የትምህርቱ ርዕስ | ሰላም

 

ሰላም ሳለ ርካሽ ፣ ከሄደ በኋላ ግን በውድ ዋጋ እንኳ የማይገኝ ነው ። ሰላም ካለ ትንሹ ብዙ ነው ። ያለ ሰላም ጮማ ከሚቆርጡ ፣ በሰላም ጥሬ የሚቆረጥሙ ወዝ አላቸው ። ሰላም ፊትን የሚያበራ ፣ ጉልበትን የሚያጸና ፣ ነገን ብሩህ የሚያደርግ ነው ። ያለ ሰላም ማቀድ አይቻልም ። ገበሬ እንዲያርስ ፣ ተማሪ እንዲማር ፣ ኀዘነተኛ ኀዘኑን እንዲወጣ ሰላም አስፈላጊ ነው ። ሕፃናት አዲስ እንግዶች ናቸውና ሽማግሌዎችም ይህችን ዓለም ተሰናባቾች ናቸውና ሰላም ይገባቸዋል ። የሚያድገው ልጅ ሰባራ ፣ የሚሞተው አረጋዊ ኀዘነተኛ እንዳይሆኑ ሰላም አስፈላጊ ነው ። ያለ ሰላም ታዳጊ አገራት ሊያድጉ ፣ ያደጉትም በከፍታቸው ሊቆዩ አይችሉም ። የዓለማችን ከፍተኛ ሀብት የሚባክነው ለሰላምና ለደኅንነት ነው ። እግዚአብሔር የሰጠን በረከት በቂ ነው ፣ ለጠብ ግን የሚበቃ አይደለም ። 

ሰላም ለኢኮኖሚ ዕድገት አስፈላጊ ነው ። ባለ ሀብቶች ወደ ልማት የሚገቡት ፣ ምሁራን በአገራቸው ረግተው የሚቀመጡት ሰላም ሲኖር ነው ። ሰላም ካለ ከከፍታ ወደ ከፍታ እንራመዳለን ፤ ሰላም ከሌለን ግን ምንም ነገር አይኖረንም ። እንግዳ ተቀባዮቹ ስደተኛ ፣ ሰጪዎቹ ተመጽዋች የሚሆኑት ሰላም በሌለ ጊዜ ነው ። ሰላም ዘር ነው ፣ ሰላምን ዘርተን ሰላምን እንድናጭድ አንደበታችንን መጠበቅ አለብን ። ሰላም ዋጋ ከፍሎልን ከእኛ ጋር አይሆንም ፣ ብዙ የሚፈልጉት አሉና ኩሩ ነው ። ሰላምን ዋጋ ከፍሎ መያዝ የእኛ ፈንታ ነው ። መጽሐፍ ሰላምን በሚመለከት “ሰላምን ይሻ ይከተለውም” ይላል ። 1ጴጥ. 3፡11። ሰላም ፍላጎት ይፈልጋል ፣ ቀጥሎ ወደሚወስደን መከተል ይጠይቃል ። ሰላም ሲመራን እሺ ብለን መሄድ እንጂ ልምራህ ማለት ሰላምን አያመጣም ። 

በሽተኛ ጠያቂ ፣ ሟች ቀባሪ  ፣ አገር ተረካቢ ፣ ሴቶች ባል ፣ ነጋዴ ትርፍ ፣ መንግሥት ክብር ፣ ካህን ሰሚ ፣ ሰባኪ አድማጭ እንዲያገኙ ሰላም አስፈላጊ ነው ። አገር ጎብኚዎች እንዲዘዋወሩ ፣ በዓለም መንግሥታት ፊት ክብር ለማግኘት ሰላም ያስፈልጋል ። ሰላም የሌላቸው ሕዝቦች ለጊዜው ገላጋይ ያገኛሉ ፣ ሲቆይ ግን ሁሉም ይጠላቸዋል ። በመጨረሻ ጥቅማችንን እየነኩ ነው ተብለው ጥፋት ይፈረድባቸዋል ። ሰላም ከሌለበት አገር የሚሄዱ ዜጎች በሌላው አገርና ሕዝብ ክብር የላቸውም ። የትም ስንሄድ የምንጠራው በአገራችን ስም ነውና የአገር ሰላም ወሳኝ ነው ። ሰላም በጋራ የምንገነባው እንጂ በጥቂቶች ጥረት ብቻ የሚገኝ አይደለም ። አንዱ ሲያሸማግል ሌላው የሚያጋግል ከሆነ ሰላም አይገኝም ። የግል ሰላም ማጣት ፣ የጎረቤት ሰላም ማጣትን ይወልዳል ። የታወከ ጎረቤት የታወከ መንደርን ፣ የታወከ መንደርም የታወከ አገርን ይፈጥራል ። ሁከትና እሳት ትንሽ ናቸው ፣ ሲቆዩ ግን አገሩን ያዳርሱታል ። ሰላምን በግላችን እንለማመድ ፣ ቤታችንን ሰላም እያደረግን ፣ አገሩን ሰላም ለማድረግ እንጣር ። በዓለም ላይ ትልቁ ውሸታም ከሁከት አተረፍኩ ፣ ከሰላም ከሰርሁ የሚል ነው ። ሰላምን እንጠብቃት ፣ ሰላም ትጠብቀናለች ።

ልጆችዋ እየተጋደሉ የምትተኛ እናት የለችምና ቤተ ክርስቲያን ለሰላም ልትነሣሣ ይገባታል።

ሰላማዊ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ሰላምህን ይስጠን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን 

ሐምሌ 26 ቀን 2013 ዓ.ም.

እውነት 6

ለልባችሁ የቀረላችሁን አሳብ እስቲ ግለጡ ። እግዚአብሔር ሰላሙን ይስጣችሁ !

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ

አዳዲስ መጻሕፍት

ትርጉሙ:- ቀይ ዕንቈ

ለምድራችንና ለአገልግሎታችን በረከት የሆነ መጽሐፍ
የመጀመሪያ እትም ጥቅምት 2016 ዓ.ም

1ኛ ጢሞቴዎስ ትርጓሜ – ክፍል አንድ

የመጀመሪያ እትም ሐምሌ 2013 ዓ.ም

ምክር አዘል መጽሐፍ

የመጀመሪያ እትም