱ ይዛለችና፡፡
2.    ድንጋዩን ማን ያንከባልልልኛል? የሚል ስጋት ነበረባት፤ ክርስቶስ ከድንጋዩ ውስጥ መሆኑን እርግጠኛ ነች፡፡
3.    ባዶውን መቃብር አይታ እንኳ ለደቀ መዛሙርቱ ጌታዬን ወስደውታል በማለት መሰረቁን እንጂ መነሣቱን አላመነችም፡፡
ዮሐንስ ወንጌሉን ሲጽፍ፡- «እየሮጠችም ወደ ስምዖን ጴጥሮስና ኢየሱስ ይወደው ወደነበረው ወደ ሌላው ደቀ መዝሙር መጥታ፡- ጌታዬን ከመቃብር ወስደውታል ወዴትም እንዳኖሩት አናውቅም አለቻቸው»  (ዮሐ. 2ዐ፣2)፡፡
ወደ ሁለቱ ደቀ መዛሙርት ገሰገሰች፡፡ አንዱ የካደ ሲሆን ሁለተኛው ግን የፀና ነው፡፡ የጌታችን ትንሣኤ ግን የካደውንም የፀናውንም ይማርካል፡፡ የትላንት በደልም የትላንት መጽናትም ለዛሬ አይጠቅምም፡፡ አሁን በትንሣኤ ማመን ግን አዲስ መንገድን ይከፍታል፡፡ በዚህ ገለፃ ውስጥ፡-
1.     ስምዖን ጴጥሮስ፣
2.    ኢየሱስ ይወደው ወደ ነበረው፣
3.    ጌታዬ፣ የሚሉት ንግግሮች ልብ ይነካሉ፡፡
ስምዖን ጴጥሮስ
ስምዖን ጴጥሮስ ከመጠራቱ በፊት ስምዖን ይባል ነበረ፡፡ እንደ ሸምበቆ የሚወዛወዝ የድካም ኑሮ፣ የችኩልነት ሩጫ ያዛለው፣ ራሱን መለወጥ ያቃተውና በራሱ የሚናደድ፣ሽምግልና ማስተዋል ያልሰጠው፣ ብዙ ኖሮ ጥቂት እንኳ ያላወቀ ሰው ነበር፡፡ እንዲህ ያለውን ማንነት እንኳን በሽምግልና በወጣትነትም ያውም ለደቀ መዝሙርነት የሚፈልገውማንም የለም፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ተቀበለው፡፡በማንነቱ አልገፋውም፡፡ የራሱን ማንነት ሊሰጠው ተቀበለው፡፡ በተጠራ ቀን ጴጥሮስ ወይም ዓለት እንደሚባል ነገረው (ዮሐ. 143)፡፡ የጴጥሮስን ኑሮ ስናየው የድካም ጥላ ያጠላበት፣ ከብስሉ ጥሬው የበዛበት ነው፡፡ እስከ ሽምግልና የሚሸከመው፣ እስከ ሕይወት ህቅታ በማንም ተስፋ የማይቆርጠው ጌታ ግን ተቀበለው፡፡ ሸምበቆ ቢሆንም ጴጥሮስ አለው፡፡ የሆነውን ሳይሆን የሚሆነውንአይቶ ጴጥሮስ አለው፡፡ ብዙ የተስፋ መዋዕለ ንዋዩን አፈሰሰበት፡፡
ጴጥሮስ ከመጠራቱ በፊት ስምዖን ይባል ነበር፡፡ ከተጠራ በኋላ ግን ስምዖን ጴጥሮስ እያሉ ፀሐፊያኑ ዘግበውለታል፡፡ የኖረው ኑሮ የፈረቃ ነውና፡፡ ከትንሣኤውበኋላ ግን ጴጥሮስ ብቻ በማለት ጠሩት፡፡ መንፈስ ቅዱስ ኢየሱስ የተመኘለትን ማንነት አጎናጽፎታልና፡፡ እኛስ እንደ ሸንበቆ የምንወዛወዝ ስምዖን ነን? ወይስ በአንድ ምዕራፍ የሚመሰገንና የሚገሰጽ ስምዖን ጴጥሮስ ነን? (ማቴ. 1617.23)፡፡ ጴጥሮስ እንድንሆንየመንፈሱን ኃይል ያድለን፡፡
ኢየሱስ ክርስቶስ ሞቶ የሚቀር መስሎት ጴጥሮስ እንደ ካደው እናውቃለን፡፡ ክርስቶስ መነሣቱን ሲሰማ ከማንም ይልቅ ሐፍረት የሚያንገዳግደው ጴጥሮስን ነው፡፡ ኢየሱስ ክርስቶስ ግን ከሞቱ በፊት በነበረው ፍቅር ጴጥሮስን ይወደው ነበር፡፡ ለዚህ ነው መልአኩ ለመግደላዊትማርያምና ለባልንጀሮቿ፡– «… ተነሥቶአልና በዚህ የለም እነሆ እርሱን ያኖሩበት ስፍራ፡፡ ነገር ግን ሄዳችሁ ለደቀ መዛሙርቱ ለጴጥሮስምወደ ገሊላ ይቀድማችኋል እንደነገራችሁ በዚያ ታዩታላችሁ ብላችሁ ንገሩአቸው» ያለው (ማር. 166-7)፡፡ «ለጴጥሮስም» የሚለው ቃል ልዩ መልእክት አለው፡፡ የክርስቶስን ፍቅር ሞት እንኳ አልለወጠውም፡፡ ሥጋውን እንጂ ፍቅሩን መግደል አልቻሉም፡፡አይሁድ በእርሱ ፈጽሞ ለመጨከንና ልክ ነን የሚል ስሜትን ለመጎናጸፍከእርሱ ክፉ ቃልን ሲጠብቁ በማይሞተው ፍቅሩ፡«አባት ሆይ. የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» በማለት ለመነላቸው፡፡ ከሞት በኋላም መነሣቱን በተለይ ለጴጥሮስ ንገሩልኝ አለ፡፡ ትልልቅ ሸለቆዎች የሚገናኙት በድልድይ ነው፡፡ በእኛ ኃጢአትና በእርሱ ቅድስና መካከል ያለውን ርቀት የራሱ ይቅርታ እንደ ድልድይ ሆኖ ያገናኘናልና ስሙ ቡሩክ ይሁን።፡…..
…….ይቀጥላል…..
ረቡኒ
በዲ/ን አሸናፊ መኰንን
የመጀመሪያ እትም ሚያዝያ 2002 ዓ/ም
አድራሻ – 0911 39 35 21/0911 67 82 51
ፖ.ሳ.ቁ. 62552
አ.አ. ኢትዮጵያ
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ