ምእመኑ ቃተተ …
ጌታዬ ሆይ !
ሃይማኖቴን ሰዎች ለሚጠይቁኝ ጥያቄ መልስ ለመስጠት እንጂ ለመዳንና ለማረፍ አልያዝሁትም ። እየጸለይሁ እፈራለሁ ፣ አንተንና ራሴን አወዳድራለሁ ። ሥጋዬ እንዳይከፋው አንተን ማሳዘን እመርጣለሁ ። የእኔ መድኃኔ ዓለም ብልህም የእኔ አንተ ብቻ አይደለህም ። አንተንም የሚጠፋውን ዓለምም በልቤ ጋብዤአለሁ ። ነገር መቋጨት አልችልም ። ቂም ብርሃኔን አጨልሞታል ፣ በቀል ያንተን ሥልጣንና ፈራጅነት እንድረሳ አድርጎኛል ።
አምላኬ ሆይ !
የተሻለ ሕይወት ያጽናናኛል ፣ የተለወጠ ሕይወትን ገና አልናፍቅም ። ለራሴ ዋጋ እየሰጠሁ ከትላንቱ እሻላለሁ እላለሁ ። ምናለ ጌታዬ አንተን እስክመስል ምጥ ቢይዘኝ ! የምወዳቸውን እወዳችኋለሁ ለማለት አፍራለሁ ። የማልወዳቸውን እወዳችኋለሁ በማለት እሸነግላለሁ ። ከእውነት ይልቅ ሽንገላ ቤቱን ሠርቶብኛል ። ፍቅር አንተን እስከ ሞት አድርሶሃል ፤ ፍቅር እኔን እስከ ወጪ ሲያደርሰኝ “ይህን ፍቅር አልሻም” እላለሁ ። ፍቅር ለወዳጅ ነፍስን መስጠት ነው ፣ እኔ ግን ጊዜ ስለ ሰጠሁ ይቆጨኛል ። ያንተ ፍቅር ትሑት ያደርጋል ፣ የእኔ ፍቅር ግን መሸነፍን ይጠላል ። ያንተ ፍቅር ይቅር ይላል ፣ የእኔ ፍቅር ግን ፍጹምነትን ይፈልጋል ። ጌታ ሆይ ሰውን ሁሉ እወዳለሁ እላለሁ ፣ አንድን ሰው መውደድ ግን ተቸግሬአለሁ ።
የመድኅን ቃል
ልጄ ሆይ ማዕበሉ በእኔ ዘንድ ጭምት ልጅ ነው ። ወጀቡም ይሰግድልኛል ። ጨለማ በእኔ ዘንድ አይጨልምም ። መጨረሻ በእኔ ዘንድ መጀመሪያ ይሆናል ። ጭላጩን ለዓመታት ፣ ጉድለቱን ለሙላት ማድረግ እችላለሁ ። ሃይማኖትን የክርክር ርእስ ማድረግ ሥጋዊነት ነው ። ወንድሜ ይዳን እንጂ ይፈር ብሎ መናገር በእኔ ዘንድ አጸያፊ ነው ። ብዙ ሰዎች ሀብታቸውን አለኝ ለማለት እንጂ አይጠቀሙበትም ፣ አንተም ሃይማኖትን አለኝ ለማለት እንጂ ለጥቅም አልሆነልህም ። ንስሐ ሳትገባ ፣ የእኔን ሥጋና ደም ሳትቀበል ሃይማኖት አለኝ ብለህ መናገር አይገባህም ። በደጅ ስለካዱት ታወራለህ በቤቴ ውስጥ ስለ መጥፋትህ ግን አላወቅህም ።
ልጄ ሆይ !
እየጸለይህ መልሰህ ችግርህ ቢያስፈራህም መጸለይህን አታቋርጥ ። ከልብ ሁኖ ባይተኩስም ተኳሽ ይገድላል ። ከልብ ሁነህ ብትጸልይ ጸሎትህ በፊቴ ሞገስ ያገኛል ። ከልብህ ሳትሆን ብትጸልይም ከቃልህ በሚወጣው ቃለ እግዚአብሔር አጋንንትና ችግርህ ላንተ መንገድ ይለቃሉ ። ከሺህ ቃል አንዲቱ ላይ ልብህ ይወድቃልና በጸሎት በርታ ። በእኔ ለማመን ራስህን መካድ አለብህ ። የእኔ ማንነትና ወገን ይበልጣሉ እያልህ ውድድር ውስጥ ከገባህ ራስህን አለመካድህ ነው ። ራሱን ያልካደ ሰው መስቀል አሸካሚ እንጂ ተሸካሚ መሆን አይችልም ። ራሱን ያልካደ ሰው ለሌላው ተራራ ያሸክማል ፣ ለራሱ ግን ብናኝ ችግር ይከብደዋል ። እኔ ያንተ ነኝና አንተም የእኔ ሁን ። ብዙ ጊዜ እግዚአብሔር ከእኔ ጋር ነው ትላለህ ፣ አዎ ካንተ ጋር ነኝ ። ችግሩ አንተ ግን ከእኔ ጋር አይደለህም ።
ልጄ ሆይ !
ሰውን ለመቅረብም ለመሸሽም አትቸኩል ። እሳት ካልተገለጠ አይሞቅም ፣ የተዳፈነ ፍቅርም ተፈቃሪውን ደስ አያሰኝም ። ያንተ ኑሮ ፍቅር በልብ ፣ ጠብ በአፍ ነው የሚል ይመስላል ። ሁሉን ሰው መውደድ መልካም ነው ፤ የሁሉ ወዳጅ መሆን ግን አይቻልም ። አዎ ሁሉ ስለ እኔ ይወደዳሉ ፣ እኔ ግን ስለ ራሴ እፈቀራለሁ ። የተሰበረ ድልድይ አያሻግርም ፣ ንስሐ ያልገባና ወንድሙን ይቅርታ ያልጠየቀም አይድንምና የንስሐና የይቅርታ ወዳጅ ሁን ። ጤናህ እንዳይታጎል ፣ ሰላምህ እንዳይጠፋ ልብህ ይቅር ባይ ይሁን ። ቂም የተቄመበትን ሳይሆን አንተን የሚበላ እሳት ነው ። ጠላትህ አንድ ጊዜ ጎዳህ ፣ ቂምህ ግን መላልሶ ይጎዳሃል ። የሰጠሁህን የዘመን መክሊት ተጠቀምበት ። የእኔን ምስጋና በምታስብበት ሰዓት ፣ የሰዎችን ክፋት አታሰላስል ። ሲታሰብ ደስ የሚል የእኔ ዝና ብቻ ነው ።