ምእመኑ በጽድቅ ለሚሰማው ጌታ ተናገረ፡-
ጌታ ሆይ ! አንተ ካልሰጠኸው አንድ ቃል የሚጽፍ ፣ አንተ ካልረዳኸው የወደቀን የሚያነሣ ፣ አንተ ካልቀባኸው ተናግሮ የሚያጽናና ፣ አንተ ካልባረከው ሰባራን የሚጠግን ፣ አንተ ልቡን ካላረጠብከው ፍቅርን የሚሰጥ ፣ አንተ ካላረጋጋኸው የዘመንን ማዕበል የሚያሸንፍ ፣ አንተ ሁን ካላልከው ሰው መሆንን የሚያገኝ ማንም የለም ። ዓለም ተበጥብጣ ልትበጠብጠኝ ስትሻ ፣ ምን እንደሚፈልጉ የማያውቁ የሰው ልጆች አቅሌን ሊነሡኝ ሲነሣሡ ፣ የይሁዳ መሳም ጥርስ ሁኖ ሲያደማኝ ፣ የጴጥሮስ ክዳት የዓርቡን ሌሊት ሲያረዝምብኝ ፣ የቀድሞ ጉልበቴን ሳጣው ፣ መልኬን በፎቶ ስፈልገው ፣ ልቤን ማመን አቅቶኝ ስፈራው ፣ መሐላዬን ሳፈርስ ፣ ወስነው የመጡብኝን ወስኜ ማምለጥ ሲያቅተኝ ፣ በጥቅስ የምወደው ቃልህን ለመኖር ሲመርረኝ አንተ ግን ለእኔ መልካም ነህ !!
መሪውን ልምራህ ፣ ምሁሩን ላስተምርህ ስል ፣ የረዳኝን ሰው በችግሩ ስሳለቅ ፣ መልካሙን ሰው “ምስኪን” ብዬ ስጠራ ፣ አንተ ግን ከዚህ ማንነቴ ልታወጣኝ ትታገሠኛለህ ። በድጡ ላይ ስወድቅ ዝም ያሉኝ ፣ በማጡ ስነከር ከዚህ በኋላ አይወጣም ብለው ይስቁብኛል ። ነውሬን ክብሬ አድርጌ ስኖር ፣ ወደ ግብጽ ለመመለስም ከነዓን ለመድረስም አካፋይ መንገድ ላይ ስቆም አንተ ግን በርታ ትለኛለህ ። አንተን ለመውደድ ብዙ ውለታህን ለመቍጠር እነሣለሁ ፣ አንተ ግን ሳትቆጥር ወደኸኛል ። ለጥላቻ አቅም እንዳላስፈለገኝ ፣ ለፍቅር ግን አቅም ያሻኛል ። ዓለም ስም መስጠት ጠባይዋ ነው ። ሎቱ ስብሐት ላንተም ብዙ ስም ሰጥታሃለች ። በሬን ስዘጋ ጋኔን ጎታች ፣ ሰውን ስቀርብ ክብር የለሽ ትለኛለች ። ለሰው የኖርኩትን ላንተ ብኖር ቍጥሬ ከቅዱሳን አበው ነበር ። አማኑኤል ሆይ ከብርሃን በሚፈጥነው ረድኤትህ ድረስልኝ ።
የምሕረት አምላክም መለሰ፡-
ልጄ ሆይ !
ሳትታክት መለመን በእኔ ዘንድ እንደ ሰማዕትነት ይቆጠራል ፣ በሰው ዘንድ ጨቅጫቃ ያሰኛል ። ኃጢአት ሲስማማህ እንጂ ከቆረቆረህ የፈውስ ዋዜማ ላይ ነህ ። ማስተዋል መንገድን ያቀናል ፣ መጥኖ መናገር ያስከብራል ። መጨረሻውን ኃጢአት ያደረገ በደለኛ ይባላል ፣ መጨረሻውን ጽድቅ ያደረገ ኃጥእ ግን ጻድቅ ይሰኛል ። ችግሮች ወደ እኔ የምትጮህባቸው ርእሶች ናቸው ፣ ትልቁ ችግር ከእኔ መራቅ ነው ። ባልመጣው በረከት የመጡትን በረከቶች አትርሳቸው ። ላያልቅ የጀመረ ፈተና የለም ። እኔንም አልፎ ሊያጠፋህ የሚሻ ኃይለኛ አይገኝም ። ከሰዎች ላይ ጋኔን ከማውጣት ክፉ ምኞታቸውን ማውጣት ይከብዳል ። ሰው ከክፋቱ የበለጠ ጠላት የለውም ። ለውስጥ ሰዎች ሸካራ ለውጭ ሰዎች ግን ለስላሳ አትሁን ።
ልጄ ሆይ !
የሹመት ሞቱ ሺህ ነውና አትውደደው ። ስሜትህን መቆጣጠር አቅቶህም ሕዝብን የሚዋርድ ቃል አትናገር ። ያንተ ድርሻ መናገር ብቻ ነውና ለምን አልተቀበሉም ብለህ አትበሳጭ ። እኔ ለፈጠርኩት ዓለም ከእኔ በላይ አሳቢ አትሁን ። መሳትህ ለብዙዎች መሳት በር ይከፍታልና ለሚያዩህ ስትል በአቋምህ ጽና ። የሰውን አንደበት መቋቋም ከቻልህ ሌላው ፈተና ቀላል መሆኑን ተረዳ ። የሌላቸውን ጽድቅ ባንተ ላይ ይፈልጋሉና የሚሰድቡህን አትስማቸው ። የሚያምርህን ትተህ የሚያምርብህን ያዝ ። ሁሉ ከእኔ ነውና ሁሉን ለእኔ ክብር አድርግ ።
ልጄ ሆይ ! በተለዋዋጭ ዓለም ላይ ነህና በሚለዋወጡ ነገሮች አትደንግጥ ። እኔን ማየት ስትጀምር የሰዎችን ይሁንታ አታስስም ። የእኔ በር ክፍት ነውና የተዘጋውን የሰዎች በር አታንኳኳ ። በመሆን እንጂ በስልት መልካም አትምሰል ። ሁልጊዜ የምወድህ እኔ ኢየሱስ ክርስቶስ ነኝና ደስ ይበልህ ።
አሜን!!!
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ተፃፈ ሐምሌ 28 ቀን 2015 ዓ.ም.