መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች » ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች /2

የትምህርቱ ርዕስ | ሰባቱ የፈሪሳውያን ዓይነቶች /2

አልምጥ ፈሪሳውያን

በሁለተኛ ምድብ የሚገኙት ፈሪሳውያን ከበጎ ነገር የዘገዩ ፣ ዳተኛ ምድብ ናቸው ። ለሌሎች መልካም ሥሩ ብለው ያስተምራሉ ፣ እነርሱ ግን አያደርጉትም ። በጎ ለማድረግ ያስባሉ ነገር ግን ዛሬ አይደለም ይላሉ ። አንድ በጎ ነገር በማድረግ ለነገ የሚቆይ ነገር ለመሥራት ምክንያት ይፈጥራሉ ። እነዚህ ፈሪውያን አድርጉ የማለት እምቅ ትምህርት አላቸው ፣ ትእዛዙ ግን እነርሱን የሚመለከታቸው አይደሉም ። ሐኪሙ ይህን አታድርጉ ብሎ ራሱ ግን ያደርገዋል ። እነዚህም ለሌሎች ጤና ቀና ምክር ይሰጣሉ ፣ ለራሳቸው በሽታ ግን መድኃኒት አይወስዱም ። ሰዎች ታማሚ እንደሆኑ ፈውስም እንደሚያስፈልጋቸው እርግጠኛ ናቸው ፣ የራሳቸውን በሽታ ስላላመኑ መድኃኒቱን አይፈልጉትም ። እነዚህ ፈሪሳውያን ጊዜው አሁን ነው የሚለውን የእግዚአብሔር መንግሥት መመሪያ አይከተሉም ፣ ነገ ይሆናል ብለው ይወረውሩታል ። ክፉ ከሚያደርጉት በላይ በጎ ባለማድረጋቸው እግዚአብሔርን ያሳዝናሉ ።

አይሁዳውያን እግዚአብሔር ሁለት ሚዛን እንዳለው ያስቡ ነበር ። የአይሁድ ጥፋትና የአሕዛብ ጥፋት አንድ ዓይነት ቢሆንም እግዚአብሔር እኩል አይቀጣንም ብለው ያስቡ ነበር ። ስህተታቸውን ቀላል ለማድረግ የሄዱበት ርቀት እግዚአብሔርን አባይ ሚዛን ያለው አስመስለው ሳሉት ። አይሁዳዊ መሆን በጎ ለማድረግ መመረጥ ነው የሚለውን አይሁዳዊ መሆን ክፉ ለማድረግ ፈቃድ ማግኘት ነው ብለው ተረጎሙት ። ነቢዩ ሳሙኤል፡- “ባሪያህ ይሰማልና ተናገር” አለ ። በዚህ ዘመን ያለን አማንያን “ባሪያህ ይናገራልና እግዚአብሔር ሆይ ስማ” የምንል ይመስላል ። አይሁዳውያን በስህተታቸው እንደሚቀጡ ብዙ ማሳያዎች አሉ ። ወንድማቸውን ዮሴፍን በመሸጣቸው ምክንያት በግብጽ ምድር ባሪያ ሆኑ ፣ የሐሰት ነቢያትን በመከተላቸው በባቢሎን ተጋዙ ። መሢሑን በመስቀላቸው በሮማውያን ተደመሰሱ ። እስካለፉት ሰባ ዓመታት ድረስ አገር አልባ ሆነው ለ1900 ዓመታት በዓለም ላይ ተበተኑ ። የፈለግነውን እየሠራን እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ጥሎ አይጥልም ማለት ግብዝነት እንጂ እምነት አይደለም ። በጎ እየሠራን ያንን ብንናገር ወይም ክፉ ነገር ሳይመጣብን ብንፎክር ያምር ነበር ። በዓለም የሌለ መከራና ጉድ ተሸክመን ከዚህ በላይ መጣልና መውደቅ አለ ወይ( በሚሊየን የሚቆጠር ወገን በጦርነት ሲያልቅ እነዚያ ኢትዮጵያውያን አይደሉም ወይ ( አጉል መመጻደቅ ንስሐ እንዳንገባና ለተጎዱት እንዳናዝን አድርጎናል ። ትንቢት የተነገረለትን ፣ ሱባዔ የተቆጠረለትን ፣ አንተ አትሠራውም ልጅህ ሰሎሞን ይሠራዋል የተባለውን መቅደስ ያፈረሰው ኃጢአት ነው ። እግዚአብሔር በዓላማው ጨካኝ ነው ፣ በፍርዱም አድልኦ የለውም ።

አንዳንድ ሰዎች የብሉይ ኪዳኑ እግዚአብሔርና የአዲስ ኪዳኑ እግዚአብሔር ልዩ እንደሆነ ያስተምራሉ ። የብሉይ ኪዳኑ ጨካኝ ፣ የአዲስ ኪዳኑ ሩኅሩኅ እንደሆነ ይገምታሉ ። እግዚአብሔር ግን ፍርዱ ምሕረቱን ሳያስቀርበት ፣ ምሕረቱም ፍትሑን ሳያጓድልበት ለዘላለም ይኖራል ። እግዚአብሔር በአንድ ጊዜ ፈራጅም መሐሪም ነው ። እናት ለልጅዋ መሐሪ ብትሆን ፍትሕን ረግጣ ነው ፣ መንግሥት ፍትሐዊ ቢሆን ፍቅር የሚባልን ነገር ላለማወቅ ወስኖ ነው ። እግዚአብሔር ግን የፍቅርም የፍትሕም አምላክ ነው ። ሁላችንም ብንሆን ደግ ሲጠቃ ክፉ ሲያጠቃ ማየት አንችልም ። ይህ ማለት እግዚአብሔር እንዲፈርድ እንከጅላለን ማለት ነው ። በሌሎች ስህተት ላይ የሚፈርደው በእኛም ስህተት ላይ እንዲፈርድ መፍቀድ አለብን ። የተቀበልሁት የሚገባኝን ነው ማለት ታላቅ ብፅዕና ነው ። በአዲስ ኪዳን የተገኘው ነጻነት እንደ ፈለግን የመኖር ሳይሆን እንደ ተፈቀደልን የመገኘት ነው ። ነጻነት ከባርነት በላይ ኃላፊነትን የሚጠይቅ ነው ። ነጻነትን ማስተዳደር አለመቻል ከባድ ነገር ነው ።
በዚህ ዘመን ያለን ሰባክያን ምናልባት አልምጥ ክርስቲያን ሆነን ይሆናል ። ቤተ ክርስቲያንን እነ እገሌ ጎዷት ብለን እንቆረቆራለን ፣ እኛ ስንጎዳት ግን አይሰማንም ። የአንዳንዶችን ነቁጥ ስህተት እናጎላለን ፣ የሌሎችን ተራራ የሚያህል ስህተት ደግሞ በአገር ልጅ ስሜት እናልፈዋለን ። እገሌ የተናገረውን ስህተት ስህተት ስንለው ፣ ወዳጅ ከሆነ ደግሞ የአንደበት ማዳለጥ ፣ ከፍቅር የተነሣ የተነገረ ነው ብለን እናልፈዋለን ። ቤተ ክርስቲያንን ዘረኝነት የሚወዘውዛትን ያህል ቤተ መንግሥትን አይወዘውዘውም ። የፖለቲከኞች ዘረኝነት ጠቅለል አድርጎ አራት ክፍለ አገርን ላንዱ ፣ አምስት ክፍለ አገርን ለሌላው ሰጥቶ ነው ። በእኛ ያለው እስከ ቤት ቍጥር ወርዶ እስከ ጎጥ ዘቅጦ ይታያል ። ፈሪሳዊነት አስመሳይነት ነው ።

ጌታችን ወደ ዓለም የላከው ሕይወታችን እንዲመሰክር እንጂ ቃላችን ብቻ እንዲመሰክር አይደለም ። አንድ ሰው፡- “የምትናገረውን የምትኖረው እያፈረሰብኝ ነውና ልሰማህ አልቻልኩም” እንዳለው እኛም ሆነናል ። በጎ ሥራ ምግባርን ሙሉ ያደርገዋል ። ባለ መስረቅ ብቻ ምግባር ሙሉ አይሆንም ፣ መስጠትም ያስፈልጋል ። ምግባር ሁለት እጆች አሉት፤ ክፉን ማቆምና በጎ መጀመር ናቸው ። የኃጢአት በጀታችን ለጽድቅ ካልዋለ ገና አላመንም ማለት ነው ። አለማመንዘር ብቻውን ብቂ አይደለም ፣ ለትዳር አጋር አሳቢ መሆንም ያስፈልጋል ። በጎ ሥራ ትላንት የሠራነውን ክፉ ነገር መካሻ ማጠቢያ ነው ። የበደሉትን መካስ ፣ የቀሙትን መመለስ እርሱ ንስሐ ይባላል ። በጎ ሥራ ዛሬን ኖርኩ የሚያሰኘን ነው ። ለነገው ትውልድ ቀሪ ሀብት ነው ። “የቄስ ልጅ እግዚአብሔር አጎቱ ይመስለዋል” እንዲሉ እኔን ምንም አይለኝም ብሎ ያውም በቤቱ በበደል መጽናት ተገቢ አይደለም ። ምክንያት አያድንም ። ወገን እያለቀ ምክንያት የሚደረድር ሹም ካለ ተባባሪ ነው ። ይህን ካላቆምሁ የእኔ መኖር ምን ጥቅም አለው ( የሚል ወኔያም ያስፈልጋል ። ዛሬ ማድረግ የሚገባንን ነገ ብናደርገው ከክፉ ሊቆጠር ይችላል ። ታሞ ያልረዳነውን የመቃብሩን ሐውልት ብንሠራለት ጥቅም የለውም ። ብዙዎች ስሞት አትቅበሩኝ ፣ ዛሬ አዳምጡኝ እያሉን ነው ። ፈሪሳዊነታችን ግን አልሰማቸውም ።

አንድ የበላይ ሰው አውቃለሁ ። ራበኝ የሚል ማመልከቻ ሲመጣላቸው በእሳቱ “ሰ” ሊጻፍ የሚገባውን በንጉሡ “ሠ” ጽፈሃልና አስተካክለህ አምጣ ይሉ ነበር ። ያ ረሀብ ዘመኑን እንዳያሳጥርበት የሚጨነቅ አገልጋይ “መቼ(” ሲል “ከዐሥር ቀን በኋላ ና” ይባላል ። ምክንያቱም ነገ የቦርድ ስብሰባ ፣ ተነገወዲያ የውጭ እንግዶች … እየተባለ ምክንያት ይሰጠዋል ። ረሀብተኛን ነገ ና ማለት አይቻልም ፣ ያለው ቀን ዛሬ ነውና ። ለፊደሉ ስንጨነቅ ለራበው ሰው ግን አንጨነቅም ። ጭካኔም ልክ አለው ።

አቤቱ ምን እየሆንን ነው ፣ እባክህ መልሰን !

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 15 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ