የምእመን ድምፅ
ጌታዬ ኢየሱስ ክርስቶስ ሆይ !
ምንም የሌለኝ ድሀ ነኝ ። ዕራቁቴን ተወልጄ ዕራቁቴን የምጓዝ ነኝ ። ካንተ በቀርም በጎነት የለኝም ። መንገዴም ፣ እውነቴም ፣ ሕይወቴም አንተ ነህ ። ያላንተ መጀመር ፣ ያላንተ እርግጠኛ መሆን ፣ ያላንተ መፈጸምም አይሆንልኝም ። ይህን እመሰክራለሁ ፣ ይህን እታመናለሁ ። ነገር ግን እንደ ምሥራቅ ነፋስ እሸቱን እንደሚያጠወልገው ፣ እንደ በረሃ አውሎ ትቢያን እንደሚያለብሰው በድንገት እምነቴን አጣዋለሁ ። ካጠገቤ እያለህ ርቀሃል እልሃለሁ ። በልቼ አልበላሁም ብዬ አጉረመርማለሁ ። የእኔ ባልሆነ እስትንፋስ ቆሜ እግዚአብሔር ትቶኛል እልሃለሁ ። ግልጥ ነገሮችን ለማየት ዓይኔን እጨፍናለሁ ፣ የተሰወሩ ነገሮችን ይታዩኛል እያልሁ በጥርጣሬ ማዕበል እመታለሁ ። ባላያቸውም የሚጸልዩልኝ ፣ ባልሰማቸውም ስለ እኔ ባንተ ፊት የሚቆሙልኝ ስላሉ አለሁ በቤትህ ብዬ አምናለሁ ። ቀኑ ሲጫነኝ ቀንበሩን አንሣልኝ ። ማየት ሲያቅተኝ ውስጤን አብራልኝ ። መናወጡ ከመሠረቴ እንዳይነቅለኝ ፣ በእኔ ላይ የደከምከውን ረስቼ ተስፋ እንዳልቆርጥ አቤቱ አጽንተህ ያዘኝ !
ታላቁ አፍቃሪዬ ሆይ !
ብዙዎች ከስፍራቸው በሚታጡበት ዘመን ፣ አገልጋይነትን ለተገልጋይነት በሚጠቀሙበት ዓለም ፣ ሐሰት እየተፈጠረ ሰውን ጥላሸት የሚቀቡ አርካሾች በበዙበት ፣ ክርስትና የወንድምን ድካም መሸፈን ነው የሚለው እውነት ጉድጓድ በገባበት ወራት እኔም እያወቅሁ ሳጠፋ መልሼ እጸጸታለሁ ። ጸጸቴ ጉልበት አጥቶ የተፋሁትን መልሼ እልሳለሁ ። የሚደረገው ሲደረግ የኖረ ፣ የሚሆነው የዓለም መገለጫ ግብር መሆኑን ዘንግቼ ለመናወጥ ዝግጁ ሁኛለሁ ። የማየው ትልቅ ሰው ስፈልግ ሁሉ ድንክ ሁኖ ይታየኛል ። በራሴም ተስፋ ለማድረግ ስሻ ካንተ በቀር ዋስ አጣለሁ ። ኃይሌ ሊከዳኝ ሲሞግተኝ አቤት እልሃለሁ !
ክርስቶስ መለሰ፡-
ልጄ ሆይ !
እንኳን ኃጢአትን ጽድቅን በሚከስሰው ዓለም ላይ የእኔን መሐሪነት ብቻ አስብ ። በዚህ ዘመን ኃጢአት የሚባለው ከሰዎች ክፋት ጋር አለመተባበር ነው ። ኅብረትን በአድመኝነት ፣ ትጋትን በምቀኝነት ፣ ተከላካይነትን በበቀለኝነት ስሜት በለወጠ ዘመን አንተ ግን የእኔን ልብ ፈልግ ። በምሳሌነቱ የሚያሳርፈኝ ሰው አጣሁ ስትል እኔ ሰው ሁኜ ምሳሌ እንደሆንኩህ አስብ ። የሚያስተምሩህን ስማ እንጂ ሕይወታቸው ምንድነው? ብለህ ለራስህ ስህተት ድፍረት ለማግኘት ሰውን አትመርምር ። ሕይወትን የምመዝን ፣ ለሁሉ እንደ ሥራው የምሰፍር እኔ ነኝና በሥራዬ አትግባ ። ልቅሶህ አጋዥ እንዳያጣ በሰው ልቅሶ አታላግጥ ። ለእገሌ መሸ ብለህ አትደሰት ፣ ቀጥሎ ይነጋለታልና ። ያንተ ብርሃን ግን ወደ ጨለማ ይሄዳልና ቀን ሆነልኝ ብለህ አትመካ ። ብዙ ነገሮችን ለማወቅ አትሻ ። እኔን ማወቅ ብቻ ያሳርፋል እንጂ ሌላ እውቀት እንዳወከ ይኖራል።
ልጄ ሆይ !
ጽድቅን የሚሠራው ጨክኖ ይሥራ ፣ የሚረክሰውም ጨክኖ እየረከሰ ነው ። ከሌሎች ብርታት ተማር እንጂ ድካማቸውን መስነፊያህ አታድርገው ። ክርስትና የእኔ እንጂ የአገልጋዮች አይደለችምና እኔን በሰው ልክ አትመዝነኝ ። የሚያጥለቀልቁ ክፉ ቀኖች ቢመጡም እኔ መርከብ ሁኜ አድንሃለሁ ። መዘጋጀትንና መጸለይን ሥራህ አድርገው ። ፈቃድህን ለፈቃዴ አስገዛው ። ደግነትህ ለሁሉ ይሁን ። ፍቅርን ስጥ እንጂ በሰው ብዙ አትተማመን ። መንፈሳዊ ዝምድና ተንቋልና አክብረህ ያዘው ። ወረት ከሚወጋህ ሞት ቢወስድህ ምረጥ ። ከእምነትህ ጋር ሙት ። እኔ ዋጋ እከፍልሃለሁ ።
ሰማያዊ ወግ / 6
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
የካቲት 7 ቀን 2015 ዓ.ም.