መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰማያዊ ወግ » ሰማያዊ ወግ -12

የትምህርቱ ርዕስ | ሰማያዊ ወግ -12

ምእመኑ በእንባ ተናገረ፡-

ጌታ ሆይ ! የሰማሁት የዓለም ነገር ቢያውከኝም ፣ መልሼ ለመስማት እጣደፋለሁ ። የሰማሁት ቃልህ ቢያስደስተኝም ተመልሶ ለመስማት ዳተኛ እሆናለሁ ። ሕይወት ለሚገኝበት ነገር እስከ መቼ እዘገያለሁ ( ለቃልህ ተኝቼ ለሣንቲም እነቃለሁ ። የበረሃው ጉዞ ፣ የጥማቱ ጅራፍ ልክ የለውም ። የሚያረካ ነገር ከራሴም ከሰውም ፣ ከሁኔታዎች አጣሁ ። የእርካታ አገርዋ ወዴት ነው ( ግልጹን መልእክት ፍቅርን መኖር ትቼ ፣ የተሰወረውን እቆፍራለሁ ። ቃልህን ለለውጥ ሳይሆን ለአእምሮ እብጠት እፈልገዋለሁ ። የጠባዬን አንካሳነት እኔው ራሴ አውቀዋለሁ ፣ አሁን በራድ ቀጥሎ ሙቅ መሆኔን ፣ ያመሰገንኩትን ለመራገም ጀምበሩ ሳይጠልቅ መጣደፌን ፣ ለቀረቡኝ የማይፈታ ቅኔ መሆኔን ፣ ፍቅሬን ከጥርጣሬ ፣ ቸርነቴን ከብድር መቀላቀሌን አውቀዋለሁ ። ማወቅ ግማሽ መፍትሔ ቢሆንም ሙሉ መለወጥ ግን አልሆነልኝም ። ቀኖቼን ለጥፋት ሳይሆን ላንተ ክብር ብቻ የማውለው መቼ ነው ( ራሴ ጠይቄ ራሴ መልስ ለመስጠት የምጓዝበት ርቀት አቅሌን እንዳያሳጣኝ እፈራለሁ ። ምክንያቱን ባውቀውም በሰዎች ዝለት እፈርዳለሁ ። ራሴን ሳስብ ግን “የተሰማኝ ነው ምንም ማድረግ አልችልም” ብዬ ይቅርታ እሰጠዋለሁ ። ጌታ ሆይ ጥግ ያጣውን ሕይወቴን ወደ ኋላ ለመመለስም ወደ ፊት ለመድረስም መሐል ላይ ያለውን ክርስትናዬን የምትፈውሰው መቼ ነው (

ሠሪዬ ሆይ ስላንተ ብዙ ሰምቻለሁ ። የሚወዱህ ተሰባስበው ሲቀኙልህ አድምጫለሁ ። መመሪያ የሚሰጥ ሳይሆን መሪ ነው ይሉሃል ። ራሱን ሰጥቶ ራሳችሁን ስጡኝ ባይ ነው ተብለሃል ። የጠበቅሁትን ሕይወታችሁን ስጡኝ ይላል ብለው ይናገሩልሃል ። ሣሩን እያዩ ገደል ገቡ ፣ ኑሮን ብለው ሕይወትን አጡ ብለህ ማዘንህን ሁሉ ሰምቷል ። ተፈጥሮዬ ነው አትበሉ ፣ ተፈጥሮችሁ ጽድቅ ነው ፣ አቅም የለኝም አትበሉ አቅማችሁ እኔ ነኝ ብለህ ውዳቂዎችን እንዳነጋገርህ መረጃ ወጥቷል ። በማዘን የምታስተምር ፣ በዜማ የምትመራ ፣ በፍቅር የምትቀርብ ፣ በዘመን የማትጨልም ፣ ተመኝተው የማያጡህ ነህ ። አንተ የወይን ጭማቂ ሆይ ጠጥቼ የምረካህ መቼ ነው ( አንተ ዝርግፍ ወርቅ ሆይ አጊጬህ የምደምቅብህ መቼ ነው ( የጆሮዬ የምሥራች አንተ ነህ ፣ ጆሮ ቆራጩ ዓለም ከልጅነት ጀምሮ ሲያሸብረኝ ይኖራል ። አደጋውን ስሰማ የሚራመደው እግሬ ይወላከፋል ፣ የሚናገረው አንደበቴ ይተሳሰራል ፣ የሚመታው ልቤ ሥራ ላቁም ይላል ። አቧራው ጠርቶ ባሻገር ለማየት ፣ ጉሙ ተገፎ ነገን ለመመልከት እፈልጋለሁ ። የምደርስበት እያሳሰበኝ ለራሴ አለቅሳለሁ ። እንዳንለያይ እያልኩኝ የመንገዱን አስቸጋሪነት እፈራለሁ ። እንደ ገደል ማሚቱ የገዛ ድምፄ እየተመለሰ ያውከኛል ፣ ወልድ ሆይ ስምህ መድኃኒት ይሁነኝ !

የምሕረት ድምፅ ከሰማይ ተሰማ!

ልጄ ሆይ!

የጠላት ሴራ ፣ የፈሪዎች ዛቻ ፣ የተቃዋሚዎች ክስ ፣ የአድር ባዮች ሽሙጥ ፣ የከንቱዎች ሐሜት ፣ የአራዊት ጥርስ ፣ የመንገደኛው ትዝብት ፣ የሚና የለሾች ፍርደ ገምድልነት እንዳደከመህ አውቃለሁ ። መተማመን የሌለበት ውሎ ፣ እረኛና በግ የተፋጠጡበት ፣ አባትና ልጅ በብልጠት የሚያወሩበት ፣ ባልና ሚስት ስለ ገንዘብ ብለው የሚተቃቀፉበት ዓለም እንዳዛለህ ፊትህ ምስክር ነው ። ኢየሩሳሌም ልዋል እያልህ ኢያሪኮ መውረድህ ፣ የሞተልህን ትተህ ከሚገድሉህን ወንበዴዎች መንደር መግባትህን አላስተዋልህም ። ሦስቱ ፈሳሾችህ ያሳዝኑኛል፡- እንባህን ፣ ላብህና ደምህ ሲፈስስ አየዋለሁ ። እንባህ እሳት ነው ፣ ላብህ ምግብ ጠያቂ ነው ፣ ደምህ ይግባኝ ባይ ነው ። ታላቁን ሐኪም እኔን ይዘህ ከቍስልህ ጋር እስከ መቼ ትኖራለህ ( የችግርህን ወራጅ እንጂ ምንጩን እንድደፍን አልፈቀድህልኝም ። ልጄ ሆይ ! ከክርክሩ መልስ እኔን አግኘኝ ። የተቀደሰውን ጉባዔ ተቀላቀል ። የሞት ድምፅ በቃሌ ይገሠጻል ፣ ከውድነቱ የተነሣ ብርና ወርቅ ለትእዛዜ ተመን አይሆኑም ። የፍቅር ድምፅ ነውና ከሞት መንገድ ይመልሳል ፣ የሥልጣን ቃል ነውና ሰማይና ምድርን ያዝዛል ። እባክህ ልጄ ሆይ ቃሌን ተተገን ። በመመረር ከቀነስከው የጨመርከው ይበዛል ፣ ስለ ፀሐይ መጥለቅ ስታዝን ከዋክብትም ይሰወሩብሃል ። ልጄ ሆይ ! ባልገባህ ዓለም ላይ ነህና ምስጋና ብቻ አቅርብ ። ሕብር ምስጋና ፣ የተነባበረ ውዳሴም እኔን አይገልጠኝም ። እንኳን ምሬትን የቀዘቀዘ ምስጋናን አልወድም ። ላልፈጠርከው ሕይወትህ በጣም አትዘንለት ። ካንተ ይልቅ ላንተ ቅርቡ እኔ ነኝ ።

ልጄ ወዳጄ ሆይ !

የመንገድህ ዋስትና እኔ ነኝ ። በበረሃ ልጥልህ ከቤት አላወጣሁህም ። ስጸዳ እመጣለሁ ብለህ ከቤቴ አትራቅ ። ካልሞትህ በቀር ከቤቴ አትቅር ። ጥያቄዎችህን ሳይሆን እኔን አስብ ። የሁሉም ነገር መልስ በዓለም ላይ የለም ። የሁሉም ነገር መልስ ግን እኔ ነኝ ። አንድ ቃል ልንገርህ፡- ዋጋ ያለህ ፍጥረቴ ነህ ። በዚህ ቃል ተጽናና !

ምእመኑን እንዲህ እያለ ተመለሰ፡- የሰማርያ ውኃ ቢቀዱት ያልቃል ፣ ካልሄዱበት አይመጣም ፣ ጉድጓድ ነውና ። ምንጩ ክርስቶስ ግን ካለሁበት ደረሰ ። ንቃቃቴን በቃሉ አረሰረሰ ። የምትወዱት ውብ ነህ በሉት ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 4 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ