የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰማያዊ ወግ /1

የምእመን ቃል

ጌታ ሆይ ፣ ወዳንተ መገስገስ ወደ ምሥራቅ ፣ ወደ ፀሐይ መውጫ መጓዝ ነው ። በአሳቤ ፣ በቃሌ ፣ በተግባሬ ወደማትጠልቀው ፀሐይ ወዳንተ መገስገስ እፈልጋለሁ ። አንተን የሚከተል ጨለማ አያገኘውም ። ተስፋ መቍረጥና ትካዜ ለዘወትር አይከቡትም ። ከሞት ባሻገር ያለው ዓለም ይታየዋል ። የሚረግጠው ይታየው ዘንድ ቃልህ በእግር ላይ እንደ ታሠረ ብርሃን ይሆንለታል ። ህልውናህ በአናቱ ላይ እንደ ተሰቀለ ፋና ያበራለታል ። የሚታየውን ዓለም እንደማይታይ ቆጥሮ ይንቀዋል ። የማይታየውን ዓለም በእምነት መነጽር እያየ ያከብረዋል ። አዎ ጌታዬ አንተን የሚከተል ጨለማ ሞት አያስፈራውም ።

በቀኙ ጓደኞች ፣ በግራው ዘመዶች በመታጣታቸው አይጨነቅም ። የዘላለሙን መንገድ ሲጀምር ፣ ከመቃብር ወዲያ ማንም አይከተለውምና ፣ ለጊዜው ሰው አጣሁ ብሎ አይሸበርም ። ለልብ የምታበራ እውነተኛው የሕይወት ብርሃን የእግዚአብሔር ልጅ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ ይቅር በለኝ ። ብርሃን ሳለልኝ ጨለማን ፣ መስክ ሳለልኝ ዋሻን መርጫለሁና በመልካም አስበኝ ። ሰው ፣ “እርሱ ይህን ይመስላል” እያለ የራሱን ሥዕል እየሳለ ይጠላኛል ። አያሌው ወገን ክፉ ይለኛል ። አንተ ግን በጥሩ ዓይኖችህ ተመልከተኝ ።

የመድኅን ቃል

ልጄ ሆይ ፣ አንተ ወደ እኔ አንድ እርምጃ ስትመጣ እኔ ወዳንተ ሁለት እርምጃ እመጣለሁ ። ጀርባህን ለእኔ በሰጠህበት ወራት እንደ ጨለመብህ አውቃለሁ ። የእኔን እንጀራ እየበላህ ስትክደኝ እኔ ግን ይህችን የንስሐ ቀን እጠብቅልህ ነበር ። አሳብህ ብትን ፣ ቃልህ ጭንቁር ፣ ተግባርህ ጠማማ ሁኖ ብዙ ዘመን አስቸግረኸኛል ። ከፈለከኝ በላይ ልፈልግህ ከሰማይ ወደ ምድር ወርጃለሁ ።

ኑሮው ፣ ሰዉ ፣ አገሩ ፣ አመራሩ ፣ ነገ አልታይ ብሎህ ስትጨነቅ አይሃለሁ ። ተስፋ ከሰው ፣ አለኝታም ከምድር የለም ብዬ በመምህራን የነገርኩህን ለምን ትረሳለህ  ተስፋ ማለት ተስፋ በማይደረግበት ዘመን ብርሃን ማየት ነው ። ተስፋ የአሁኑ ሳይሆን የሚመጣው ፣ የሚታየው ሳይሆን ወደ ፊት የሚገለጠው ነው ። ተስፋህ እኔ ነኝና አትፍራ ።

የመደነቃቀፍ ጉዞህ ፣ የማመንታት ፍቅርህ ፣ የማሳከር ቃልህ ይበቃ ዘንድ ቃሌን አፍቃሪ ሁን ። ያንተ ደስታ ለብዙዎች ደስታ ነውና በእኔ ብቻ ደስ ይበልህ ። ይህን ጠፊ ዓለም ላፈቀሩ እዘንላቸው ። ገንዘብ እንጂ ዕድሜን መቍጠር አልቻሉምና በየዕለቱ በሞት በትር የሚሰበሩትን ወጣቶች አስብ ። የትላንት ጌቶች የዛሬ ከርታቶች ሁነዋል ። ምድር አይበቃንም ብለው በሰማይ ይበርሩ የነበሩ ፣ የድሆችን ጎጆ ቀምተው የፎከሩ ዛሬ የሉም ። ባንተ ጊዜ ሳይሆን በራሴ ጊዜ እፈርዳለሁ ። ይህን ሁሉ ስታይ “እሰይ” አትበል ። ይልቅስ ለራስህ ፍራ እንጂ ።

በወረተኛው ዘመን ጓደኞች የሚቆሙት ከእንካ ጋር ነው ። ዘመዶችም ሲገናኙ መወቃቀስ ፣ ሲለያዩ መረሳሳት ያጠቃቸዋል ። ልብህ በከዳህ ዘመን የልብህ ወዳጅ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝና እኔን ብቻ ተከተል ። ዓይኖቼ እንደ ሰው ፣ ሚዛኔም እንደ ምድር ዳኞች አይደለምና አትፍራ ። አንተን ከጥፋትህ ለይቼ የምወድህ ፣ ላነጻህም ሥልጣን ያለኝ እኔ ብቻ ነኝ ። ልጄ ሆይ አሁንም አነጋግረኝ ።

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ