የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰማያዊ ወግ /5

የምእመን ድምፅ

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !

ነገን እያሰብኩ ዛሬን አበላሻለሁ ፣ ዛሬ ከሌለ ነገ እንደማይኖር እረሳለሁ ። ሰው መሆኔን እንዴት ላድርገው ? ሌላውን የመከርኩበት ምክር የእኔን ጭንቀት አይመክረውም ። የተናገርኩትን የምኖርበት የፈተና ሰዓት ሲመጣ ቀልሎ ከመገኘት አድነኝ ። ተድላዬ እግዚአብሔር ሆይ ! ከዚህ ማንነት እንዴት እወጣለሁ ? ሰው ከሰው ጋር እልህ ይጋባል ። እልህ ጣዖት አምልኮ ነው ። እኔ ግን ከራሴ ጋር እልህ እጋባለሁ ። ራሴንም በኃጢአት ጦር እወጋለሁ ። ነፍሴ የራሴ እስከማትመስለኝ ትቻታለሁ ። አንተ ግን ረጅሙን የክፋት ጉዞ ሳደርግ ፣ ቀጠሮዎቼን ታግሠህ ፣ በመንገዴ ሁሉ ሞት እንዳይቀድመኝ ሰስተህ ዛሬን አሳይተኸኛል ። ጠላቱን የሚወድድ ፣ የሚያሳዝነውን የሚያፈቅር እንዳንተ ያለ ማንም የለም ። ብጠጋህ ለጥቅሜ ነው ። ከማስፈልግህ ይልቅ አንተ ታስፈልገኛለህ ። እኔ ግን ያላንተ ለመኖር ሳስብ ያለ አየር ለመቆየት እያቀድሁ ነው ። አቤቱ ሆይ ! ዕፀ በለስ መምረሩን በልቼ ሳይሆን ተሰብኬ እንዳውቅ እርዳኝ ። ሞትን ሞቶ ከማወቅ እባክህ አድነኝ ።

ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !

ያልተሰበሰቡ አሳቦቼ ፣ ዝርው የሆኑ ኀሊዮቶቼ ፣ ገደብ ያጡት ምኞቶቼ ዛሬን እንዳልኖር ያደርጉኛል ። ኑሮዬ በአሮጌው ጨርቅ ላይ አዲስ እራፊ መጣፍ ነው ። የመጣሁበትን መንገድ መልሼ እደግመዋለሁ ። ይህን ተራራ መዞር አይበቃኝም ወይ ? እላለሁ ። ያልታየኸው ነገር ግን በየዕለቱ በሥራህ የምትታየው ፤ አየሁህ የማትባለው ፣ አላየሁህም የማትባለው ፣ ድንቅ እግዚአብሔር ሆይ ብርታትህን እፈልጋለሁ ። የከበሩ አሳቦችን በውስጤ አኑር ፣ ዓለምን በከንቱነት ልኳ እንዳያት እርዳኝ ። የምጨነቀው ለሰባና ለሰማንያ ዓመት ሳይሆን ለዘላለም በምድር ላይ የሚኖር ሰው ዓይነት ነው ። ተደራጅቶ የመጣብኝን አሳብ ሁሉ በማይመከተው ክንድህ አርቀው ።

የመድኅን ክርስቶስ ቃል ይህ ነው !

ልጄ ወዳጄ ሆይ !

ቅዱስ መንፈስ በጸጸት ራሳቸውን ለሚጎዱ ፣ ከክርስቶስ ደም የተነሣ ያለውን ስርየት እያሳየ ዕረፍትን ይሰጣቸው ዘንድ ወደ ዓለም መጥቷል ። ራስን ብቻ መስማት ፣ በራስ አለማወቅ ተጠልፎ መውደቅን ያመጣል ። የአባቶችህን ምሳሌነት ተከተል ። ብርታታቸው ስንፍናህን ይውቀሰው ፣ ድካማቸው ተስፋህን ያድሰው ። ለስላሳ ጣዕም እንዳለው ዜማ ፣ በእርጋታ እንደሚፈስስ ውኃ ፣ በጥበብ እንደሚሳብ መረብ ፣ በትሕትና ጎንበስ ቀና እንደሚል ዛፍ ፣ በተመሥጦ እንደሚጠፋ ፈላስፋ ፣ ለነጽሮተ ሥሉሥ ቅዱስ እንደበቃ መናኝ በጸሎትና በቃሌ ወደ እኔ ልስብህ እፈልጋለሁ ። አንተ ግን የአምላክን ቀጠሮ በፍጡር ቀጠሮ ትሽራለህ ። ቆይ አይቼ ልምጣ ብለህ እዚያው ትከርማለህ ። ወደ ክፋት ግዛት እየገባህ ታስረህ ትጨነቃለህ ። የልደቴን ደስታ እያሰብህ ስጦታ ትለዋወጣለህ ፣ የሞቴን ዋጋ እየዘነጋህ ራስህን ለእኔ ለመስጠት ትሰስታለህ ። ከወሬ ሰዓትህ ቀንሰህ አትሰማኝም ። የምኞትህን ያህል እኔን አትወደኝም ። በድንኳንህ እልልታ እንዲሰማ ብዙ ጊዜ መጣሁ ። አንተ ግን የምትገዛውን ደስታ ፈለግህ እንጂ የምትገዛለትን ሐሤት አልፈለግህምና ተጎዳህ ።

ልጄ ወዳጄ ሆይ !

ያልገበሩ የአካልህ ግዛቶች ለእኔ እንዲገብሩ ሰዓቱ አሁን ነው ። ስንቶች ወዳጆችህ በየቀኑ በሞት እየተጠሩ ነው ። ሞት ዙሪያህን ሲዞርህ እንዴት አልነቃህም ? እኔ ስመጣ በዓላማህ ማማ ላይ እንዳገኝህ በርታ ። የምትበረታውም በጸሎት ፣ በቅዱስ ቃሌና በአባቶች ምክር ነው ። አንተ ተላላ ሆይ ! ገና በማኅፀን ሳሉ የሚሞቱ ጽንሶችን ፣ በተወለዱ በመጀመሪያው ቀን የሚያንቀላፉትን ጨቅላዎች ቍጠርና ብዙ ዘመን እንደ ቀረህ አታስብ ። ለዓይንህ የሞሉትን ሰዎች የምወስደው እንድትማር እንጂ እንድትማረር አይደለም ። ቅና ንስሐ ግባ ። ራስህን ከማሳደድ ወጥተህ ራስህን በእኔ አግኘው ። የሁልጊዜው አፍቃሪህ ፣ በተራራው በሸለቆው የማልለይህ አባትህ እግዚአብሔር እኔ ነኝ ።

ቀንህ በእኔ ይብራ !

ሰማያዊ ወግ / 5

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 14 ቀን 2015 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ