መግቢያ » ከመጻሕፍት » ረቡኒ » ረቡኒ /ክፍል2

የትምህርቱ ርዕስ | ረቡኒ /ክፍል2

 ምድር ብዙ ነገሮችን ተሸክማለች ፣ የአምላኳን ሞት ግን መታገሥ አልቻለችም ። ትንሣኤውንም መደበቅ አቅቷት ተናውጣለች ። ነገሥታትና ጠቢባን ሁሉ ለሞት ተገዝተዋል ፣ ሞት ግን በትንሣኤ ተሸንፏል ። ሰው ከሞት ላያድን ንግሥናን ለምን ይፈልጋል ? እግዚአብሔር ታላቅ ኃያሉን በትንሣኤ ገልጧል ። በትንሣኤው ያመኑ የብርሃን ልጆች ናቸው ። ከምድር ነገሥታት ፣ ከዓለም ጠቢባን ይበልጣሉ ። መግደላዊት ማርያም ትጓዝ የነበረው ይህን ሁሉ አስባ አልነበረም ። ጌታዋን አልቅሳ ለመጨረሻ ጊዜ ለመሰናበት ነበር ። አልዓዛርን እንዳስነሣ አይታለች ፣ እርሱ እንደሚነሣ ግን አላመነችም ። እኛም ትንሣኤውን አምነናል ፣ በእርሱ ሥልጣን እንደምንነሣ በማመን ኀዘናችንን ገደብ ልንሰጠው ይገባል ። ትንሣኤ ኀዘንን ያቋረጠ ፣ የልቅሶን ጅረት የከፈለ ነው ። ጌታ ግን ወደ ኋላ የሚተርኩት ሳይሆን ዛሬም ለዘላለምም ሕያው ነው ። የሃይማኖት ምሥጢራት በልኩ አልገቡኝም ብለን ከእግዚአብሔር ቤት መራቅ አይገባም ። እግዚአብሔር ንጋትንና እውቀትን በጊዜው ያመጣል ። ባወቅነው መጠን ስንታመን የማናውቀውን ነገር እያወቅን እንመጣለን ። እውቀት ጠል ሁኖ አለመኖር ፣ ገናም ለማወቅ መኖር እርሱ የብርሃን መገኛ ነው ። ወደ እግዚአብሔር ቤት በትንሣኤ እግሮች ይገሠግሣሉ ፣ ቅኔው ዝማሬው ብዙ ምሥጢር ያለው ነው ፤ የሚረዱት ግን ጥቂቶች ናቸው ። ብዙ ብናውቅም የምንባረከው በማመን ነው ።

መናወጦች ሦስት ጊዜ ይሆናሉ ። ጠቢባን ይህ ዓለም የታላቅ ፍንዳታ ውጤት ነው ይላሉ ። ስለ ነውጥ የሚያምኑት በፍጥረት መገኘት ላይ ነው ። እግዚአብሔር ግን በዝምታ ሰማይና ምድርን ፈጠረ ። መናወጥ ግን ሦስት ጊዜ ይሆናል ። ክርስቶስ ሲሞት ፣ ክርስቶስ ሲነሣ ፣ ክርስቶስ ዳግም ሲመጣ ። ክርስቶስ ሲሞትና ሲነሣ ምድር ተናወጠች ። በዳግም ምጽአት ግን ሰማይም ይናወጣል ። በክርስቶስ ሞት መናወጡ የሆነውን መሸከም አለመቻሉ ነው ። ሲነሣ መናወጡ ደግሞ ኃይሉን ማውራቱ ነው ። በዳግም ምጽአት መናወጡ ግን ለአዲሱ ሰማይና ምድር ስፍራ መልቀቁ ነው ። በሕይወታችንም ሦስት መናወጦች ይሆናሉ ። ለዓለም ስንሞትና መስቀሉን ለመሸከም ዝቅ ስንል ቤተሰቦቻችን መናወጥ ይጀምራሉ ። አእምሮውን ቢያጣ ፣ አቅሉን ቢስት ነው ይላሉ ። ለእግዚአብሔር ለመኖር ስንነሣ ዓለም ይናወጣል ። ከሀዲ ነው ፣ ውሸታም ነው ይላል ። አሮጌውን ጥለን አዲሱን ብቻ ስንይዝም ፣ ለዘመናት በውስጣችን የኖረው ድካም ተቀርፎ ሲወድቅ ፣ ወደ ክርስቶስ ድል ስንደርስ በፈታኙ ዓለም መናወጥ ይሆናል ።
መግደላዊት ማርያም በእነዚህ ተአምራት ተስባ የመጣች ሳትሆን በፍቅሩ ተነክታ የመጣች ናት ። ብዙ ተአምራት እነዚያን ሰቃዮች አላሳመናቸውም ።በመጨረሻው ቀን ቅዱስ እንደሚቀደስ ርኩሱም እንደሚረክስ በዕለተ ዓርብም እንደዚያ ነበረ ።
የሮማ ወታደሮችና የካህናት ሎሌዎች ፣ ሮማዊው ጲላጦስና ኤዶማዊው ሄሮድስ ለወትሮ የሚዋደዱ አልነበሩም ። ክርስቶስን በመግደል ግን አንድ ሆኑ ። በጌታችን ሞት ብዙ አስደናቂ ነገሮች ተከናውነዋል ። በሊቀ ካህናቱ የሚመራው የአይሁድ ሸንጎ በቀን የማይገኘው በሌሊት ችሎት አስችሏል ። የሄሮድስን ሥልጣን ለማሳነስ የመጣው ጲላጦስና ግዛቱ የተከፈለበት ሄሮድስ በዚያ ቀን ፍቅር ሆኑ ። ለቄሣር ሞት የሚለምኑ አይሁድ የቄሣር ወዳጅ አይደለህም በማለት ክርስቶስን እንዲሰቅል ጲላጦስን አግባቡት ። በርባን መፈታቱ ፣ የቀኙ ወንበዴ/ፈያታዊ ዘየማን ገነት መግባቱ አስደናቂ ነው ። በልደቱ ካህናት ቀርተው እረኞች ተገኙ ፣ በሞቱም ወንበዴ ገብቶ ሊቃነ ካህናት ሐናና ቀያፋ ተኰነኑ ። የሚጠበቁት ቀርተው የማይጠበቁት ሲገኙ ይህ የወንጌል ጠባዩ ነው ።
መግደላዊት ማርያም ሰንበትን እቤቷ አሳለፈች ፣ ጌታም በመቃብር አሳለፈ ።ሰንበት የእግዚአብሔርን ቀን ለእግዚአብሔር የምንሰጥበት ነው ። የብሉይን ሰንበት አክብራ በማግሥቱ በአዲሱ ሰንበት ክርስቶስን አከበረች ። በሁለቱም ኪዳን የከበረች ሴት ሆነች ። ሚሊኒየም ላይ መገኘት ብዙዎች የሚመኙት ነው ፣ በሺህ ዓመት አንዴ ስለሚመጣ የሚያገኙት ጥቂቶች ናቸው ። ከዚያ በሚበልጥ ሁለቱ ኪዳናት አንዱ አንዱን ሲያከብርና ሲረካከብ መግደላዊት ማርያም ተገኘች ። የመጨረሻውን የብሉይ ኪዳን ፋሲካ አክብራ የዘላለሙን ፋሲካ ማክበር ጀመረች ። በሚቀጥለው ዓመት በእስራኤላዊነት ፋሲካን ብታስበው በክርስቲያንነት ግን አዲሱን ፋሲካ ታከብራለች ። የብሉይ ፋሲካ የሥጋ ነጻነት የአዲሱ ፋሲካ የነፍስ ነጻነት የተገኘበት ነው ።
ቀትር የጨለመው ፣ እኩለ ሌሊት የበራው በክርስቶስ ሞትና ትንሣኤ ነው ። ቀትር ፀሐይ አናት ላይ የምትወጣበት ፣ ሙሉ ቀን ተብሎ የሚጠራበት ፣ የብርሃን ድምቀትና ትኩሳት ያለበት ነው ። እኩለ ሌሊት ሰማዩ አጋም የሚመስልበት ፣ ጥቁር ግምጃ ለብሶ የሚያስጨንቅበት ነው ። ክርስቶስን በታሪካችን ስንሰቅል ሥልጣኔው አለማወቅ ፣ ብርና ወርቁም ዝገት ይሆናሉ ።ሥልጣኔም ገንዘብም እንደማያድን ይህ ዘመን ምስክር ነው ። ስለ ጨረቃ ላይ ሆቴል በሚወራበት ዘመን ገና እጃችሁን ታጠቡ መባል የሚገርም ነው ። ያለ እግዚአብሔር የሚጓዙ ሲከልሱ ይኖራሉ ። የደመቀውን ሥልጣኔ ማንም አያቆመውም ፣ በሰዓታት ዓለም ከዓለም እንጓዛለን ፣ ኢኮኖሚያችን ጣራ ነክቷል ፣ ዓለም አንድ መንደር ሁኗል የሚባለው ሁሉ እንደ ቀትር ይጨልማል ። ያለ ማስተዛዘኛ ሁሉም ነገር ድንገት ያበቃል ። ክርስቶስን ለሚያስሱም እኩለ ሌሊት ብርሃን ይሆናል ። ወደ ኋላ ለመመለስ ጉልበት ፣ ወደፊት ለመሄድ ወኔ ያጡ ፣ ሁሉም ነገር የከዳቸው ፣ አለመኖር የሚሰማቸው ፣ ወልደው መሐን የሆኑ ፣ አፍቅረው ስድብ የተሸከሙ ፣ የእኔ ነገር አብቅቷል ብለው ለራሳቸው የዕድር ጡሩንባ የሚነፉ ፣ የእርሱ ነገር አብቅቷል ተብሎ ሁሉ ተስፋ የቆረጠባቸው ፣ የትላንቱን እምነት አይደለም ወንድነት አጥተው ትጥቃቸው የላላባቸው ፣ የወረደባቸው በረዶ ያደነዘዛቸው ፣ ቢያፈጡ መልሶ ችግራቸው የሚያፈጥባቸው ለእነዚህ ጨለምተኞች የትንሣኤ ብርሃን ይበራላቸዋል ። ይህን ብርሃን የሮማ ክንድ ሊከለክለው አይችልም ። ዓርብ ዕለት የወጡ ወረኞች ቀኑ ጨለመባቸው ፣ እሑድ ዕለት የወጡ ምስክሮች ግን ጨለማው በራላቸው ። ወረኞችን ጨለማ ፣ ምስክሮችን ብርሃን ይከተላቸዋል ።
የመቶ አለቃው ሞቱን አይቶ አመነ ፣ ትንሣኤውን ያዩ ወታደሮች ግን አላመኑም ወይም እንዳመኑ አልተጻፈልንም ። እግዚአብሔርን በዝምታው የሚያከብሩት እንዴት የታደሉ ናቸው ? ለበደላችን ይህም ሲያንስ ነው እያሉ በእሳት ውስጥ የሚዘምሩ ቡሩካን ናቸው ። አድርግልን ሳይሆን ያደረግህልን እንዴት ድንቅ ነው ! የሚሉ አማንያን ናቸው ። ክርስቲያን ገና እንዲደረግለት አይኖርም ። የዘላለም ሕይወት ሆኖለታል ። የሰው ልጆች ልብሱን ሲገፉት ፀሐይ ዕርቃኑን አላሳይም ብላ ጨለመች ። ሰው ሲደፍር ፀሐይ አፈረች ። ዛሬም ሰው ለሰው መርዝ ሲበጠብጥ አትክልት ግን ንጹሕ አየር ይለግሳሉ ። ለመርዙ ማርከሻም ላም ወተት አለኝ ትላለች ። በግፍ የተገደለውን ጌታውን ከመቃብሩ አልለይም በማለት ውሻው ይጠብቀዋል ። ምነው ዛሬ የጌታችን ውሾቹ እንኳ በሆንን ።
ሰው በፍጥረቱ ክቡር ፣ በአኗኗሩ ግን ርካሽ መሆኑን ዕለተ ዓርብ ይናገራል ። ሲወለድ በበረት ከብቶች አውቀውት ሰዎች በር ዘጉበት ። ሲሰቀል ፀሐይ አዝናለት ያዳናቸው ጨከኑበት ። ለሰው የተደረገውን ግዑዛንም ይመሰክራሉ ። ጨካኙ የባቢሎን ንጉሥ ሰዓዳም ሁሴን ፣ የቀሬናው/የሊቢያው ጋዳፊ ሲያዙና ሲንገላቱ ልባችን አዝኗል ። የክፉዎች ሞት እንኳ ካሳዘነ የመድኃኔ ዓለም ሞት እንዴት ያሳዝናል ። መላእክት እስከ ዛሬ አመስግነው በማያውቁት አዲስ ቅኔ አመሰገኑ፡- የታረደው በግ ኃይልና ባለ ጠግነት ጥበብም ብርታትም ክብርም ምስጋናም በረከትም ሊቀበል ይገባዋል አሉ።” /ራእ. 5፡12 ።/ ትንሣኤ አዲስ ዝማሬን በሰማይ ያመጣ ነው ። ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን “ክርስቶስ ተነሣ” ብላ ማወጇ ተገቢና ከሰማይ የወረሰችው ነው ።

የማትችለው መግደላዊት ማርያምና መግደል የሚችሉት መላእክት ከጌታቸው ትዕግሥት ጋር ተባበሩ ። ጌታው የቻለውን ሎሌው አይቆጣውምና ። እግዚአብሔር ሎሌዎቹን ያከብራል ። ነቢዩ ኤልያስ ለእግዚአብሔር ቀንቶ ሰማይን ለጎመ ፣ ምድርን ገዘተ ። እግዚአብሔርም ከአሳቡ ጋር ተስማማ ። ያ ሕዝብ ግን አልመለስም ባለ ጊዜ እየራበው ከሚክደኝ እየበላ ይካደኝ ብሎ ኤልያስን ተገለጥላቸው አለው ። ቅዱስ ገብርኤልም ዘካርያስን ዱዳ ቢያደርግ እግዚአብሔር ተስማማ ። በሞቱ ግን መላእክትን ገረመመ ፣ እንዲታገሡም አስጠነቀቀ ። ልደቱና ሞቱ ይመሳሰላሉ ። የተወለደው ሊሞት ነውና ። በልደቱ ድንግልን እንዳያስደነግጥ መልአኩ ገብርኤል ታዘዘ ወይም በትዕግሥት አናገራት ። በሞቱ ዕለትም ገዳዮችን እንዳያጠፉ መላእክት ቅንዓታቸውን አብርዱ ተባሉ ። ልደቱና ትንሣኤውም ተመሳሳይ ናቸው ። በሁለቱም መላእክት ነበሩ ። በሁለቱም በዝግ በር ወጥቷል ። በሕቱም ድንግልና የተወለደ ፣ በሕቱም መቃብር ተነሣ ። ላብ ከሰውነት ሲወጣ ቆዳን እንደማይቀድ ፣ ብርሃን በመስተዋት ሲያልፍ መስተዋት እንደማይሰበር የአምላክ ልጅም ከድንግል ሲወለድ ማኅተመ ድንግልናዋን አልለወጠም ። በዝግ መቃብርም ሲወጣ የሮማውያንን ማኅተም አልቀደደም ።
መግደላዊት ማርያም በትንሣኤ ቀን “ረቡኒ” አለችው ። አዳኜ የሚለው ምስጋና ይገባው ነበረ ። እመቤታችን ግን በብሥራቱ ቀን፡- ነፍሴ ጌታን ታከብረዋለች ፥ መንፈሴም በአምላኬ በመድኃኒቴ ሐሴት ታደርጋለች አለች ። ሉቃ. 1፡47 ። ልደትና ትንሣኤ ፣ ትንሣኤና ምጽአት ሲናበቡ ይኖራሉ ።
አቤቱ የትንሣኤህን ብርሃን በልባችን አብራ ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8ለ
ሚያዝያ 21 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ