የማያዩ ፈሪሳውያን
እነዚህ የፈሪሳውያን ወገኖች ሴቶችን ላለማየት ፊታቸውን አዙረው ፣ አቀርቅረው ፣ ዓይናቸውን ጨፍነው ይሄዱ ነበር ። በመንገድ ላይ እኅታቸውንና እናታቸውን ቢያገኙ እንኳ ሰላምታ አይሰጡም ነበር ። ሴቶችን ላለማየት በሚያደርጉት ጥረት ከግንብ ጋር ይጋጫሉ ፣ ወደ ገደል ይገባሉ ። በዚህ ምክንያት የሚደርስባቸውን ጉዳትና ቍስል ለሃይማኖት እንደ ተከፈለ ዋጋ ይቆጥሩታል ፣ የቅድስናም አካል እንደ ሆነ ያስባሉ ። ራሳቸውንም እንደ ሰማዕት ይቆጥራሉ ። ሃይማኖት ሰምቶ ማመዛዘን እንጂ ከንቶውም አልሰማም የሚል አይደለም ። ሐዋርያው፡- “ሁሉን ፈትኑ መልካሙንም ያዙ ፤” የሚለው ምክሩ ዝነኛ ነው ። (1ተሰሎ. 5 ፡ 21) በተለያዩ ዩንቨርስቲዎች ላይ ይህ ጥቅስ መሪ ቃል ሆኖ ተለጥፏል ። ሁሉን መፈተን መልካሙን መያዝ ፣ ልበ ሰፊ መሆን የሚያዋጣውን ግን መለየት ይገባል ። ጌታችን ክፉ ከሚባሉት ሳይቀር መማር እንደምንችል ሲገልጥ “እንደ እባብ ብልህ ሁኑ” አለ ። እባብ እንደ ጠላት የሚታይ ነው ። ከጠላትም ትምህርት መውሰድ ይገባል ። ጠላቶቻችን ራሳቸውን የሚጠብቁ ፣ ጠንቃቃ የሆኑ ፣ ብዙ ለመኖር የሚያቅዱ ፣ ወጥመድ ውስጥ ልገባ እችላለሁ ብለው ከዝሙትና ከመጠጥ የሚርቁ ሊሆኑ ይችላሉ ። ይህንን ከእነርሱ መማር ብልህነት ነው ። ሃይማኖተኛነት ምንም ነገር አላይም ማለት አይደለም ፣ የማየውን ሁሉ ግን አልከተልም የሚል መርህ ያለው ነው ።
ዝሙት ያለው ከዓይናችን ይልቅ በልባችን ውስጥ ነው ። በርግጥ ዓይንና ጆሮ የልብ መስኮት ናቸውና መጠበቅ ይገባናል ። መስኮት መክፈቻ ብቻ ሳይሆን መዝጊያም አለው ። የመስኮት ዓላማ ደጁን ለመመልከት ፣ ብርሃንና ነፋስ ለማግኘት ፣ ከቤት የማይገባውን ሰው በሩቅ ለመሸኘት ፣ ሒሳብ ለመቀበል የሚያገለግል ነው ። መስኮት ግን ካልተዘጋ ለሌባ በሩ ነው ። ሌባ ስልጠናው በበር ከመግባት በመስኮት መግባት ነውና ። ለምናየው ለምንሰማው ጠንቃቃ መሆን ይገባናል ፣ ጨርሶ አላይም አልሰማም ማለት ግን አንችልም ። ጨርሶ ሴት ባለማየት ከዝሙት ለመራቅ የሚፈልጉ ሰዎች ይኖራሉ ። ሴቶች ግን እኅቶችም ፣ እናቶችም ከሁሉ በላይ የተፈጥሮ እኩዮቻችን ናቸው ። ከሴቶች ጋር አንድ አማኝም አገልጋይም ያላቸው ግንኙነት ሥርዓት ያለው ሊሆን ይገባዋል ። ሴቶችም ከወንዶች ጋር ያላቸው ግንኙነት ለውድቀት የማያደርስ መሆን አለበት ። አስቀድመው ካላጠሩት ድንበሩ ላይ ከደረሰ በኋላ መመለስ ይከብዳል ። አገልጋዮች ሁለት ሁነው አንዲት ሴትን ቢያገለግሉ መልካም ነው ፣ አሊያ ሁለት ሴቶችን አንድ አገልጋይ ማገልገል አለበት ፣ ስፍራውም ግልጥ መሆን ይገባዋል ። ይህ ሁሉ ዝሙት እስከ ዕድሜ ልክ ድረስ የሚጓዝ ቀውስን ሊያመጣ ስለሚችል ፣ ከሁሉ በላይ የአገልግሎት ጉዞን ስለሚያሰናክል ነው ። በወጣትነት የተዘራው በሽምግልና ይታጨዳልና ጠንቃቃ መሆን ይገባል ።
ጥንቃቄአችን ጥላቻን እንዳይፈጥር መጠንቀቅ ይገባል ። እጅግ ጥንቃቄ ከስህተት ይዳርጋል ። ቅድስና በእኛ ፈቃደኝነት መንፈስ ቅዱስ በውስጣችን የሚሠራው የለውጥ ሂደት ነው ። ቅድስና በጉልበት አይደለም ፣ በስጦታው መንገድም መጓዝ ያስፈልጋል ። መሳሳቦችን ማርገብ ይገባናል ። አንድ ወንድ ወንጀል ፈጸመ ማለት መላው ወንድ ክፉ ነው ማለት ላይሆን ይችላል ። የወንዶች ማኅበር ፣ የሴቶች ጽንፍ አስፈላጊ አይደለም ። ይህን ዓለም ቀና ለማድረግ የሁለቱም አስተዋጽኦ ያስፈልጋል ። ጥንቃቄአችን ጥላቻ እንዳይሆን አሁንም ደግመን ማሰብ ይገባናል ። ፈሪሳውያን እንዲህ ሰንጥረው የሚያዩ ፣ በአጉሊ መነጽር እያዩ ለመታዘዝ የሚፈልጉ ናቸው ። ውስጣቸው ግን ቅሚያና ግድያ ሞልቶበታል ።
በዚህ ዘመንም አሸንክታብ ባይኖረንም ፣ የፈሪሳውያንን ቀሚስ ባንለብስም ዘመናዊ ፈሪሳዊ ልንሆን እንችላለን ። ፈሪሳውያን እስራኤልን ይወዳሉ ፣ እስራኤላውያንን ግን ይንቃሉ ። ፈሪሳዊነት ዕውር ስለሚያደርግ ኢትዮጵያን እወዳለሁ እያሰኘ ኢትዮጵያውያንን ግን ሊያስጠላና ሊያስንቅ ይችላል ። ስለ ቅድስና ሲያወሩ ነቁጥ ስህተት የሌለባቸው የሚመስሉ ፣ በቅድስና ችግር እገሌን ገፋሁ ፣ አወገዝሁ የሚሉ ራሳቸው እጅግ የረከሱ ናቸው ። መግለጥና ማጋለጥን ለይተው የማያውቁ ፣ ለቅድስና በመቆርቆር ስሜት በሐሜት ሰውን ሲበክሉ የሚውሉ አያሌ ፈሪሳውያን አሉ ። አንዱ ቅድስና አትፍረድ የሚለው ትእዛዝ ነው ። እገሌ ደከመ ሲባል እኔም የማውቀው አለ ብለው ቶሎ ብለው አደባባዩን የሚይዙ ሰዎች በብዙ ጭቃ ውስጥ እንደ ቦኩ ሕሊናቸው ያውቀዋል ። በሰው ስህተት የራስን ቅድስና መሥራት አይቻልም ። ምሕረት የለሾች ስለ ኢየሱስ ተቆርቋሪ ነን ብለው ሲናገሩ እንሰማለን ። ወንጌል ያለወጣቸው ጨካኞች ለወንጌል ተገፋሁ ብለው ሲያነቡ ፣ ተውኔት ሲሠሩ እንመለከታለን ። መቼም ባለጌና ጨዋ ቢጣላ የሚያሸንፈው ባለጌ ነው ይባላል ። ምክንያቱም ባለጌ የሚገድበው ምንም የሞራል አጥር የለምና እንደ ፈለገው ያወራል ፣ ጨዋው ግን ለራሱ ክብር ስላለው ዝም ይላል ። በዚህ የተነሣ ጨዋውን ሁሉም ይኰንነዋል ።
ፈሪሳዊነት አቀርቃሪነት ነው ። አንገት ደፊ አገር አጥፊ እንደሚባለው እጅግ ዘማዊ የሆኑ ሰዎች ከቀልቃሎች ይልቅ ስልክልኮቹ ናቸው ። በአደባባይ ሴት ሰላም ማለት የሚሰቀቁ ፣ የብዙዎችን ዕድል የሰበሩ ፈሪሳውያን ዛሬም አሉ ። ስለ ፍቅር የሚያስተምሩ ፣ በመንገዴ ቆሟል የሚሉትን ሰው ግን የሚያስወግሩ እየበዙ ነው ። ከዚያን ጊዜው ይልቅ ቤቱ የወንበዴዎች ዋሻ የሆነው አሁን ነው ። ወንበዴ ሌባ ብቻ አይደለም ፣ ገዳይም ነው ። ነፍስን ሰርቆ ኪስን የሚፈትሽ ነው ። ዛሬም ቀማኛነትና ገዳይነት እያበዛን ነው ። አንድ ጊዜ መግደል ሞኝነት ነው ብለን መጀመሪያ በሥነ ልቡና ፣ ቀጥሎ በመንፈሱ እንዲሞት እንታገላለን ። እኛው ገድለን ጥሩ የቀብር ሥነ ሥርዓትን እናዘጋጃለን ። ለሰው የተሰወረው ሳይገልጥ ለሚያየው ጌታ የተብራራ ነው ። ፍርድም በደጅ ነው ።
ጌታ ሆይ ከውጫዊ ይልቅ ውስጣዊ ጭምትነትን አድለን !
ዲያቆን አሸናፊ መኮንን
ጥቅምት 17 ቀን 2018 ዓ.ም.