የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላማችን ነውና

“እርሱ ሰላማችን ነውና ፤ ሁለቱን ያዋሐደ በአዋጅ የተነገሩትንም የትእዛዛትን ሕግ ሽሮ በመካከል ያለውን የጥል ግድግዳን በሥጋው ያፈረሰ ፤ ይህም ከሁለታቸው አንድን አዲስን ሰው በራሱ ይፈጥር ዘንድ ሰላምንም ያደርግ ዘንድ ፥ ጥልንም በመስቀሉ ገድሎ በእርሱ ሁለታቸውን በአንድ አካል ከእግዚአብሔር ጋር ያስታርቅ ዘንድ ነው ።” ኤፌ. 2 ፡14-17 ።

ይህን ዓለም ብንዞር ለሰላም የሚበጅ ነገር የለውም ። በሕግና ፣ በእውቀት ፣ በሞራል የተደራጁ ተቋማትም ስጋትን እንጂ ሰላምን አያበስሩም ። የዚህች ዓለም ከፍተኛ ሀብት የሚባክነውም ለስለላና ለጦርነት ነው ። ይልቁንም በዚህ ዘመን መጠኑ ይለያይ እንጂ ሁሉም ሰው ሁከት አለበት ። ባሕር የረጋ እንዳልሆነ በባሕር የሚመሰለው የሰው ሕይወትም እርጋታ አጥቷል ። ትላንትና የነበረው የአቅርቦት ችግር ፣ ከትላንት በስቲያ የነበረው ውጥረት ረሀብ ይሆናል ። ዛሬ ደግሞ የሰላም ጥያቄ ይመጣል ። ፍርድ በፍርድ ቤት ፣ ጤና በሐኪም ቤት ፣ ፍቅር በፍቅር ቤት ፣ እውነት በእውነት ዐውድ ፣ ዳቦ በዳቦ ቤት የማይገኝበት ዘመን ፣ ሕይወት በብዙ ቍስሎች የተወጠረችበት ፣ ሁሉ ባለጉዳይ ሁኖ አእምሮው የተወጠረበት ጊዜ ነው ። ማታ ላይ ያገኘነው ሰው “እንደምን አደራችሁ?” ብሎ ሰላምታ የሚሰጥበት ፣ እየተሰናበተ ያለው ወገን “ደኅና ዋልህ ወይ?” የሚልበት ፣ የሰላምታ እጅና እግር የጠፋበት ፣ ሰው ከአቅሉ ያልሆነበት የእኛ ዘመን ነው ። የነገር እሹሩሩ ይዞ የሚወዘወዘው ፣ ልጅ አዋቂው ውስጡ የሳሳበት ዘመን ነው ። የሃያ ዓመት ትዳራቸውን የሚያከብሩ በቤት ውስጥ ከተለያዩ ዐሥር ዓመት የሆነበት ፣ ሰው ፊት “ማርዬ-ሃኒ” እየተባባሉ የሚቀራደዱበት ፣ በደረቁ የሚለጫጩበት የታይታ ዘመን ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎች ፍርድ ቤት ተካስሰው በሩ ላይ ሲገናኙ “ወንድሜ ፣ ወንድሜ” ተባብለው የሚሳሳሙበት ፣ ዳኛ ፊት ቆመው አንዱ የአንዱን ዕርቃን የሚገፍበት ፣ አገልጋይነት ተውኔት የሆነበት ጊዜ ነው ።

የአዳም ዘር በምቹ ትራስ ላይ ሁኔታዎች እየቆረቆሩት ፣ አልጋው ሲገኝ እንቅልፉ እየጠፋበት ነው ። ሰው ሁሉ እኔ ነኝ ላለማለት በሁሉም ነገር እገሌ ነው በማለት ሰበብ የሚበጅበት ፣ ኃላፊነት የሚወስድ የታጣበት ፣ የጥቆማ ዘመን የእኛ ዘመን ነው ። ሺህዎች በረሀብ ፣ ሚሊየኖች በመፈናቀል ፣ አእላፋት በሞት እየታጨዱ ለጉዳቱ ሳይሆን ለሰበቡ የሚጨነቁ አለቆችን ያፈራችው የእኛ ስምንተኛ ሺህ ናት ። ወደ ግራ ዞር ስንል ሱስ ጠባያቸውን ነሥቶአቸው በቀን ዘጠኝ ጊዜ የሚያብዱ ሰዎችን እንመለከታለን ። ወደ ቀኝ ስንዞር ግፍን በምስኪኖች ላይ ሲያደርጉ ፣ የሌላውን ቀምተው በመክበር “እግዚአብሔር ሰጠኝ” ብለው ምስክርነት የሚያሰሙ ሰዎችን እንታዘባለን ። ወደ ኋላችን ስንዞር የመከራቸው ጅረት መቆሚያ አጥቶ የሚሰቃዩ ድሆችን ፣ መኖሪያ ሳይሆን መቀበሪያ የተነፈጉ ምስኪኖችን እናስተውላለን ። ወደ ፊት ለፊታችን ስናማትር ሰዎች ተጠባብቀው ሲኖሩ ፣ ለአንድ ክፉ ቀን ቀጠሮ ይዘው እንዳደፈጡ እንገመግማለን ። ያሳደጉት ልጅ ጎሣዬን አገኘሁ ብሎ ሽማግሌዎችን ሲገድል ፣ አባትና እናቱን አቅፎ ይዞ የሰው አባትና እናት ሲገድል ፣ ሽበት የማይታፈርበት ፣ ሽምግልና ውርደት የሆነበት ዘመን ላይ እንዳለን ተረድተናል ። ክህነት ተዋርዶ ፣ “አባቴ ይፍቱኝ” እያለ አባቶቹን ለማሰር በጨለማ የሚያደባ ምእመን የሞላበት የእኛ ዐውድ ነው ። የዕዝ ሰንሰለት ተቋርጦ ሁሉም በየሰፈሩ አለቃ የሆነበት ፣ አስጨናቂው በዝቶ አቤት ይሉበት የጠፋበት ፣ ራስና እግር ቦታ ተለዋውጠው የምንውለበለብበት ዘመን ፣ ሁሉም በተበዳይነት ስሜት ዱታ ነኝ ብሎ የተከመረበት ጊዜ ነው ።

አሁን ያለነው ዘመናዊ ዓለም ውስጥ ነው ፤ ሰው ጠንቋይ ቤት ሊሄድ አይችልም ብለን እናስብ ይሆናል ። ጠንቋዮቹ ግን ቤተ ክርስቲያን መጥተው “በአንድ ድንጋይ ሁለት ወፍ” በሚል ስልት በቤተ እግዚአብሔር ከእግዚአብሔር የጠፋንበት ዘመን ላይ ነን ። ሐኪም ቤት ሲበዛ ታማሚ ፣ ፈዋሽ ሲበዛ በሽተኛ ፈላብን ። ጸሎትና ፈውስ እንደ ሸቀጥ የሚቸረቸሩበት ዘመነ አብዳን የእኛ ዘመን ነው ። ታዲያ በዚህ ሁሉ ውስጥ ሰላማችን ማን ይሆን ? ብለን መጠየቃችን አይቀርም ። ሰላማችን አንድ አለ ። እርሱም በቀራንዮ መስቀል ስለ እኛ የሞተው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ። እርሱን ብቻ ስናይ የጠፋው ዓይናችን ይበራል ፣ የተስፋ ችቦአችን ይቀጣጠላል ። በኀዘን የደነቆሩ ጆሮዎቻችን የምሥራች ይጠግባሉ ። የዛለ ጉልበታችን ይበረታል ። የታፈነው ልባችን አዲስ አየር ያገኛል ። እርሱ ሰላማችን ነው ። ያስደስታሉ ብለን የሄድንባቸው ስፍራዎች ትዝብት ይዘን ስንመለስባቸው ኃጢአት በኃጢአት አልነጻ ብሎን ስንጨነቅ ፣ ሁሉም ነገር ፍለጋና ድካም ብቻ ሲሆንብን ልባችን ይታወካል ። ሰላማችን ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

ሰላም የማጣት ትርጉሙ ሁለት ወገኖች ዳርና ዳር ሁነው መታኮሳቸው ነው ። አንዱ ማንነታችን ለሁለት ተከፍሎ ፣ አንዱ ትዳራችን በእጥፍ ተቧድኖ ትግል ሲጀምር እርሱ ሰላም ማጣት ነው ። ይህን ሊያስታርቅ የሚችል ማነው ? አዳም አንድ ነበረ ። ሁሉም ከአንድ ምንጭ ተገኘ ። ኋላ ላይ ግን ሕዝብና አሕዛብ ተብሎ ተከፈለ ። ሰውና መላእክትም በተፈጥሮ ክብር የተካከሉ ፣ አንድ መንግሥተ ሰማያትን የሚወርሱ ናቸው ። ኃጢአት ግን ግንብ ሁኖ ለያቸው ። በእውነት አስታራቂ ነኝ የሚል ቢነሣ ሰማይ ደርሶ መላእክትን ፣ ምድር ወርዶ ሰውን አግባብቶ ድልድይ መዘርጋት አለበት ። ፍጹም አምላክ ፣ ፍጹም ሰው ከሆነው ከክርስቶስ በቀርም ይህን ሰላም ሊያመጣ የቻለ የለም ። ሰውና መላእክት ፣ ሕዝብና አሕዛብ በደሙ ታረቁ ። ሰይጣን ለመለያየት ምክር ብቻ ተጠቀመ ፤ ጌታችን ግን አንድ ለማድረግ ደሙን አፈሰሰ ። ለመለያየት የሚያስፈልገው “አንተ እኮ ትልቅ ነህ” የሚል ውዳሴ ከንቱ ነው ። ለማገናኘት ግን ያስፈለገው ደመ ወልደ እግዚአብሔር ነው ። አንድ ማድረግ ከባድ ነው ።

እርሱ ሰላማችን ነው ። ከራሳችን ያስታረቀን ፣ ግንቡን ያፈረሰልን ኢየሱስ ክርስቶስ ነው ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ