የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረቡኒ/6

 ጌታችን የሴቶችን ሽቱ በሁለት ምክንያት አይቀባም ። የመጀመሪያው እርሱ ሕያው ነውና ለሙታን የተዘጋጀ ሽቱ አይቀባም ። መላእክትም “ሕያውን ከሙታን መካከል ስለ ምን ትፈልጋላችሁ?” ብለዋል ። በእውነት ሕያው ጌታን ሙት ከሆነው ዓለምና ኃጢአት መካከል አንፈልግም ። ከደጎች እንደ አንዱ ፣ ከቅዱሶችም እንደ አንዱ አይደለም ። እርሱ ልዩ ነው ። ጌታችን የሴቶችን ሽቱ ያልተቀባበት ሁለተኛው ምክንያት በትንሣኤ አካል እንደ ማርታ እንጀራ ቢያዘጋጁለት የሚበላ ፣ እንደ መግደላዊት ማርያም ሽቱ ቢያመጡለት የሚቀባ አይደለም ። በትንሣኤ አካል የሚቀባው የምስጋናን ሽቱ ነው ፤ ለስሙ ዕጣን ከፀሐይ መውጫ እስከ መግቢያው ይታጠንለታል ። አሁን ለእርሱ ሽቱ ከማምጣት በፊት ሽቱ ሁኖ መቅረብ ይገባል ። ጌታችን የተናገረው ስለ ሞቱ ብቻ ሳይሆን ስለ ትንሣኤውም ነው ። ሰዎች ትንሣኤ ቀድሞ ሞት ቢከተል ማዘናቸው ፣ ሞት ቀድሞ ትንሣኤ ቢሆን መጠራጠራቸው አይቀርም ። ዓለም እርግጠኛ ኀዘንና አጠራጣሪ ደስታ አላት ። እገሌ ወደቀ ሲባል ሁሉም ያምናል ፣ ተነሣ ሲባል ግን ላስብበት ይባላል ። ሞትን የሚቀበል አእምሮ ትንሣኤን አይቀበልም ። የሚያመነታ ማንነት ባሕር ዳር እንዳለ አሸዋ ሲወዛወዝ የሚኖር ነው  ። መወዝወዙ በቀንና በሌሊት በመሆኑ ዕረፍት የለውም ።

ጌታችን እነሣለሁ ያለውን ቢያምኑ ኑሮ ብዙ ነገሮች ይወገዱ ነበር፡- ወደ መቃብሩ ከመገስገስ እቤታቸው ሁነው ይጠብቁት ነበር  ። በጨለማና በቋጥኝ ስጋት አይያዙም ነበር ። ሊጥሉት ሽቱ በመግዛት ገንዘብ አያባክኑም ነበር ። የእግዚአብሔርን ተስፋ አለማመን ዕረፍትን ያሳጣል ፣ ከንቱ ዋጋ መክፈልን ያመጣል ፣ ገንዘብን ያባክናል ። በተስፋውና በፍጻሜው መካከል ብዙ ነውጥ አለ ። እስራኤል 430 ዓመት በባርነት ኑረው አርባ ዓመት ግን በምድረ በዳ መታገሥ አቃታቸው ። ተስፋ ከተነገረ በኋላም መቅበጥበጥ ይኖራል ። መድኃኒቱ፡- “እኔ እግዚአብሔርን አልቀድመውም” ብሎ መታገሥ ብቻ ነው ። እግዚአብሔር ተስፋን የሚሰጠን ፡- ከመቅበዝበዝ ሊያድነን ፣ ባዶ ነገር ፍለጋ እንዳንሮጥና የሌለ ነገርን አለ ብለን እንዳንሰጋ ፣ ገንዘባችንም እንዳይባክን ነው ። በዚያ ሌሊት በአሳብ ተናጡ ። ቅዱስ ሥጋውን ላያገኙ ወደ ባዶ መቃብር ገሰገሱ ። ድካሙ ተጨባጭ ነው ፣ ውጤቱ ግን እንዳሰቡት አይደለም ። የሌለ ነገርን እንዳለ አሰቡ ። ነገር ግን ቋጥኙም ወታደሮቹም የሉም ። ስንደርስ ባዶ በሆኑ ነገሮች ፣ አሉ ብለናቸው በሌሉ ስጋቶች ፣ ገንዘባችንን በጨረስንባቸው ነገሮች ተጠያቂው አለማመናችን ነው ።
ሴቶች በኩሽና የተቆለፈባቸው ፣ የሠሩትን ምግብ እንኳ በሳሎን ለመመገብ ያልተፈቀደላቸው ፣ እንደሚናገር እንስሳ በሚታዩበት በዚያ ዘመን ሰማይና ምድር የሚጠብቁትን ትንሣኤ ለማየትና ለመመስከር በቁ ። በጣም በሰው መናቅ እንዴት መልካም ነው ! የምንከብረው በናቁን መጠን ነው ። ሰዎች ገፍተው የሚያደርሱን እግዚአብሔር ጋ ነው ። ዳዊት ቢንቁት ንጉሥ ሆነ ። እግዚአብሔር ውጭውን አያይም ፣ ዙሪያውንም አያማትርም ፣ የሚመርጠው በልባችን መሠረት ነው ። መናቅ ሰዎች ከፍ የምንልበትን ደረጃ መሥራታቸው ነው ። ከሰው ንቀት ከእግዚአብሔር ክብረት አይጠፋም ። ያከበርነው ሲያሳፍረን ፣ የናቅነው ግን ዝም ያሰኘናል ። ብርታታችንን የሚያበረቱ ፣ እሳትን የሚያቀጣጥሉ የሚንቁን ሰዎች ናቸው ። ባይንቁን ኑሮ የማንደርስባቸው ብዙ ከፍታዎች ነበሩ ። እግዚአብሔር ሆይ ስለ ናቁን ሰዎች ፣ ገፍተው አናት ላይ ስላወጡን ወገኖች ተመስገን ።
መግደላዊት ማርያም ከሌሎች ቅዱሳን ሴቶች ጋር ወደ መቃብሩ ብትጓዝም እርምጃቸው አላረካትም ። ልቧ ደርሶ ስለ ነበር እግሯ አልፈጥን አላት ። በብስጭትም ሩጫ ጀመረች ። ወደ መቃብሩ ቀድማ ደርሳ መቃብሩ ባዶ መሆኑን ስታይ ወደ ጴጥሮስና ወደ ዮሐንስ እንደገና ሮጠች ። ያደረሰችው ወሬ ጌታን ወስደውታል የሚል ኀዘን ነው ። አለማወቅ ደስታን ኀዘን ፣ እልልታን ልቅሶ አድርጎ ይውላል ። በምርኮው ቀን ጌታን ወስደውታል ብላ አዘነች ።
መግደላዊት ማርያም ሁሉም ጥለዋት ሄዱ ፣ እርስዋም ብቻዋን በመቃብሩ ስፍራ ቀረች ። ጌታን ያኖሩበትን ስፍራ ካላወቅሁ አልመለስም አለች ። መቃብሩን ማዶ ማዶ እያየች ታለቅስ ነበር ። የምታለቅሰው ለሞቱ ሳይሆን ለአሟሟቱ ፣ ጠላቶቹ ሞቶም ላልተኙለት ወዳጅዋ ነው ። እንደ ሞኝ ጠብ ጠባቸው ማለቂያ አጣ ። ዛሬም ገፍተውም ፣ አውግዘውም ፣ ሰድበውም ፣ ይሙት በቃ ፈርደውም የማያርፉ አሉ ። በሥራቸው ከማልቀስ ለሥራቸው ማልቀስ ዕረፍት ለማጣታቸው መንሰቅሰቅ ይገባል ።
ከእኛ በላይ ኃያል የለም ያሉት ሮማውያን ፣ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉት ሰዱቃውያን ፣ ገደልነው ያሉት ፈሪሳውያን ፣ “አገር ከምትሞት ግለሰብ ይሙት” ያሉት ፀሐፍትና ዳኞች ፣ የራሳቸው ጠብ የሌላቸው አዳማቂዎች የክርስቶስ ትንሣኤ አሳፈራቸው ። ከሐፍረት ፍርሃት ይሻላል ። ፍርሃት መናጥ ነው ፣ ሐፍረት ግን በፈቃድ ልነቀል ማለት ነው ። ሰው የሚፈራው ራሱንና ሰዎችን ነው ። የሚያፍረው ግን ሰማይና ምድርን ነው ። ሰዎችን እያማናቸው ሲደርሱብን ፣ ስማቸው እገሌ ነው እያልን ስማቸው ሌላ ሲሆንብን ፣ ይጥፉ ብለን በላያች ሲሾሙብን ፣ ገደልን ብለን ሕያው ሲሆኑብን ፣ እናጥፋቸው ስንል ይበልጥ ሲበሩብን እናፍራለን ። ሐፍረት ሲኦልን በምድር መለማመጃ ነው ። ክርስቶስ ከሐፍረትን ሊያድነን ከሞት ተነሣ ። በሰማይ ታላቅ ዝማሬ በምድር ታላቅ ኀዘን ነበረ ። በሰማይ እውነቱ ፣ በምድር ስሜቱ አይሎ የተለያየ ድምፅ ተሰማ ። ከሰማያውያን ጋር አንድ ለመሆን ጌታ የተናገረውን መስማት በቂ ነው ። ሰማይና ምድረን አንድ የሚያደርግ የእርሱ ቃል ነው ። ሰማይ ተነሥቷል ይላል ፣ ምድር ተሰርቋል ይላል ። ሁሉም ነገር ከሰማይና ከምድር ሲያዩት ትርጉሙ ልዩ ነው ። ጌታችን የተነሣው ባዶ መቃብርና ምሉዕ ሕይወትን ለመስጠት ነው ።
የካህናት አለቆች የፈጠሩትን ውሸት አምነውታል ፣ “ውሸቴን እንዳላምነውና የአዞ እንባ እንዳላነባበት ጠብቀኝ” ማለት ትልቅ ጸሎት ነው ። የውሸት ክፋቱ ሲቆይ ባለቤቱንም ያሳምነዋል ። ውሸት ካፒቴኗ ሰይጣን ነው ። በአቡሀ ለሐሰት ነውና ። እነ መግደላዊት ማርያምም ወስደውታል የሚለው ስሜት ተቆጣጥሯዋል ። ሰው ልቡን የሚያምነውን ያህል ቃሉን አያምንም ። ሰይጣን ለአንዳንዶች በልባቸው ጥርጣሬን ፣ ለሌሎችም በጆሮአቸው ውሸት ይዘራል ። ማሳደጉ ግን የሰው ድርሻ ነው ።
በዚያች ሰዓት ያለው ልቅሶ ግምትን ማመን የወለደው ነው ። በግምት ስንት ትዳር ፈረሰ ፣ ስንት ወዳጅነት ሜዳ ቀረ ፣ የለፋንበትን ሳንለፋ በተንነው ። ጌታችን በሰማይ ያለውን ምስጋና እየሰማ በምድር ያሉ ወገኖቹን እንባ ያብስ ነበር ። ሰዎች ጠፍቷል እያሉ ያለቅሱልናል ፣ እኛ ደግሞ የጠፉት ፈላጊ የሆነው ጌታ ጋ ነን ። የሚለቀስላቸው ባለማወቅ ያለቅሱልናል ። ለማን እንደሚለቀስ አለማወቅ ከባድ ነው ። በደስታ ቀን ማዘን ፣ በእልልታ ቀን ማምረር በእውነት አለማመን ነው ።
ብዙ ጊዜ የሚሰሙ ክርክሮች አንድ ቀን ልባችንን እንደገዙት እናውቃለን ። አለመስማት በሚመስሉ መስማቶች እንደ ተሸረሸርን እናውቃለን ። በፈሪሳውያንና በሰዱቃውያን መካከል ትንሣኤ ሙታንን በሚመለከት ክርክር ነበር ። ማንበብና መጻፍ የማይችለው ሕዝብ ያልተጨበጡ ረቂቅ ነገሮችን አናምንም በሚለው በሰዱቃውያን ሳይንሳዊ ጉዞ ተስቦ ነበር ። ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉት የመቅደሱን ሥልጣን የያዙት ሊቃነ ካህናት ናቸው ። ፈሪሳውያን የሚባሉት ቡድኖች ዘርዐ ክህነት የሌላቸው ቀናዒነታቸው ያሰባሰባቸው እሳቶች ናቸው ። የመቅደሱ ሥልጣን ዘመናውያንና ቁሳውያን በሆኑት በሰዱቃውያን እጅ ነው ። መስመሩን ጠብቀው ስለ መጡ ሥልጣኑን በዘር ሐረግ ያገኙታል ። እምነት ግን የላቸውም ። መቅደሱ መሥሪያ ቤታቸው እንጂ አምልኮት መፈጸሚያቸው አይደለም ። ስለ ረቂቅ ነገርና ስለ ትንሣኤ አያምኑም ። ገንዘብ ሲባል ግን ንቁ ናቸው ። ፈሪሳውያን ደግሞ ድህነትን እንደ ጽድቅ የሚያዩ በድብቅ ግን ገንዘብ የሚያከማቹ ፣ ቀናዒ ነን በማለት እንቢ ለአገሬ ፣ እንቢ ለሃይማኖቴ በማለት የዋሁን ሕዝብ ልቡን የሰለቡ ናቸው ። አመለካከታቸው ጥልቅ የነገረ መለኮት እሳቢ ስለሌለው ለብዙኃኑ ተስማሚ ናቸው ። የላኛው አካል ከሀዲ ፣ የታችኛው ደግሞ የሃይማኖት እውቀት የሌለው ወገኛ ቡድን ነበር ። ሕዝቡ በእነዚህ ሁለት ቡድኖች ተውጦ እግዚአብሔርን ማየት አልቻለም ። ደቀ መዛሙርቱ  ትንሣኤ ሙታን የለም በሚለው ከሀዲዎች ንግግር አእምሮአቸው ተሞልቶ እነሣለሁ ያለውን ለማመን ፣ በባዶ መቃብር ፊት ለፊት ለመዘመር ለጊዜው አልታደሉም ። ዛሬ ትንሣኤ ሙታን የለም የሚሉ አስተማሪዎች በመካከላችን አሉ ። አዲስ መገለጥ ሳይሆን ሰዱቃዊ እንደሆኑ ዘንግተዋል ። እንኳን አዲስ እውቀት ፣ አዲስ ኑፋቄም የለም ።
ጌታችን ትልቁን ትንሣኤ ያምኑ ዘንድ ከሳምንት በፊት አልዓዛርን ከሞት በማሥነሣት አለማምዶአቸዋል ። እርሱ የሰውን አቅም ያውቀዋልና ቀድሞ ያዘጋጃል ። ከሁሉ በላይ እነሣለሁ ባለው ቃሉ ሊያምኑት ይገባል ። እግዚአብሔር የእሳት ላንቃ ነው ፣ መያዣ የለውም ፤ የሚያዘው በቃሉ ነው ።
መግደላዊት ማርያም ወደ መቃብሩ እያየች ስታለቅስ በመቃብሩ ራስጌና ግርጌ ሁለት መላእክት ታዩአት ። መላእክቱ የተገለጡት በጎበዝ አርአያ ነው ። እግዚአብሔር ኃያል ነው ማለታቸው ነው ። ነጭ ልብስ ለብሰዋል ። ጽድቅ አሸነፈ ፣ ደስታ ተበሠረ ማለታቸው ነው ። “አንቺ ሴት ስለምን ታለቅሻለሽ?” አሏት ። ለምን እንደምታለቅስ ያውቃሉ ። ችግሯን በገዛ አንደበቷ ስትናገረው ይቀላታልና ጠየቁአት ። የዚች ሴት ልቅሶ ጓደኞቼ አግብተው እኔ ብቻ ቀረሁ የሚል አይደለም ። ሳልወልድ ጊዜ ተላለፈኝ ብላም አይደለም ። ልቅሶዋ “ጌታዬን ወስደውታል” የሚል ነው ። መግደላዊት ማርያም ሁሉም ጥለዋት ቢሄዱ ጨክና ተቀመጠች ። ሃይማኖት ግራና ቀኙን ሳያዩ እግዚአብሔርን ብቻ መከተል ነው ። መግደላዊት ማርያም ምላሽዋ ወስደውታል የሚል ነው ። መግደላዊት ማርያም ሌላ መቃብር ላይ ቀብረውታል የሚል አሳብ ገብቷታል ። ስለ ሁለት መቃብር ታስባለች ። አንዱም እንደ ፈረሰ ረስታለች ። ብቻ “ጌታዬን ወስደውታል” አለች ። ሞቶም ጌታዋ ነው ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8  ረ
ሚያዝያ 26 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ