የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰማያዊ ወግ /10

ምእመኑ ልቡን በጌታው ፊት አፈሰሰ፡-

ጌታ ሆይ! በተራ ሰውነት ስኖር ትልቅ ሰው መባል ያምረኛል ፤ ደግሞ መዋከብ ከበዛበት ጌትነት ውስጥ ነጻ መሆን ይናፍቀኛል ። በሰለጠነው ከተማ ስኖር ገጠሩ በዓይኔ ላይ ያልፋል ። ገጠሩን ሳገኘው የከተማው ብልጭልጭ ይታወሰኛል። የምፈልገውን አላውቅም ። የፈለኩትን ሳገኝ አልረካም ። ጌታዬ ሆይ ! ስሙን ሳልጠራው የምፈልገው ያንተ መሆንን ነው ። ውስጣዊ ጥማት አሰቃየኝ። ጥረቶቼን አይቼ ለመደሰት ሞከርሁ ፤ ድካሙ ነበረ ፣ እርካታው ግን ከዳ ። ትልቅ ሥራ ትልቅ ዕረፍት አልሰጠኝም ። የከወንኩት ሲካብም ሲናድም ስሜቴ የማይጨበጥ ነው ። ብዙ አገልጋዮችን ተመኘሁ ፣ ደግሜ ሰውን በማሽን ለመለወጥ ፈለግሁ ። ብዙ ወዳጆችን አሰባሰብሁ ፣ ደግሞም መካነ እንስሳትን ናፈቅሁ ። የመላእክት ወዳጅነት ያምረኛል ፣ ከሰዎች ጋር ጭቃ ማላቆጥ ደግሞ እወዳለሁ ። የጠቀለልሁትን ሳልጎርስ ሌላ እመኛለሁ ፤ ያኘኩትን ሳልውጥ ረሀብ ያሰጋኛል ። የደረሱልኝን ሰዎች ትቼ ባልደረሱልኝ ሰዎች አዘንሁ ።

ጌታዬ ሆይ ! የቀረበኝን እውነት ገፍቼ ያልቀረበኝን ጥርጣሬ እጣራለሁ ። ስነሣ የጠሉኝ ፣ ስወድቅም ይጠሉኛል ። ለዓለም የቱ እንደሚሻል አላውቅም ። አንተን ለመስማት መጥቼ እኔ አወራለሁ ። ትዕግሥትህና ፈገግታህ ፣ ሳትንቅ መስማትህ ፣ አለማወቄን አለመታዘብህ ይደንቀኛል ። በሁኔታዎች ቁጥጥር ሥር መሆንን አልሻም ። ሁልጊዜ ግን የምጓዘው ራሴን ወደማስርበት አጥር ውስጥ ነው ። ትላንት የተከላከሉልኝ ዛሬ አሳልፈው ይሰጡኛል ። የሞሉ ማድጋዎች ባዶ ሲሆኑ ፣ ባዶ ማድጋዎች ደግሞ ሙሉ ሲሆኑ አያለሁ ። ከምግባር የሚወድቁትና ወደ ምግባር የሚወጡት የገደሉ መሐል ላይ ይገናኛሉ ፣ አንዱ አንዱን ዝም ይለዋል ። ስሜቴን የሚቀሰቅስ አምልኮ ሳይሆን ያንተን ክንድ የሚያንቀሳቅስ ቍርጥ ልመና ስጠኝ ። ወቅቱን ከመፍራት አንተን መፍራት ይሁንልኝ ።

መሐሪዬ ሆይ ! ከሞቱት ጋር ተወዳጅቼ ያለፉትን ክፉዎች ደግ ናቸው ብዬ ካሉት ጋር ከመጣላት ጠብቀኝ ። ለመላው ዓለም ራእይ አለኝ ብዬ ላንድ ሰው የማልበቃ መሆኔ ያሳዝነኛል ። የተሰጠኝን ነገር ያልተሰጠኝ ነገር ሲሸፍንብኝ ልቤን አስተካክለው ። ከአደጋ ፣ ከታቀደ የጥፋት ቀን ያመለጥኩብህ ሆይ ወዳንተ አቅርበህ ከሞት አድነኝ ።

መድኅን ክርስቶስ መለሰ፡-

ልጄ ሆይ ! መሄድ ያለበት የሄደው አንተን እንዳያጠፋህ ነው ። ያለህ ነገር የሚጸናው ስለሌለህ ነገር ማጉረምረም ስታቆም ነው ። መልእክትህ ዋጋ የሚኖረው ለተናገርከው ስትታመን ነው ። ክረምቱ ምቾት ባይኖረውም የበጋው ጥጋብ ግን እርሱ ነው ። የሰው እጅ የሌለበትን የእኔን በረከት ትሻለህ ፣ እኔ ያለ ሰውም ፣ በሰውም እሠራለሁ ። ያለ ሰው የምሠራልህ ኃይሌን እንድታውቅ ፣ በሰው የምሠራልህ የሰውን ዋጋ እንድትገነዘብ ነው ። በቅዱሳን ሕይወት የሠራሁበትን መንገድ አስታውስ ። በርግብ ሰላምን አበስራለሁ ፣ በቁራም ነቢይን እመግባለሁ ። እኔ ሳዝዝ አህያ ሰነፍ ሰውን ትገሥጻለች ፣ የቢታንያ ድንጋዮችም ይዘምራሉ ። ይህች ቀን እኔ የሠራኋት ቀን ናትና መጀመሪያ በእርስዋ ደስ ይበልህ ። መኖርህን እረስተህ ስለ መኖሪያህ ታጉረመርማለህ ።

ልጄ ሆይ ! ራስህን ብዙ ትለዋለህ ፣ ችሎታህን ተማምነህ ወጥተህ አፍረህ ስትመለስ ትሳቀቃለህ ። ያለ እኔ በለስላሳ ጎዳና ከመሄድ ከእኔ ጋር ወጥመድ ባለበት መንገድ መሄድ ይሻላል ። የሕይወትህን መነሻ ፣ የሕይወትህን ማዕከል ፣ የሕይወትህን ግብ እነዚህን ሦስቱን አስቀድመህ ለይ ። ሊተባበሩህ የወጡትን ሊገድሉህ ከወጡት እኩል በአንድ ዓይን አትመልከት ። ይህ ዓለም ጽድቅም ኃጢአትም አለበት ፤ የሚመጣው ዓለም ግን ጽድቅ ብቻ የሰፈነበት ዓለም ነው ። እንዴት መኖር እንዳለብህ የምታውቀው ለምንና ለማን እንደምትኖር ስታውቅ ነው ። የሕይወትህን ክፍተት ጥረትም ጉልበትም አይሞላውምና መንገድህን ከእኔ ጋር አሰማምር ። ካንተ ልብ ይልቅ ማዕበል ለእኔ ይታዘዛልና ከሞገድ ይልቅ ልብህን ሥጋ ። የሥራዬ ጠባይ ነው እያልህ ኃጢአትን አታቆንጅ ። ሁሉ በእኔ እንደሚቻል እመን ። የሠራህልኝ ባይኖር በሠራሁልህ አስቀድመህ ተደሰት ። በፊትህ የሚሄድ መልአክ ልኬአለሁና የሚመራኝ የለም አትበል ። ፍቅርህ ያላቀረባቸውን ተዋቸው ። በማያስፈልግ ቦታ ጊዜህን አታባክን ። ፈጥኖ የመጣ ፈጥኖ ይሄዳልና ሁሉም ነገር ዛሬ ካልሆነ አትበል ።

ልጄ ሆይ ! የሚነድድ መብራት አስቀድሞ ያስለቅሳል ። ከመከራ በኋላም ዘላቂ ትምህርት ይገኛል ። ሕይወትን ትምህርት ቤት አድርጌ የማስተምርህ እኔ አምላክህ ነኝ ። በጥበብ ተባረክ ።

ሰማያዊ ወግ /10

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተፃፈ ሰኔ 3 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ