መግቢያ » ልዩ ልዩ ሁለት » ሰውን ሰው አድርገው

የትምህርቱ ርዕስ | ሰውን ሰው አድርገው

ረፈደ አይሉህም በገባዖን ፀሐይን አቁመሃል ፣ መሸ አትባልም ፣ ጨለማ በአንተ ዘንድ አይጨልምም ተብሏል።  ጀምበር አዘቀዘቀ አይሉህም፣ ሠርክን ማለዳ እንደምታደርግ በሕዝቅያስ ታይተሃል። እባክህ እኔ አልለወጥም፣ ታጥቦ ጭቃ ነኝ፣ ዋጋ የለኝም፣ የእኔ ነገር አብቅቷል፣ በሰማይ በምድር ስደተኛ ነኝ፣ ለእኔ አትድከሙ  ፣ አባት እናቴን ሳይቀር ተስፋ ያስቆረጥኩ ነኝ፣ ወዳጅ ዘመድን ያስከፋሁ ነኝ የሚለውን ሰው፣ ሰው አድርገው። አጥቶ ሳይሆን ሰጥተኸው አላውቅበት ላለው ፣ የትላንቱን ስህተት ዛሬ ላይ ለሚደግመው፣ ኃጢአት ማንነቴ ነው ለሚለው፣ በሞከርኩ ቁጥር ይብስብኛል እያለ ለሚናገረው እባክህን ሰውን ፣ ሰው አድርገው።

ንዴት ጊዜያዊ ፣ ጸጸት ዘላለማዊ ለሆነበት ፣ ምነው እንዲህ ባላደረግሁ ኖሮ እያለ መልሶ ያንን የሚያደርገውን ፣ በቆመበት ስፍራ የሚረግጠውን፣ ጭቃ ላይ ተቀምጦ አጠቡኝ የሚለውን እባክህ ሰው አድርገው። ዝንብ እንኳ በተፈጥሮዋ ውብ ናት፣ በውሎዋ ግን ቆሻሻ ናት። ተፈጥሮው ሳይሆን ውሎው ያቆሸሸውን ፣ ጓደኛ መምረጥ የማይችለውን፣ እንደ በሬ ካራጁ ጋር የሚውለውን፣ ጨረስኩ ሲል የሚጀምረውን፣ የክለሳ ኑሮ ያደከመውን ያንን ሰው፣ ሰው አድርገው::

የወደደውን ቢያጣ የጠላውን የሚቀላውጠውን፣ ቀጥ ቀጥ ያለ ቢያጣ ጎባጣ የሚመርጠውን፣ የዘመናት ወዳጅነት ፈርሶበት የዕለት ትውውቅ ትልቅ ግኝት የሚመስለውን፣ ተላላነትን የዋህነት፣ በታኝነትን ቸርነት እያለ የሚጠራውን ያንን ሰው፣ ሰው አድርገው።

በመንገዱ የማይጠነቀቀውን፣ ሁለት እጆቹን በኪሱ ከትቶ የሚሮጠውን፣ ሲወድቅ የገዛ እጆቹ የማይደግፉትን፣ ይበልህ አርፈህ አትቀመጥም ነበር? እያለ ልቡ የሚፈርድበትን፣  በገደል አፋፍ ላይ የሚታገለውን፣ ያንን ሰው ፣ ሰው አድርገው። የሚውልበትን የማያውቀውን፣ ጓደኝነት ያልመረጠውን፣ አንተ እኮ ያለውን የሚከተለውን ፣ ላወደሰው  አንገት የሚሰጠውን ፣ ብዙ አይቶ ጥቂት የማይማረውን ፣ ሐሣር ያልመለሰውን፣ መከራ ያልመከረውን ያንን ሰው  ፣ እባክህ ሰው አድርገው። የመጀመር እንጂ የመጨረስ አቅም ያላገኘውን ፣ ቢያዝ ዋስ፣ ቢቸገር መግቢያ የሌለውን ፣ በግድ የሚስቀውን፣ ሰውን ለማስደሰት የተቀመጠ የሚመስለውን ፣ ወርቅ አበድሮ ጠጠር የሚመለስለትን ፣ ለማያፍሩ እያፈረ የሚኖረውን ያንን ሰው፣  ሰው  አድርገው።

ይገባኛል ለሚለው ፣ በችግሩ ለማይመረረው ፣  አድሮ ጥጃ ለሆነው፣ የማይወዱትን ለማስደስት የሚወዱትን ለሚያስቀይመው፣ ሁሉም ነገር ለሚያስደነግጠው፣ አሳዳሪውን ጌታ፣ ዘላቂውን ሕይወት መለየት ላልቻለው ጌታ ሆይ ሰውን፣ ሰው አድርገው። ልቡ ለሚያመረቅዘው፣ በገዛ ስህተቱ ራሱን ለሚገርፈው፣ ለትዳሩ ለልጆቹ ገንዘብ እንጂ ጊዜ እንደሚያስፈልግ ላልተረዳው ፣ ሁሌ  ፋሲካ ለሚመስለው፣ የሰውን አመል መጨበጥ ላቃተው፣ አስደስታለሁ ብሎ ለሚያስከፋው፣ የጨው ውኃ እየጠጣ መልሶ ለሚጠጣው ጌታ ሆይ ያንን ሰው፣ ሰው  አድርገው:: እንደገና ከጭቃ አንሥተህ ሥራው። መፍጠር ብቻ አይደለም፣ እንደገና አበጃጀው::

በከንቱ ጸጸት ራሱን ለሚያደክመው፣ ተበድሎ ይቅርታ ለሚጠይቀው፣ ልፍስፍስነት መጫወቻ ላደረገው፣ ትሕትናው ላስረገጠው፣ ብዙ አለቃ በላዩ ላይ ለሾመው ለዚያ ሰው፣ እንደገና ሰውነትን አልብሰው። ብዙ ደክሞ ጥቂት ላላተረፈው፣ ብዙ አፍቅሮ እፍኝ መውደድ ላላገኘው፣ አግብቶ ፈት፣ ወልዶ መሐን ለሆነው፣ ራሱን ለሚፈራው ፣ የገዛ ቀልቡን ለሚጠራጠረው ወልድ ሆይ አንተ ዋስ ሆነው ።

ከራሱ ጋር ላለመገናኘት የዘመናት ሽሽት ላይ ላለው፣ ለራሱ ጊዜ ሰጥቶ ለማያውቀው፣ ውስጡን ማዳመጥ ለተሣነው፣ የሚፈልገውን በትክክል ላለየው ኢየሱስ ጌታ ሆይ ሰውን ሰው አድርገው።

ሸለቆውን በሚሞላው ስምህ በኢየሱስ ክርስቶስ አሜን!

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ነሐሴ 2 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ