የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ረዳታችን

“አምላካችን መጠጊያችንና ኃይላችን ፥ ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው።” (መዝ. 45፡1።)

“እርዱኝ እረዳችኋለሁ” ይላል መጽሐፉ የሚሉ ሰዎች አሉ ። እንዲህ የሚል መጽሐፍ የለም ። ያልተጻፈውን የሚያነቡ ሰዎች የተጻፈውን ለማንበብ ደካማ መሆናቸው ያሳዝናል ። እግዚአብሔር ከሰው ጸሎትን ሲፈልግ ፣ እርሱ ደግሞ በመለኮታዊ ኃይሉ ያደርገዋል ። ሰው የሚሻው ነገር በእግዚአብሔር ቸርነት ይፈጸማል ። ምክንያቱም እግዚአብሔር ለእኛ የሚያስፈልገውን ከምንሻው በላይ ስላዘጋጀልን ነው ። ስለዚህ ጸሎታችን ገና ለእኛ እንዲያስብና እንዲፈጥር አያደርገውም ። ያሰበልንን በጸሎት እንቀበላለን ። እርሱ ለዘላለማዊ ሕይወታችን አስቦአል ። ከዘላለም ሕይወት የበለጠ የምንለምነው ክቡር ነገር ፈጽሞ የለም ። ፈቃድህ ይሁን ብለን መለመናችን እግዚአብሔርን ለማራራት ሳይሆን ጸሎት የሚፈጸመው በእርሱ ሉዓላዊ ሥልጣን ነውና መንግሥትነቱን እንድናምን ነው ። እርሱ እግዚአብሔር ከሰው ፈቃድ ይፈልጋል ፣ ለመፈጸም ችሎታው የተደነቀ ነው ። ፈቃዳችሁን ከሰጣችሁኝ ኃይሌን እሰጣችኋለሁ የሚል አምላክ ነው ።

እሺ የምንለው ፣ የምንሮጠው ፣ የምንዘራው ፣ የምንሠራው እግዚአብሔርን ለመርዳት አይደለም ። እርሱ የማያግዙት ኃያል ፣ የማያበድሩት ባለጠጋ ነው ። ስለዚህ እርዱኝ እረዳችኋለሁ አላለም ። እግዚአብሔርን በምክር ያገዘው ፣ በአቅም የረዳው ማንም የለም ። ለመላእክት ምጡቅ አሳብን የሰጠ ፣ ኃይልንም ያፈሰሰላቸው እርሱ ነው ። ሠራዊተ መላእክት አይጠብቁትም ፣ ይጠብቃቸዋል እንጂ ። ኪሩቤልም ንግሥናውን ለመግለጥ ዙፋን ተሸካሚ ቢባሉም የተሸከማቸው እርሱ ነው ። በሰማያት የምትኖር ስንል በምድር የለም ማለታችን እንዳልሆነ ሁሉ በዘባነ ኪሩቤል ተቀምጧል ማለታችንም እነርሱ ችለው ይሸከሙታል ማለት አይደለም ። ነቢዩ እንዲህ እያለ ይጠይቃል፡- የእግዚአብሔርን መንፈስ ያዘዘ፥ ወይስ አማካሪ ሆኖ ያስተማረው ማን ነው? ወይስ ከማን ጋር ተመካከረ? ወይስ ማን መከረው? የፍርድንም መንገድ ማን አስተማረው? እውቀትንስ ማን አስተማረው? የማስተዋልንስ መንገድ ማን አሳየው? እነሆ፥ አሕዛብ በገንቦ እንዳለች ጠብታ ናቸው፥ በሚዛንም እንዳለ ትንሽ ትቢያ ተቈጥረዋል እነሆ፥ ደሴቶችን እንደ ቀላል ነገር ያነሣል።” (ኢሳ. 40 ፡ 13-15) ።

ክቡር ዳዊት እግዚአብሔርን አምላካችን ፣ መጠጊያችን ፣ ኃይላችን ካለው በኋላ ረዳታችን ይለዋል ። ሰው እውነተኛ አምላኩን ካላወቀ እንደ እርሱ ለተፈጠረ አንዳንዴም ከእርሱ ለሚያንስ ነገር ይሰግዳል ። ሰው መጠጊያ ካላገኘ “እዚህ ነው ያለው” ሳይባል ጠፍቶ ይቀራል ። ሰው ኃይል ካላገኘ መኖር ተራራ መግፋት ይሆንበታል ። ሰው ረዳት ካላገኘ አጥቂው ብዙ ይሆናል ። እግዚአብሔር ግን አምላክ ፣ መጠጊያ ፣ ኃይልና ረዳት ነው ። ነቢዩ እግዚአብሔርን በአምልኮ ያልበደለ ነው ። ጉልበቱ ለጣኦት አልተንበረከከም ። “እንደ ልቤ” ያለውም በዚህ ምክንያት ነው ። ነቢዩ ቤተ መንግሥት ቢኖረውም ፣ ግዛቱ ከዳን እስከ ቤርሳቤህ ቢሆንም መጠጊያ ያደረገው እግዚአብሔርን ነው ። ነቢዩ ሠራዊት ቢኖረውም የፎከረው በእግዚአብሔር ነው ። ሠራዊትም ይከዳል ፣ የደገፈ ሕዝብም ይገፈትራል ። እግዚአብሔር ግን ቆሞ ሁሉን ያሳልፍልናል ። ነቢዩ ረዳቴ አለው ። ብዙ አማካሪዎች ቢኖሩትም የልብ አውቃ እግዚአብሔር ብቻ ነው ።

ነቢዩ ረዳቴ ብቻ አላለም ። “ባገኘን በታላቅ መከራም ረዳታችን ነው” አለ ። የሚናገረው በብዙ ቍጥር ነው ። እግዚአብሔር ያልረዳው ማንም የለምና ። መከራን ፈልገን አናገኘውም ። ፈልጎ ግን ያገኘናል ።

መከራ ሲመጣ አይነግርም ዐዋጅ ፣
ሲገሰግስ አድሮ ቀን ይጥላል እንጅ ።

ተብሏል ። ሰሙ ጠላት ሌሊት ገስግሶ ቀን ላይ አደጋ ያደርሳል የሚል ነው ። ወርቁ ግን ሰውን ዘመን ያዋርደዋል ፣ ቀን ይጥለዋል ማለት ነው ። ወደ መከራ ባንሄድም መከራ ወደ እኛ ይመጣል ። አንድ ቀን ከመከራ ጋር እንገናኛለን ። ሁልጊዜ የታመመ አንጠይቅም ፣ የምንታመምበት ቀን ይመጣል ። ሁልጊዜ ልቅሶ አንደርስም ፣ እኛም ሊደርሱን ሰዎች ይመጣሉ ። እንዳማረ ያለ ፣ የሚኖር ማንም የለም ። ነቢዩ ያገኘው ታላቅ መከራ ምንድነው ? ስንል ሁለት ነው ። ይህንን የምናውቀው ቀጥሎ በገለጸው ቃል ነው ። የመጀመሪያው የጸኑ ሰዎች ሲክዱ ማየት ሲሆን ፣ ሁለተኛው ያከበርናቸው ታላላቅ ሰዎች ቃላቸውን ማጠፋቸው ነው ። የእነዚህ ሁለት ወገኖች መከራ ነፍስን የሚጎዳ ነው ።

እግዚአብሔር አምላክ ባገኘን በታላቅ መከራ ረዳታችን ነው ። አሜን ።

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ኅዳር 27 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ