ሰይጣን ጌታችንን ከዓርብ እስከ እሑድ ገደልሁት በማለት ታላቅ ደስታ ተሰማው ። የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ወደጆችም እህል ውኃ አንቀምስም ብለው ያለ ሆቴል የመገባቸውን ፣ ያለ ሆስፒታል የፈወሳቸውን ፣ ያለ መስፈርት የወደዳቸውን ጌታ እያሰቡ አዘኑ ። ዓርብ የሁሉ ደስታ አልነበረችም ፣ እሑድም የሁሉ ደስታ አትሆንም ። የዓርብ ሰርገኞች የእሑድ ለቀስተኞች ሆኑ ፣ የዓርብ ኀዘነተኞች የእሑድ ሰርገኞች ሆኑ ። እግዚአብሔር ጊዜን እየለዋወጠ ይፈርዳል ። ሰቃዮቹን አልቀጣቸውም የገዛ ሥራቸው ግን እንቅልፍ እየነሣ ቀጣቸው ። ሁልጊዜ ሰጪ ሁልጊዜም ተቀባይ ፣ ሁልጊዜ ተገፊ ሁልጊዜም ገፊ የለም ። እግዚአብሔር ምስኪኖችን ያንገዳገደውን ጽዋ ተቀብሎ ለትዕቢተኞች ይሰጣቸዋል ። የትዕቢተኞች ካባም ለትሑታን ይሆናል ። ሰንበት አክባሪዎች የሰንበትን ጌታ ሰቀሉት ። እነርሱን ባይገድሉት ትንሣኤ የሚል ቃል አይኖርም ነበር ። ጠላት እንደ ጳውሎስ ባያገለግልም እንደ ፈርዖን እግዚአብሔርን ያገለግላል ። /ዘጸ. 9፡16/ የሚቀብር ባይኖር የሚነሣ አይኖርም ነበር ። ምቀኛ ጎረቤት ባይኖርም ሰው ዕቃ አይገዛም ነበር ። ክፉ አከራይ ባይገጥመውም ሰው ቤት አይሠራም ነበር ። ገዳዮች መግደል ቢችሉ እግዚአብሔር ማስነሣት ይችላል ። እግዚአብሔር ካሥነሣም ከገዳይ ጋር ሒሳብ መተሳሰብ ከንቱ ነው ። ማታ ልቅሶ ይሆናል ፣ ጥዋት ግን ደስታ ይሆናል ። በእንባ የሚዘሩ በደስታ ይለቅማሉ ።
አዳም በገነት ጫካ በወደቀ ጊዜ እግዚአብሔር እባቡን ፈረደበት ። የሳቱ ሳይፈረድባቸው አሳቹ ተፈረደበት ። ማሳት ትልቅ በደል ነውና ። እግዚአብሔር ሰው ሁኖ አዳምን እንደሚያድነው የተስፋውን ቃል ለእባቡ ነገረው ። ለእባቡ ግን የመርዶ ቃል ነበረ ። አዳምና ሔዋንን በመጣሉ ፈጽሞ ደስ እንዳይለው ደስታውን አቋረጠው ። አዳምና ሔዋንም በመውደቃቸው ጨርሶ እንዳያዝኑ ኀዘናቸውን ገደበው ። እግዚአብሔር ጠላትን በሁለት መንገድ ይዋጋዋል ። የመጀመሪያ ደስታውን ወዲያው በመንጠቅ ሲሆን ሁለተኛው የቤት ሥራ ሰጥቶ ጊዜ በመንሣት ነው ። እንዲሁም የክርስቶስ ወዳጆች በሞቱ ፈጽመው እንዳያዝኑ ፣ ገዳዮችም በመግደላቸው ጨርሶ ደስ እንዳይላቸው ትንሣኤ ቦታ አለዋወጣቸው ። በትንሣኤ የማይጠፋ ተስፋ ተገኘ ። /1ጴጥ. 1፡3/
አቤል ደሙ “ውረድ ፍረድ” እያለ እስከ ሰብአ ትካት ዘመን ፣ እስከ ማየ አይኅ ጥፋት ይጮህ ነበር ። መሐርኩ ሠረይኩ እያለ የሚጮህ የክርስቶስ ደም ዕረፍት ይሰጣል ። ገዳዩን የሚምር የክርስቶስ ደም ክብር ይገባዋል ። በትንሣኤው ተናጋሪ መሥዋዕት ለሆነው ለደጉ ኢየሱስ ምስጋና ይገባል ። ይስሐቅ በሕሊና አብርሃም ከተሠዋ በኋላ በሦስተኛው ቀን ሕያው ሆነ ። ክርስቶስም በሦስተኛው ቀን ከሞት ተነሣ ። ይህች ቀንም የእግዚአብሔር ቀን ናት ብሎ አብርሃም አያት ። ትንሣኤም የእግዚአብሔር ዓመት ፣ ዓመተ ምሕረት የታወጀበት ነው ። ዮሴፍ በይሁዳ አሳብ አቅራቢነት በወንድሞቹ በሃያ ብር ለአሕዛብ ተሸጠ ። ክርስቶስም በይሁዳ መሪነት በሠላሳ ብር ተሸጠ ፣ ለሮማውያን ተላልፎ ተሰጠ ። ዮሴፍ በአባቱ የተወደደ ነበር ፣ ክርስቶስ “የምወደው ልጄ ይህ ነው” ተብሎ በእግዚአብሔር አብ የተመሰከረለት ነው ። ዮሴፍ ሕልም ነበረው ፣ ክርስቶስም እኛን የማዳን ናፍቆት ነበረው ። ዮሴፍ ወንድሞቹ ኋላ እንደሚሰግዱለት ራእይ አየ ፣ ክርስቶስም የወጉት ሁሉ ዋይ ዋይ ይሉለታል ፣ የእግሩም መጫሚያ ሁነው ጠላቶቹ ይገዙለታል ። ዮሴፍ በከነዓን ሞተ ተብሎ ሲለቅስ በግብጽ ግን አለ ተብሎ ይወደሳል ። ክርስቶስም በሥጋ ሞቶ በነፍሱ የታሰሩትን ሲፈታ በሰማይ ታላቅ ደስታ ሆኗል ። ዮሴፍ ኃጢአትን እንቢ በማለት እንደ ኃጢአተኛ ታሠረ ፣ ክርስቶስም ዓመፅን አልተባበርም ብሎ እንደ ወንበዴ ተሰቀለ ። በዓመፅ ሳይሆን ስለ ሰው ዓመፅ ለሞተው ጌታ ውዳሴ ይገባል ። ዮሴፍ በከነዓን ሞቶ በግብጽ እንደ ተነሣ ፣ ኢየሱስም በቀራንዮ ሞቶ በጎልጎታ ተነሣ ። ዮሴፍ በተነሣ ጊዜ በእግዚአብሔር ክብር ሁኖ ወንድሞቹን ይቅር እንዳለና እንደ ባረከ ክርስቶስም ከሞት ከተነሣ በኋላ የካደውን ጴጥሮስ ፈለገ ፣ ደቀ መዛሙርቱንም እንደ ገና ሰበሰበ ። ዮሴፍ ማለት ይጨምር ማለት ነው ፤ አማኑኤልም፡- “ምርኮ ፈጠነ ፥ ብዝበዛ ቸኰለ” የተባለለት ነው ። /ኢሳ. 8፡1 /። መግደላዊት ማርያም በተስፋ ፣ በምሳሌ ፣ በትንቢት የተበሠረውን የክርስቶስን ትንሣኤ እያየች መሆኗን አላስተዋለችም ። ይህ ቀን አብርሃም ያየው የእግዚአብሔር ቀን ፣ ኢሳይያስ “የተወደደ ዓመት” ያለው ፣ እኛም ዓመተ ምሕረት ብለን የምንጠራው ነው ። /ዮሐ. 8 ፡ 56 ፤ ሉቃ. 4 ፡ 17-19 ።/
ሰይጣን የጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱስ ሥጋ ወደ መቃብር ሲወርድ መግደል ችያለሁ አሁን ደግሞ ሥጋውን በሙስና በመቃብር አጠፋለሁ ብሎ አሰበ ። ጌታችን ግን ትንሣኤን በማብሠር የመቃብር ብቻ ሳይሆን የምድር ግዛቱ ፣ የሰው ልጅ የለቀቀለት አስተዳደሩ ሁሉ ተነጠቀ ። ነፍሱን በሲኦል አስቀራለሁ ብሎ ነበረ ፣ ጠላት ልኩን አያውቅምና ። ጌታችን ግን ሲኦልን በዝብዞ ዲያብሎስ የራሱን የዋይታ ድምፅ ብቻ እንዲሰማ አድርጎ ባዶ አደረገበት ። አተርፋለሁ ብሎ ጎደለበት ። የሲኦልም አፍ ተዘጋ ። ከዚህ በኋላ ወዶ የሚወርድ እንጂ የአባት ዕዳ መጥቶበት ወደ ሲኦል የሚሄድ የለም ። እባቡ በዕለተ ዓርብ የሴቲቱን ዘር ፣ በድንግልና የተወለደውን ክርስቶስን ሰኰናውን ነከሰ ። እሑድ ዕለት የእባቡ ራስ በትንሣኤ ተቀጠቀጠ ። /ዘፍ. 3፡15 /። ሰይጣን ተስፋ የለሽ ጠላት ሆነ ። ግን የተቀጠቀጠ እንጂ የሞተ ጠላት አይደለምና ክርስቲያን ሆይ አትዘናጋ ። መግደላዊት ማርያም ሰማያዊና ምድራዊ ፍልሚያ የነበረበትን ትንሣኤ እንደ ቀላል አድርጋ ተመልክታለች ። እኛም የሆነልንን ነቢያትና ሐዋርያት ፣ ቅዱሳን መላእክት የሚያውቁትን ያህል ገና አልገባንም ። በዋጋው ብንይዘው ክርስትና ክብራችን ነው ። በዚያኛው ዓለም ያለውን ኩነት በዚህኛው ዓይን ብናየው ለመኖር አቅም እናጣ ነበር ። የመንግሥተ ሰማያት ደስታም በጨረፍታ ቢታይ ሰው ሁሉ ያለ ቀኑ ራሱን እየሠዋ ልሂድ ይል ነበር ። ራስን መሠዋት በሥልጣነ እግዚአብሔር መግባትና ትልቅ ክህደት ፣ ከመንግሥተ ሰማያት የሚያስቀር ቀቢፀ ተስፋ ቢሆንም ናፍቆቱ ግን ኵነኔን ያስረሳ ነበር ። አካል በሌለበት ጥላ አይታይም ፣ መንግሥተ ሰማያት ባትኖርም የአማንያን ደስታ አይኖርም ነበር ።
ክርስቶስ ሳይመጣ ትእዛዛቱን የገደሉ ፣ አምላካዊ መመሪያዎችን በሰው ሠራሽ ወግ የተኩ አሁን ደግሞ የትእዛዙን ባለቤት ሰቀሉ ። ኃጢአት በንስሐ ገደብ ካልተሰጠው ሲኦል እስኪያደርስ አይቆምም ። የካህናት አለቆች ልብሳቸው የእግዚአብሔር ፣ ልባቸው የሰይጣን ነበረ ። ልቡ የከዳ በልብሱ ሊያምን አይችልም ። እነዚህ የካህናት አለቆች የመጽደቅ ፍላጎትም የላቸውም ፣ ነገር ግን ታጅበው ወደ ሲኦል ለመውረድ ሕዝቡን በሥጋም በነፍስም ተቆራኝተውት ነበር ። ትንሣኤ ያሳሰባቸውም ሕዝቡ በክርስቶስ ያምናል ብለው ስለ ሰጉ ነው ። አንድ አምላክን ትተው ብዙ ሕዝብን ያመልኩ ነበር ። የሕዝቡም የነፍሱ ሳይሆን የኪሱ ወዳጅ ነበሩ ።
ሞትን ድል የነሣው ክርስቶስ ቢያጠፋንስ ብለው አልሰጉም ። ሕዝቡ እኛን ትቶ ቢጠፋስ የሚል ስጋት ነበራቸው ። “ልትጠፋ ያለች ከተማ ነጋሪት ቢጎስሙባት አትሰማም” ይባላል ። ገዥው ጲላጦስን ዝም ቢያሰኙ ፣ ወታደሮቹን በጉቦ ቢደልሉም ከሃምሳ ቀን በኋላ የትንሣኤው ምስክሮች ምድርን ሞሉት ። ወንጌል ሲያፍኑት ይብሳል ። በክርስቶስ ያደረጉትን በደቀ መዛሙርቱ ቀጠሉ ። እውነት በተገፋች ቍጥር ተራራ ታህላለች ። ጴጥሮስ ምሎ የካደው ክርስቶስ ፣ “ያህዌ ያጥፋኝ” አላውቀውም ያለው ኢየሱስ ፣ ካህናት በውሸት ከስሰነው እንደሆነ “ደሙ በእኛና በልጆቻችን ላይ ይሁን” ብለው ራሳቸውን የረገሙበት አማኑኤል ተነሣ ። የካህናት አለቆች በራሳቸው ላይ የማያልቅ የቤት ሥራ አመጡ ። ክርስቶስ በአዳኝነቱ ካላሳረፋቸው በጥያቄነቱ ሲሞግታቸው ይኖራል ። ከሰቀሉት በኋላ ለምን አያርፉም ? ዕረፍትን ሰቅሎ ዕረፍት የለም ።
ወይ ዓለም መውደድ መሞኘት ፣
ጌታን ረስቶ ጌትነት ።
በትንሣኤህ ኃይል አስበን ።
ይቀጥላል
የመስቀሉ ገጽ 8 መ
ሚያዝያ 23 ቀን 2012 ዓ.ም .
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን