የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ራስን መግዛት

 “እንግዲህ ኤጲስ ቆጶስ እንዲህ ሊሆን ይገባዋል፤ … ራሱን የሚገዛ” 1ጢሞ. 3 ፡ 2
ብዙ ሰዎች የመግዛት ምኞት አላቸው ። እገሌ የገዛውን አገር እኔ መግዛት አያቅተኝም ይላሉ ። ብዙ ፖለቲከኞች አገር የመምራት እቅድም ዝግጅትም አላቸው ። አንድ ሰው ብቻ ቢቀመጥበትም የንጉሥን ወንበር አያሌዎች ይመኙታል ። በምድር ላይ ከኖርንበት ሰባ ዓመት አገር የምንመራበት አራት ዓመት ከባድ ፈተናና ትግል ያለበት ነው ። የቀላው የሚጠቁርበት ፣ የጠቆረው የሚነጣበት ፣ እየባነነ የሚኖርበት ፣ የዛፍ ላይ እንቅልፍ ቢሆንም ብዙ ሰው መግዛትን ይመኛል ። ሁሉ ሰው አገር አይገዛም ። ሁሉ ሰው ግን ራሱን መግዛት ይችላል ። ሰው በተፈጥሮው ገዥ ሁኖ ስለ ተፈጠረ ራሱን ሊገዛ ሌሎችን ሊመራ ይገባዋል ። አምባገነን ከሆነም በሥጋው ላይ ፣ ቊጡ ከሆነም በምኞቱ ላይ ሊሆን ይገባዋል ። አገር የገዙ ሰዎች ራሳቸውን መግዛት አልቻሉም ነበር ። አገር እየገዙም ራስ ሊያምፅ ይችላልና ራስን መግዛት ትልቅ ሥልጣን ነው ። በሰው ላይ የበላይ ከመሆን በአንደበታችን ላይ የበላይ መሆን የተሻለ ነው ።

ብዙ ጠባቂ ያለው ንጉሥ ዳዊት፡- አቤቱ፥ ለአፌ ጠባቂ አኑር ፥ የከንፈሮቼንም መዝጊያ ጠብቅ” ብሏል መዝ. 140፡3 ። ሕዝቡ ይጠብቀናል የሚለው ንጉሥ እርሱ መጠበቅ ያቃተው የገዛ አንደበቱን ነበር ። ሕዝቡ ጠባቂ ያኖርልናል የሚለው ንጉሥ እርሱ የከንፈሮቹን መዝጊያ እንዲጠብቅለት እግዚአብሔርን ይማጸናል ። ምነው ባልተናገርናቸው ብለን የምንጸጸትባቸው ቃላት አሉ ። ምነው ዱዳ ባደረገኝ ያልንባቸው ያመለጡን ንግግሮች አሉ ። ከባዱ ዝሙትን ፣ ከባዱ ስርቆትን እንቢ ማለት አይደለም ። ከባዱ አንደበትን መግዛት ነው ። ሰው አንደበቱን መቆጣጠር ከቻለ ሌሎች ኃጢአቶች አይከብዱትም ። አንደበት በልባችን ያለውን ብቻ ሳይሆን የሌለውንም የምናወጣበት ነው ። አስበን መናገር ሲያቅተን ተናግረን ማሰብ እንጀምራለን ። አንደበት ፈተና ማስገቢያም ነው ። በተናገርነው እንጠመዳለን ። በፈረድነው እንያዛለን ። ኤጲስ ቆጶስ ራሱን የሚገዛ መሆን ይገባዋል ።
መኪና ጎማ ብቻ ሳይሆን ማብረጃ ፍሬን አለው ። ማብረጃ ባይኖረው መኪና አደጋ ብቻ ይሆን ነበር ። ፈረስ ልጓም ፣ መኪናም ፍሬን አለው ። ሰውም ራሱን የሚቆጣጠርበት ትዕግሥት ሊኖረው ይገባል ። ራስን መግዛት የሚለው ቃል የገበያ ቋንቋም ነው ። መግዛትና መሸጥ የሚባሉ ቃላት የገበያ ቋንቋ ናቸው ። ሰው ንብረቱን ሊሸጥ ፣ ከብቱን ሊለውጥ ይችላል ። ራሱን ግን መግዛት አለበት ። ራስ አይሸጥምና ። ራስ አይለወጥምና ። የተሸጠ ነገር የገዛው ሰው እንደ ፍላጎቱ ይጠቀምበታል ። ራስን አለመግዛት ማለት ክፉ ተናግረው ክፉ ለሚያናግሩን ሰዎች ራስን አሳልፎ መስጠት ነው ። ገዝተውናልና እንዳሻቸው ይጠቀሙብናል ። እየተሳደቡ ተሳዳቢ ፣ እየተተናኮሉ ተንኮለኛ ፣ እየወረወሩ ድንጋይ ወርዋሪ ያደርጉናል ። ራስን መግዛት ራስን አለመሸጥ ነው ። ለዝሙት የተሸነፉ ሰዎች ራሳቸውን ሸጠዋል ። ልብስና አካል እያዩ ፣ የዝሙት ቅብዐ መንግሥት የሆነውን ሽቱ እየተከተሉ የነጎዱ እነርሱ ራሳቸውን ሸጠዋል ። ራሳችንን የምንገዛበት ዋጋ ከፍ ያለ ነው ። ከወርቅም በላይ ነው ። እርሱም ቅድስና ይባላል ።
ራስን መግዛት በብዙ መንገድ ያስፈልጋል ። ራስን መግዛት ሲባል አንድ ነገርን ወይም ፈቃደ ሥጋን ብቻ የሚመለከት አይደለም ። ራስን መግዛት መናኔ ንብረት መሆንም ነው ። ቅዱሳን አባቶቻችን ዘውድ አስቀምጠው ሲመንኑ ፣ ያላቸውን ለድሆች ሰጥተው የክርስቶስ ሙሽራ መሆንን ሲመርጡ ራሳቸውን ስለ ገዙ ነው ። ራስን መግዛት መተው ብቻ ሳይሆን መስጠትም ነው ። ራስን መግዛት ስርቆትን እንቢ ማለት ብቻ ሳይሆን መስጠትንም መፈለግ ነው ። ያዩትን ዕቃ የእኔ የሚሉ ፣ እንደ መንፈቅ ልጅ ሁሉን ላፌ በማለት የሚያስቸግሩ ራሳቸውን መግዛት ያልቻሉ ናቸው ። ይልቁንም በድህነት ያደገ ወርቅ አይጠግብምና መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ወርቅ የማይጠግቡ ነገሥታት ገዳማትን ዘርፈዋል ። የእግዚአብሔርን አሥራት ሰርቀዋል ። መቅደስ አቃጥለዋል ። ብዙ ትዳሮች የሚፈርሱትም በምኞታቸው ራሳቸውን በማይገዙ ሰዎች ምክንያት ነው ። ያገኙትን ልብስ ፣ የማያደርጉትን ጫማ እያግበሰበሱ ይዘው የሚገቡ ኑሮአቸው ላይ እክል ይገጥማቸዋል ። ራስን አለመግዛት አለመርካትን ያመጣል ። በየገበያ የሚያዞር አመል ያለባቸው ሰዎች አሉ ። ይህ መታከም ያለበት በሽታም ነው ። ተበድረው ፣ በዱቤ ያገኙትን ሁሉ አግበስብሰው ይገባሉ ። በዕቃ ላይ ራስን መግዛት ካልቻልን መተኛ ቦታ እስክናጣ ቤታችን ገበያ ይመስላል ።
ኤጲስ ቆጶስ ራሱን መግዛት አለበት ። የመነኮሳት ፆራቸው ስስት ነው ይባላል ። ጌታችን ስስትን በምድረ በዳ ድል ነሣ ። የቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪዎች እናትና አባታቸው እግዚአብሔር ነውና የሚጦር ልጅ ፣ የሚረዳ ዘመድ የለኝም ብለው ሊስገበገቡ አይገባም ። ምክንያቱም የሚሰብኩት አምላካቸው እንኳን ለሚያገለግሉት ለጠላቶቹም የሚመግብ ነው ። ስስት ራስን አለመግዛት ነው ። ገቢ እንጂ ወጪ አለመውደድ ራስን አለመግዛት ነው ። በስስት ምክንያት በቀላሉ ታክመው ሊድኑ ሲችሉ ከፍተኛ በሽታ በራሳቸው ላይ የጠሩ አሉ ። ራስን አለመግዛት መሰብሰብ ብቻ ሳይሆን በስስት ራስን መርዳት አለመቻልም ነው ።
ኤጲስ ቆጶስ አንደበቱን የሚገዛ መሆን አለበት ። እንኳን ክፉ ቃሉ ደግ ቃሉም ይተረጎማልና ትዕግሥተኛ መሆን አለበት ። ከእርሳቸው ይህን አንጠብቅም የሚሉ ብዙ ታዛቢዎች ሲኖሩ ጥቂት ሸፋኞች ማግኘት ከባድ ነው ። ሰው አገልጋይ ቢሆንም ሰውነቱ አይቀርም ። አገልጋይ የሚበላ ፣ የሚጠጣ ፣ የሚያዝን የማይመስላቸው ሰዎች አሉ ። ይህ ትልቅ አለማወቅ ነው ። ስሜት ተሸክመን የሌላውን ስሜት መረዳት አለመቻል ትልቅ ኪሣራ ነው ። ክፉ ንግግርን መናገር አብረው ለመኖርም ለመለያየትም አይጠቅምም ። አብረው የሚቀጥሉ ከሆነም እንቅፋትና ተጨማሪ ቅያሜ ነው ። የሚለያዩም ከሆነ ያለቀ ጉዳይ ነውና ራስን ማራቆት ነው ። “የጨዋ ልጅ ሲፋታ የሚጋባ ይመስላል” እንዲሉ ።
ለቤተ ክርስቲያን አስተዳዳሪ ቶሎ ባለመወሰን ራስን መግዛት አስፈላጊ ነው ።አንድ ውሳኔ ከመወሰን በፊት ቢያንስ የሦስት ቀን ዕድሜ መስጠት ተገቢ ነው ። በቤተ ክርስቲያን ያለው ውሳኔ በአብዛኛው ነፍስን የሚመለከት በመሆኑ ጥንቃቄ ይፈልጋል ። መሾም ማለት ለመወቀስ ፣ ለመከሰስ ራስን አሳልፎ መስጠት ነው ። ስለዚህ ወቀሰኝ ፣ ከሰሰኝ ብሎ እንጀራ መንሣት ተገቢ አይደለም ። ሰው የሚከስሰውም እየበላ ነውና እንጀራን መንሣት ለአንድ ኤጲስ ቆጶስ ተገቢ አይደለም ። ከእኔ ይቅር እያለ መጓዝ ይገባዋል ። የራስን ስምና ክብር ማስጠበቂያ ሳይሆን የክርስቶስን ስምና ክብር መጠበቂያ መንበር መሆኑን ማሰብ ያስፈልጋል ።
ኤጲስ ቆጶስ ሹመት በመስጠት ራስን መግዛት ይገባዋል ። ወንጌልን ያልተማረና መንፈሳዊነት የጎደለውን ሰው ሳመኝ ፣ አወደሰኝ ብሎ መሾም ለቤተ ክርስቲያን በሽታ መፍራት ነው ። የእልህ ሹመቶች ቀጣዩን ትውልድ የሚበቀሉ ናቸው ። ኤጲስ ቆጶስ ከመጠን ያለፈ ውዳሴ የሚያቀርቡለትን መጸየፍ ይገባዋል ። እንደ እግዚአብሔር ቅዱስ የሚሉን እንደ ሰይጣን ርኵስ ሊሉን ቅርብ ናቸውና ። ይልቁንም የጉቦ ሹመት መስጠት ራስን ማዋረድ ፣ ትውልድን ለነጋዴ አሳልፎ መስጠት ነውና መጠንቀቅ ይገባል ። የቅን አገልግሎታችን ከሰው ዘንድ ዋጋ ባያገኝ እግዚአብሔርን ካስደሰተ በቂ ነው ።ኃይለኝነት የሚያስከብር ቢሆንም ትሕትና ግን ክብሯ ከሰማይ ነው ። መንፈሳዊ መሪ ትሑት እንጂ አምባገነን መሆን የለበትም ።
ለሁላችንም ራስን መግዛት ይስጠን ።
1ጢሞቴዎስ 36
ጥር 11 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲ.አ.መ.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ