የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ

 

ወዳጄ ሆይ !

መጻሕፍት የአእምሮ ምግብ ናቸው ። ሆድን አጥግቦ አእምሮን ባዶ ማድረግ የመንፈስ ረሀብ ያመጣል ። ውስጣቸው እየሞተ ያሉ ሰዎች ማሳያው ማንበብ ማቆማቸው ነው ። መጻሕፍት ስትገዛ የምትከፍለው ገንዘብ ለወረቀቱ እንጂ ለአሳቡ አይደለም ። በምድር እጅግ ደግ የሚባሉት እውቀታቸውን ሳይሰስቱ የሚሰጡ ጸሐፍት ናቸው ። የኪስ ምጽዋት የሚሰጡትን እያከበርህ የነፍስ ምጽዋት የሚሰጡትን ደራስያን አትናቅ ። ጌጥ ለመግዛት የማይከራከር መጽሐፍ ለመግዛት የሚከራከር ደካማ ትውልድ ነው ። ከሳንሱር ሕጎች በላይ የሚያሳዝነው የማይጽፉ ሰዎች የሚጽፉትን መተቸታቸው ነው ። የአሳብ ክብር በሌለበት የአገር ዕድገት አይታሰብም ። የራስህንና የሰዎችን ዋጋ የሚያሳውቁህ ደገኛ መጻሕፍት ናቸው ። 

ወዳጄ ሆይ !

በታላቅ ስቃይ ውስጥ ላሉ ወገኖች እግዚአብሔር የሚሰጣቸው ዕረፍት ሞት ይባላል ። ሞት የሰው ልጆች ሁሉ የሚከፍሉት ዕዳ ነው ። የሞትን ዕዳ እናት ለልጅዋ መክፈል አትችልም ። እርሱ ሞቶ አንተ አትቀርምና በጠላትህም ሞት ደስ አይበልህ ። ክርስትና በውስጣችን ትኩስ በነበረበት ዘመን ከባሕር ዳርቻ መዝናኛ ይልቅ የሰማይ ወደብ ይናፍቀን ነበር ። እግዚአብሔር የልብ ሀብት በመሆኑ ዕረፍት ፣ ተስፋ በመሆኑም ናፍቆት ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

ቁምነገረኛ ሰው በሕይወቱ መጻሕፍትን ያነባል ፣ በሞቱ እርሱ ራሱ ሲነበብ ይኖራል ። ሞት ስጋት የሚሆንብን ስላልተዘጋጀን ነው ። የክርስቶስ ምጽአት ለመቃረቡ ማሳያው ምጽአቱን ክርስቲያኖች ሲረሱ ነው ። አካልና ጥላ እንደማይለያዩ ሰውና ሞትም አብረው ይኖራሉ ። እግዚአብሔርን ስንከተል በጎነት ይከተለናል ። ከምትወደው ጋር ሺህ ዓመት ብትኖር እንኳ ከትልቅ መጽሐፍ ገና አንድ ገጽ ማንበብህ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

እስከ ሽምግልና የሚከተልህ ወጣትነት ነው ። መርዛም ነገርን ማስወገድ ከተሠራበት በላይ ወጪ ያስወጣል ። ክፉዎች ቢሞቱም ክፋታቸው ሲያዋራን ይኖራል ። እጅግ ስስ መሆንህን ለማወቅ ከፈለግህ ማወቂያው የሰው ጠባይ ሲከብድህ ነው ። መወለድን ከተቀበልህ መሞትንም መቀበል አለብህ ። 

ወዳጄ ሆይ !

ካልሞትህ በቀር አትቁም ። መሮጥ ካልቻልህ መንፏቀቅም ጉዞ ነው ። ለበጎ ነገር ምቹ ጊዜ አትፈልግ ፣ ሰዓቱ አሁን ነው ። በዛሬው ዘመን ሰዎች በቃላቸው እብለት ፣ በሰውነታቸው ክፋት ተለማምደዋልና አንተ ግን በቃልህ እውነተኛ ፣ በኑሮህ ደገኛ ሁን ። ጥላቻ ከሚመርዝህ ፍቅር ቢያስጠቃህ ይሻላል ። ጠላትህ ከነጠቀህ ይልቅ በችግርህ ሰዓት ወዳጅህ አለመድረሱ ቆይቶ ይቆጫል ። በየትኛውም አገር የሚፈጸም ወንጀል ፍትሕን ዝቅ አድርጓልና ሊወገዝ ይገባዋል ። መጀመር መጨረስ ባይሆንም ለመጨረስ ግን አንድ ደረጃ መቀነስ ነው ። ለመብት መታገል መልካም ነው ፣ እውነተኛ ነጻነት ለማግኘት ግን ማደግ ወሳኝ ነው ። 

ወዳጄ ሆይ !

አንተ የምትጠላውን ሰው እግዚአብሔር እንደሚወደው አስብ ። ውድቀትህ የእግዚአብሔርን ጸጋ የምታይበት አደባባይ ነው ። ለበዛው ስህተታችን ጸጋው ባይበዛልን እንደ ሰዶም በሆንን ገሞራንም በመሰልን ነበር ። ብርሃን ጨለማን ይገፋል እንጂ እስከወዲያኛው አያርቀውም ፣ የአሁን ጸሎትህ ቢሰማም ሌላ ጥያቄ እንደሚመጣ እወቅ ። ጥላቻን በጥላቻ ለማጥፋት ስንነሣ በመተላለቅ እግዚአብሔር የሰጠንን ዕድሜ እናሳጥራለን ። ያለማወቃቸውን የሚያውቁ አላዋቂዎች ምሁራን ናቸው ። አላዋቂነታቸውን እንደ እውቀት የሚያዩ ሁሉንም ወንጀል የሚፈጽሙ ናቸው ። እውቀት በዓለም ላይ ያለኸው አንተ ብቻ አይደለህም በማለት ሌላውን አክብር ትልሃለች ። ድንቁርና ደግሞ በዓለም ላይ ያለኸው አንተ ብቻ ነህ በማለት ከፍ ያሉትን አዋርድ ትልሃለች ። 

ወዳጄ ሆይ !

በፍቅር አውሬንም ማልመድ ይቻላል ። ዓለም የጋራ ቤታችን መሆኗን ተረድተን ተደማምጠን መኖር አለብን ። ይቅርታ እንቅልፍ እንቢ ሲለን የምንመርጠው ሐቅ ሳይሆን የሁልጊዜ ጠባያችን መሆን ይገባዋል ። ዲያብሎስ ይህ ሁሉ የሚደክመው ብቻውን ላለ መኰነን ነው ፣ አንተስ ብቻህን መጽደቅ ቅር ብሎህ ያውቃል  ምሽቱ የበራችውን ፀሐይ ቢሸኝም የተሰወሩ ከዋክብትን ይገልጣል ፣ ችግርህም የማታውቃቸውን ደጎች ያሳይሃል ። ሰው በአንድ ቀን ንግግርና ትውውቅ አይመዘንም ። ቀኖች እየገፉ ሲመጡ የተደበቁ አመሎች ብቅ ማለት ይጀምራሉ።

ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምህን ስጠን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን

ኅዳር 15 ቀን 2013 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ