መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ራሔል ኢትዮጵያ

የትምህርቱ ርዕስ | ራሔል ኢትዮጵያ

“እግዚአብሔር እንዲህ ይላል፦ የዋይታና የመራራ ልቅሶ ድምፅ በራማ ተሰማ ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች የሉምና ስለ ልጆችዋ መጽናናትን እንቢ አለች ።” ኤር. 31፡15 ።
አንድ ትልቅ አባት ነበሩ ። እውቀትም መንፈሳዊነትም የነበራቸው ነበሩና የበቁ አባት ተብለው ሲጠሩ እሰማለሁ ። ምክራቸው እጅግ አሳራፊ ፣ ከእግዚአብሔር የተሰጣቸው ጸጋም በትሕትና የተሽሞነሞነ ነውና ትልቅ ውበት አላብሶአቸው ነበር ። በዚያ በዘጠና ዓመታቸው ከዓመታት በፊት የተነጋገርነውን ሁሉ ያስታውሳሉ ። ጊዜው ከዛሬ 23 ዓመት በፊት ነው ። እኒህን አባት ሳልጠይቃቸው ረጅም ጊዜ ሆኖኝ ስለነበርሁ ወደ በአታቸው የምሄደው እያፈርሁ ነበር ። እርሳቸው በቀን ብዙ ሰው የሚያስተናግዱና መንገድ የሚመሩ ስለነበሩ ሰው አጥተዋል ፣ ብቻቸውን ናቸው ብዬ ሳይሆን ለእኔው ስለቀረብኝና የእግዚአብሔርን ሰው መራቅ ተገቢ ስላልሆነ ነው ። እንደ ሱነም ሴት በቤቴ እንዳልቀበላቸው ቤት የለኝም ። በቤታቸው ግን በልቤ እቀበላቸዋለሁ ። ታዲያ እያፈርሁ ጎንበስ ብዬ ጉልበት ሳምሁ ። እርሳቸውም እንደ ፀሐይ የሚያበራውን ፊታቸውን አሳዩኝና ባረኩኝ ። “የት ጠፋህ ?” አሉኝ ። እኔም “አገልግሎት በዝቶብኝ ነው” አልኳቸው ። በርግጥ አገልግሎት በዛልኝ ነው የሚባለው ብለው ሌላ መምህርም አርመውኛል ። ታዲያ አገልግሎት በዝቶ ነው የጠፋሁት ስላቸው ትክዝ ብለው ሰሙኝና ። “እግዚአብሔር የነገረኝ ነገር ነበር” አሉኝ ። እኔም ጆሮዬን ከልቤ ጋር አንቅቼ ልሰማቸው ፈለግሁ ። “ማስተማርህ መልካም ነው ። ይህ ሕዝብ ግን በትምህርት ብቻ አይለወጥም” ብሎኛል አሉኝ ። እኔም ደንግጬ ለመስማት ተዘጋጀሁ ። “ፌዘኛና አልምጥ ስለሆነ እውቀት ያለው ንጉሥ እያስተማረና እየቀጣ ካልመራው አይሰማም ብሎኛል” አሉኝ ። ይህ ነገር ከድካም አረፍ ስል ፣ ስንዴ ዘርተን ገለባ ስናጭድ ፣ ክርስትናን ሰብከን መተራረድን ስናተርፍ አስታውሰዋለሁ ። ያ እውቀት ኖሮት የሚያስተምር ፣ ሥልጣን ኑሮት ፍትሕ የሚሰጥ ንጉሥ ማን ይሆን እላለሁ ?
ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ። ይህች ራሔል የያዕቆብ ሚስት ራሔል ከሆነች እርስዋ በወሊድ ምክንያት ሞተች እንጂ ልጆችዋ ዮሴፍና ብንያም አልሞቱባትም ። በርግጥ በግብጽ ምድር የታነቁት ሕፃናት ትውልዶቿ ናቸውና ከቀኑ በፊት አዝናለች ፣ የፍቅር አንጀቷ ስለ እነርሱ ተላውሷል ማለት ይሆናል ። ይህች ራሔል በግብጽ የባርነት ዘመን የነበረች ከሆነች ድርስ እርጉዝ ሁና ጡብ የሚሠራበትን ጭቃ ስትረግጥ ልጇ ፈትለክ ብሎ ከማኅፀኗ ወጣ ። በዚህ ጊዜ ደንግጣ ብትቆም አስገባሪው፡- “እርገጭው ምን ይለዋል ፣ የሰው ደም እንደውም ያጠነክረዋል” አላት ። በዚህ ጊዜ “በዚህ ሰማይ የእስራኤል አምላክ የለምን!” ብላ እንባዋን ወደ ላይ ረጨችው ። የራሔልም እንባ መንበረ ጸባዖትን አራሰው ። እግዚአብሔርም ለፍትሕ ተነሣ ፣ እስራኤልም ከግብጽ ባርነት ነጻ ወጣ በማለት ታሪክና ትውፊት አጣቅሰው ትምህርተ አይሁድን አስሰው አባቶች ይነግሩናል ። 
ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ። ይህች ራሔል የዘመናት አልቃሾችን ፣ በልጅ ሞት የሚተክዙትን ወክላ የቆመች ናት ። እንባዋ የዘመናትን የልጆች ሞት ሲገልጥ ይኖራል ። በባቢሎን ምርኮም የእስራኤል ሕፃናት እንደ ጎመን ሲቀረደዱ ፣ እንደ ዛፍ ሲቆረጡ ይህች ራሔል ታወሰች ። ኤር. 31፡15 ። ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ተባለ ። ሄሮድስም የቤተ ልሔም ሕፃናትን ሲፈጃቸው ራሔል ስለ ልጆችዋ አለቀሰች በማለት ቅዱስ ማቴዎስ ያነሣታል ። ማቴ. 2፡17 ። ቅዱስ ማቴዎስ ያነሣት የመጀመሪያው መራራ ኀዘን መሆኑን ስለመግለጥ ነው ። ሁለተኛ ታሪክ መደገሙን ለማንሣት ነው ። ክፉ ታሪክ ሲደገም ሰው ካለፈው አለመማሩን ያሳያልና ያሳምማል ። ካለፈው ትርፍ እንዳልተገኘ ተገንዝቦ አሁንም ትርፍ የሌለው ነገር መሥራቱ ያሳዝናል ። 
ራሔል ዛሬም ያሉትን ፣ በመላው ዓለም ስለ ልጆቻቸው የሚያለቅሱትን አባቶች እናቶች ትወክላለች ። በአገራችን ራሔል ጠፍታም ፣ ልቅሶዋም ነጥፎ አያውቅም ። የዘመናት አልቃሽ ሁና ዛሬም ትጮኻለች ። የዋይታና የልቅሶ ድምፅ በአርያም እየተሰማ ነው ። ባለፉት አርባ ዓመታት እንኳ ስንት ወጣት ረገፈ ። ቀይ ሽብርና ነጭ ሽብር እየተባባለ ስንቱ እንደ ወጣ ቀረ ። ሬሣው የሚያነሣው ጠፍቶ በአደባባይ ዋለ ። እርጉዞች ተገደሉ ፣ ብዙ ወጣቶች የት እንደ ደረሱ ሳይታወቅ ደብዛቸው ጠፋ ። በመቀጠል ለ17 ዓመታት በዘለቀ ጦርነት በሰሜኑ የአገራችን ክፍል ብዙ ወጣት ረግፎ ቀረ ። ይህም ምንም ትርፍ የሌለው የወንድማማቾች እልቂት ነበር ። በ1990 ዓ.ም. “የክፍለ ዘመኑ ኋላ ቀር ጦርነት” ተብሎ በተሰየመው በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል በተደረገ ጦርነት ትውልድ እንደ ወጣ ቀረ ። እነዚያ ወጣቶች እንዳጎደሉ የሚያውቀው ዛሬም ያ ቤተሰባቸው ብቻ ነው ። የእኛ የኢትዮጵያውያን ጸጋችን መርሳት ነውና ረስተናቸዋል ። ላለፉት አርባ ዓመታት ጥቁር ልብስ ያላወለቁ ፣ በኀዘን ምክንያት በሽተኛ የሆኑ ፣ አቅላቸውን ስተው ያበዱ ፣ አጉል ነዋሪ ሁነው የቀሩ ብዙ ራሔሎች አሉ ። በዚህ የደም ገንቦ ላይ እንጨምርበታለን ተብሎ አይታሰብም ነበር ። አሁንም እያትረፈረፍነው ነው ። አዎ ጣፋጩ ትረካችን “ኢትዮጵያ ማንንም ወርራ አታውቅም”  የሚል ነው። ኢትዮጵያውያን ግን ሲተላለቁ የሚኖሩ ናቸው ። እስከ ሰባት ቤት ደም ከሚቃቡት ጀምሮ ያለ ምክንያት እስከሚፈጁት ወገኖች ድረስ የደም ጥምቀት በአገራችን የተለመደ ሁኗል ። ያለፈው ሳይካስ ሌላ ዕዳ እያመጣን ፣ የወለድናቸው ለአንድ ቀን እንኳ የሰላም ድምፅ እንዳይሰሙ አድርገን እያሸማቀቅናቸው ነው ።
 
ራሔል ኢትዮጵያ ስለ ልጆችዋ አለቀሰች ። በጠፍ ጨረቃ ፣ በውድቅት ሌሊት በራቸው ተንኳኩቶ ስለታረዱት ፣ በጎሣቸው ምክንያት ስለተፈጁት ምስኪኖች ልቅሶ በአርያም ተሰማ ። እግዚአብሔር ፍርድ ሲሰጥ ሰምተን እንዳልሰማን የሆነውን ፣ እኔን ካልነኩኝ ብለን ያለፍነውን ሁሉ የብይኑ በትር ያገኘናል ። ሁሉም ነገር ካለቀ በኋላ ወሬ ማሯሯጥ ጥቅም የለውም ። ንጹሕ ነኝ ብሎ ማሰብም ከንቱ ነው ። ማንን ነው የምንቀየመው ? ብለን ስንጠይቅ ገዳይም ሟችም ሁሉም ኢትዮጵያዊ ነው ። 
“የገደለው ባልሽ የሞተው ወንድምሽ ፣
ኀዘንሽ ቅጥ አጣ ከቤትሽ አልወጣ ፤”
ሌላም ግጥም ትዝ ይለናል፡-
“አንጀቴ ተቆርጦ ከሆዴ ከወጣ ፣
እንግዲህ ሐኪሙ ምን ሊቀጥል መጣ ?” 
አዎ ሁለት ነገሮች ያስፈልጋሉ ። የእኛ አባት መገለጥ ቀላል አይደለም ። ፍርድና ትምህርት ያስፈልጋሉ ። ከተመከርንበት የሕንዱ የነጻነት ታጋይ የነበሩት ማኅተማ ጋንዲ እንዲህ ብለው ነበር፡- “በምድር ላይ ብቻህን ብትቀር እንኳ ከግፈኞች ጋር አትተባበር ።”
እግዚአብሔር የመጽናናትን መንፈስ ይላክልን ። ላዘኑት የሚያረጋጋ መልአክ ይላክልን ። ልብ ይስጠን ።
“ጎዳናው ሳይጠበን አመል እያጋፋን ፣
አካሄዱ ቀርቶ አቋቋሙ ጠፋን ፤”
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሐምሌ 28 ቀን 2012 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም