የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሰው ሆይ ተመከር !

ጌታችን በከተማ ፣ ዮሐንስ በበረሃ ቤት አልባ ነበሩ። ቤት አስፈላጊ ነው፣ ቤት ስላለው በምድር ላይ የቀረ ግን የለም። ካስመረቅነው ፣ ሰው ካባረርንበት፣ ካከራየነው ፣ ከኖርንበት ቤት አንድ ቀን እወጣለን።  ጌታችን ከደቀ መዛሙርት ጋር ፣ ዮሐንስ ከተፈጥሮ ጋር ነበሩ። ጌታችን በከተማ የድንግልና ሕይወትን ኖረ፣ ዮሐንስ በበረሃ የድንግልና ሕይወትን ኖረ። መናንያን በከተማም በበረሃም መኖር እንደሚችሉ በዚህ ታወቀ። ጌታችን በገዳመ ቆሮንቶስ የመናንያንን ቦታ ባረከ ፣ 40 ቀንና 40 ሌሊት ጾም ጸልዮ ሲወጣ ወዲያው የቃና ዘገሊላ ሰርግ ላይ ተገኘ። ከስብከቱ በፊት ምንኩስናንና ጋብቻን ባረከ። ወዲያውም ደቀ መዛሙርትን ጠራ። ጴጥሮስ ያገባ ፣ እነ ዮሐንስ ያላገቡ ነበሩ። በዚህም ደናግላንንና ያገቡትን ለቤተ ክርስቲያን  ሹመት ጠራ ። በደብረ ታቦር ሙሴና ኤልያስ ፤ ጴጥሮስና ዮሐንስ ነበሩ ። ሙሴ ያገባ ነው፣ ጴጥሮስም ያገባ ነው። ሁለቱም ሊቀ ነቢያትና ሊቀ ሐዋርያት ነበሩ። ለጴጥሮስ መጽናኛ መሴ መጣ። ኤልያስ ድንግል፣ ዮሐንስም ድንግል ነው። ለዮሐንስ መጽናኛ ኤልያስ መጣ። ኤልያስ ሞትን አልቀመሰም፣ ዮሐንስም ሞት አያይም ተብሎ ተነግሮለታል ።

ጌታችን የዮርዳኖስ ዳርቻ ላይ ቆመ ። እርሱ የሰማዩ የምድሩ ባለቤት ነው። አፈሩ ፣ ከተማው ፣ አገሩ የእኔ ነው እያሉ ሲጋደሉ፣ ሲገፋፉ የከረሙ በደለኞች በዚያ ቆመው ነበር። ትሕትናው ገሠጻቸው ። እያላቸው እንደሌላቸው እንዲኖሩ ፣ በምድር ላይ የሚያስመካ ምንም ነገር እንደሌለ አስተማረ። እንኳን አፈር ምድሩ እጅና እግራችንም የእኛ አይደለም። እንደ ሰው ድU የለም። ከመሬት የተገኘ ነውና ፣ ሰው፦ “መሬቱ የእኔ ነው” ከሚል ፣ መሬት፦ “ሰው የእኔ ነው” ብትል እርግጥ ነው:: ዕራቁታችንን ተወልደን፣ ዕራቁታችንን የምንሄድ ነን። አጭሩን  ዕድሜ በብዙ  ግፍ አቆሸሽነው። ሰው ሆይ ወደ ልብህ ተመለሰ!

ያልተቀበልከው ምን አለ? ሥጋህን ከመሬት ፣ ነፍስህን ከሰማይ ተቀብለኸዋል:: ተገጣጥመህ የቆምህ ፣ አንድ ቀን የምትበታተን ነህ። በእናትህ ማኅፀን ምግብ ለማኝ ነበርህ፣ ስትወለድ ለራስህ አለቀስህ። ከዚህ በፊት የማያውቁህ ሰዎች ግን ስቀው ተቀበሉህ። በነጻ ጡት ጠባህ ፣ ባልሠራኸው ቤት ኖርህ ፣ እንደገና ወራሽ ሆንህ። በነጻ በጥምቀት ወልደ እግዚአብሔር ተባልህ። ሥጋና ደሙን እንዲሁ ተመገብህ ። መምህራን በነጩ ወረቀት በአእምሮህ ላይ እውቀት ጻፉበት። እጅህን ይዘው ፣ ሰበዝን መጠቆሚያ አድርገው ፊደል ያስጠኑህ አንተ ሕፃን ፤ ዛሬ “ደንቆሮ” ብለህ ሰውን ትሳደባለህ ። ዕራቁትህን ተወልደህ ሳለ ድሀ ብለህ ሰውን ትንቃለህ ።

የመድኃኔ ዓለም ትሕትና፡ – ከሰማይ ወደ ምድር መውረዱ ፣ ንጹሕ ሳለ በዮርዳኖስ በኃጢአተኞች መካከል መቆሙ ትሕትናን ያስተምርህ!

ይቀጥላል
የካቲት 5 ቀን 2016 ዓ.ም.
ዲ/ አሸናፊ መኰንን

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ