የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላማችን

 “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ዮሐ. 20፡19
ያለ ቦታው ፣ ያለ ጊዜውና ያለ ሁኔታው የተነገረ ቃል አይደለም ። ቦታው ደጆች የተዘጉበት ፣ ጊዜው ምሽት ፣ ሁኔታውም ቅዱሳን ሐዋርያት በፍርሃት የሚናጡበት ነው ። በምድረ በዳ ላይ ፣ በጥማት ስፍራ እንደ ተገኘ ውኃ በታላቅ ጉጉት የሚቀበሉት መልእክት ነው ። ከቦታ ፣ ከጊዜና ከሁኔታ በላይ ያልሆነ ይህን ሊናገር አይችልም ። ስለ ሰላም የተነገረ የምኞት መግለጫ አይደለም ፣ ሰላምታን ማጣፈጫም አይደለም   ። እንዲህ ያለ ሰላምታ በቀን ሊነገር ይችላል ። አንድ ሰው በምሽት፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ብሎ እቤታችን ቢመጣ መልሳችን “በሰላም ነው?” የሚል ነው ። ጌታ ግን በምሽት “ሰላም ለእናተ ይሁን” አለ ። ምሽትን ማለዳ ማድረግ ይችላልና ። በተዘጋ ደጅ የገባም በተዘጋ ልብ ገብቶ ማረጋጋት ይችላል ። እርሱ የሰላም አለቃ ነው ። አለቃ የበታቹን ናና ሂድ ይለዋል ። ክርስቶስም ሰላምን ማዘዝ ይችላል ። እርሱ ራሱም ሰላማችን ነው ።

ጌታችን በሞቱ ሰማይና ምድርን ፣ ሰውና እገዚአብሔርን ፣ ሕዝብና አሕዛብን ፣ ሰውና መላእክትን ፣ ነፍስና ሥጋን አስታርቋል  ። ሰላም ተሰደው የነበሩት መመለስ ፣ ተራርቀው የነበሩት መቀራረብ ፣ ደስታ አጥተው የነበሩት ደስታ ማግኘት ፣ ተለያይተው የነበሩት አንድ መሆን ፣ ጠላቶች የነበሩት አንድ ላይ መዘመር ፣ ዋጋ አጥተው የነበሩ ነገሮች ዋጋ ማግኘት ነው ። በሰላም ውስጥ ዕርቅ ፣ መመለስ ፣ መቅረብ ፣ መደሰት ፣ ያጡትን ማግኘት ፣ አንድ መሆን ፣ ወዳጅነት አለ  ። ጌታችን ሰላምን ለማምጣት የከፈለው ውድ ሕይወቱን ነው ። ሰላም የእግዚአብሔር ልጅ የሞተበት ትልቅ ርእስ ነው ። ሰላም ውድ ዋጋ ያስከፍላል ፣ ከሄደ በኋላ ግን ዋጋ ለማገኘት ያስቸግራል ። ሰላም ሁሉም ነገር ነው ። ነግዶ ለማትረፍ ፣ ወልዶ ለመሳም ፣ አገልግሎ ለመጦር ፣ አስማምቶ ለመግዛት ፣ ተወዳድሮ ለማሸነፍ ፣ ዘርቶ ለመቃም ፣ አፍቅሮ ለመደሰት ፣ ወጥቶ ለመግባት ፣ ተቀጣጥሮ ለመገናኘት ፣ ደግሶ ለመሰረግ ፣ ሞቶ ለመቀበር እጅግ አስፈላጊ ነው ። ሰላም ማጣት የሚያስከፍለው ዋጋ ከባድ ነው ። የአንድ ዓመት ሁከት የሚያመጣውን ውድቀት የሦስት ዓመት ሰላም አያነሣውም  ። ሰላም ስናጣ ሰዎች ይፈሩናል ። የቀረቡንም ይሸሹናል ። ሰላም የሌለው ምንም ከማድረግ አይመለስም በማለት ይጠሉናል ። የተናቅን ሕዝቦች የሚያደርገን ሰላም ማጣት ነው ። በሰላም ዘመን ገንዘብ የሚያበድሩን በጦርነት ዘመን የጦር መሣሪያ ያበድሩናል ። የእኛ ሰላም ያለው በክርስቶስ እጅ እንጂ ሌላውን በመግደል ውስጥ አይደለም ። ጨው በሁሉ ቦታ ያስፈልጋል ። የጨው ዘር ከቤተ መንግሥት እስከ ድሀ ቤት ተበትኗል ። ጨው በሁሉ ምግብ ላይ ቢገባ ጣዕም ይሰጣል ። ሰላምም ሁሉንም ነገር አስደሳች ያደርጋል ። ጨው ማዳበሪያ ይሆናል ፣ ሰላምም የፍሬያማነት መገኛ ነው ። ጨው ቍስል ይደርቃል ። ሰላምም ብዙ በሽታዎችን ይፈውሳል ። ጨው በረዶውን ያሟሟል ፣ ሰላምም ጠጣሩን ነገር ፈሳሽ ፣ ክፉውንም ደግ ያደርጋል ። ሰላም በሌለበት ካህን መቀደስ ፣ ሰባኪ ማስተማር አይችሉም ። ሰላም በሌለበት ሰው ራሱን ሊያይና ሊለወጥ አይችልም ። ሰላም ሳለች እርካሽ ስትሄድ ግን ውድ ናት ። እናት እያለች ብዙም ጥቅም ያላት አትመስልም ፤ ስትሞት ግን ልጆች ሲበተኑ ፣ አሳዳጊ ሲያጡ ፣ ቤቱ ሲቀዘቅዝ ፣ ስምምነት ሲጠፋ ፣ የሁሉን አመል የሚሸከም ሲታጣ ፣ ተጎዳሁ ባይ ሲበዛ ፣ ጎዳሁ የሚል ሲጠፋ ያን ጊዜ ዋጋዋ ይታወቃል ። ሰላምም እንደ እናት ናት ።
ጌታችን ኀዘንም ደስታም ያወካቸውን ደቀ መዛሙርት ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው ። ማዕበሉም የማዕበሉም ጌታ ካወከን አስቸጋሪ ነው ። መጸለይና አለመጸለይ ሁለቱም አንድ ከሆነብን እንደ ገና ራሳችንን መመርመር አለብን ። ደቀ መዛሙርቱ ሞተ ሲባል እንዳዘኑ ተነሣ ሲባል ሊደፍሩ አልቻሉም ። በነፍሳቸው ላይ ማዕበል ማዕበልን እየጠራ ይቀጣጠል ነበር ። አንደኛው ማዕበል ጸጥ ሳይል ለሌላኛው ያስረክባቸው ነበር ። አጥተው ያዘኑ አግኝተው ካላመሰገኑ ፣ ብቻዬን ነኝ ያሉ እግዚአብሔር ሲያበዛቸው ተመስገን ካላሉ አስቸጋሪ ነው ። መልሱ መልስ ያልሆነው ጥያቄው ጥያቄ አልነበረም ማለት ነው ። ጌታችን ግን በመካከላቸው ቆሞ፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። ገድለው ወደ ደፈሩት አልሄደም ፣ አዝነው ወደ ፈሩት መጣ እንጂ ። ይህ ቢያንስ ሰውነት ነውና ። ገድለው የሚፈረጥሙ አራዊት ናቸው ፣ ባዩት ክፉ ነገር አዝነው የሚፈሩ ሰዎች ናቸው ። ልብን በእግዚአብሔር ማበርታት ግን እርሱ እምነት ነው ። እንደ ሰውነታችን ብንፈራም እንደ አማኝነታችን መበርታት አለብን ።
ጌታችን፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። የንግግር መክፈቻ አይደለም ። የልብን ማዕበል እየገሠጸ ነው ። ራሱ ተናጋሪ ራሱ ሰሚ የሆነውን የሰውን ስሜት እያበረደ ነው ። በእሳት ላይ ውኃ እንደመቸለስ ጌታችን “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። በሲኦልም የተሰማው የምሥራች ይህ ነው ። የመውጫው በር ጠፍቷቸው የሺህ ዓመት መንገድ ለተጓዙት ነፍሶች “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። ይህ የምሥራች ቅድስት ቤት ክርስቲያን ተናግራ የማትጠግበው ነው ። ካህኑ “ሰላም ለኩልክሙ” ይላል ። በሲኦልና በዝግ ቤት ገብቶ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ያለውን ክርስቶስን ወክሎ መናገሩ ነው ። ሲኦልን ፣ ዝግ ቤትን ፣ ፈሪ ልብን የሚያረጋጋው ክርስቶስ ነው ። ሰላም ካሣ ይፈልጋል ። በደሙ የካሰው ለሲኦል ነዋሪዎች “ሰላም ለእናንተ ይሁን” አላቸው ። እንዲከፍሉ ሳይሆን እንዲቀበሉ ጠየቃቸው ። በዝግ ልብ ላሉም እንዲከፍሉ ሳይሆን እንዲቀበሉ ሰላምን ሰበከላቸው ።
እርሱ ስሙ በተጠራበት የሚገኝ ነው ። በዝማሬ ስሙን ስናወደስ በመካከላችን ነው ። ጸሎት ሲጠፋብን ፣ ሁሉም ነገር አውሬ ሁኖ ሲሳልብን ፣ ማመን ሲቸግረን ፣ ፍቅር ሲቀዘቅዝብን ፣ ተስፋ ሲጨልምብንም በመካከላችን ቆሞ፡- “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ይለናል ። የብርታታችን ወዳጅ ነው ፣ የድካማችንም ዋስ ነው ።
ለደቀ መዛሙርቱ ሰላም ከሰበከ በኋላ ሥልጣንን ሰጣቸው፡- ኢየሱስም ዳግመኛ፡- ሰላም ለእናንተ ይሁን ፤ አብ እንደ ላከኝ እኔ ደግሞ እልካችኋለሁ አላቸው ። ይህንም ብሎ እፍ አለባቸውና፡- መንፈስ ቅዱስን ተቀበሉ ። ኃጢአታቸውን ይቅር ያላችኋቸው ሁሉ ይቀርላቸዋል ፤ የያዛችሁባቸው ተይዞባቸዋል አላቸው ።” /ዮሐ. 20፡20-23 ።/ ኃጢአት ሰይጣን ሰውን የገዛበት ሕጋዊ ሰነድ ነው ። አሁን ግን ኃጢአት ይቅር የማለት ሥልጣን ለአገልጋዮች ተሰጠ ። ንስሐ ፣ ስርየት ፣ ሰላም ተገኘ ። የኃጢአት የመጀመሪያ ውጤት ፍርሃት ነበረ ፣ ሰላምን ከሰበከላቸው በኋላ ሥሩን እንዲያደርቁ ኃጢአትን ይቅር የማለት ሥልጣን ሰጣቸው ። በተዋሕዶ አምላክ ሰው ፣ ሰው አምላክ ሆነ ። አምላክነትን ለዚህ ሥጋ ሲሰጥ ተቀብለናል ፣ ይቅር ማለትንም ለሰው ልጆች ሰጠ ። ኃጢአትን ይቅር ለማለት ማስተማር ፣ ወንጌልን መስበክ ይገባል ። ያን ጊዜ ሰዎች ራሳቸውን በክርስቶስ አይተው ወደ ንስሐ ይቀርባሉ ። ስርየትንም ይቀበላሉ ።
ጸሎት
ጌታ ሆይ ቃል ብቻ ተናገር ብላቴናው ሰላማችን ይፈወሳል ። አሁን ደፍረን አሁን የምንበረግግ ፣ አሁን ታርቀን አሁን ዕርቄን አፍርሻለሁ የምንል ፣ ብላቴና ሰላማችን የታመመብን ነንና እባክህን ቃል ብቻ ተናገርና ፈውስልን ። ሰላማችን ሞቶ እንዳንቀብረው ብቅ ይላል ። ኖሮ እንዳንደሰት ይሰወራል ። እባክህን በተዘጋው ልባችን ገብተህ “ሰላም ለእናንተ ይሁን” በለን ። የሁከት ምንጩ ይደርቅ ዘንድ አንተ እንዲህ ያለውን ሥልጣን ለሰው ልጆች ስለሰጠህ ምስጉን ነህ ። በከበረው ዙፋንህ ለዘላለሙ አሜን ።
የመስቀሉ ገጽ/ 10
ግንቦት 22 ቀን 2012 ዓ.ም.
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ