የትምህርቱ ርዕስ | ሰው ውኃ ነው

የሰው ልጅ በተፈጥሮው የሚበዛው ክፍሉ ውኃ ነው ። ምድርም የሚበዛው አካልዋ በውኃ የተሸፈነ ነው ። ውኃ ዕለታዊ ፍላጎት ነው ። ያለ ውኃ መኖር አይቻልም ። በውኃ ላይ የሚታዩ ጠባያት በሰው ላይ ይታያሉና ሰው ውኃ ነው ። ውኃም ሰውን ገላጭ ነው ። እግዚአብሔር በማኅፀን ውኃን ቋጥሮ ፣ ደምን አርግቶ ፣ አጥንት ሰክቶ ፣ ጅማት አስሮ ፣ ሥጋ አልብሶ ፣ ሕይወት ሰጥቶ ያበጀዋል ። ሰው ውኃ ነው ። ሲወለድም መንገድ ጠራጊው ውኃ ነው ፣ ስሙም የሽርት ውኃ የሚል ነው ፣ በማኅፀንም ልጁ እየዋኘ የሚቆየው በዚህ ውኃ ነው ፣ ውኃው ካነሰ የአካል እክል ይገጥመዋል ። በዚህ ዓለምም የሚቀበለው የመጀመሪያው ስጦታ በውኃ መታጠብ ነው ። ሁለተኛው የእናቱን ጡት ውኃ የሆነው ወተት ነው ።

ውኃ ያረካል

ሰው ውኃ ነውና ያረካል ። ጅምሩ እንደ ውኃ ንጹሕ ሲሆን በመንገዱ ግን የሚቆሽሽ ነው ። በመልአክነት ጀምሮ በመልአክነት የሚፈጽም አለ ፣ በሰይጣንነትም የሚፈጽም አለ ። ዛሬ ሰውን የሚገድለው ሽፍታ ሲወለድ እልል የተባለለት ፣ የደስታ ጥይት የተተኮሰለት ነው ። “እንኳን ማርያም ማረችሽ” የተባለለት ትንሹ ሕፃን ትልቅ አሸባሪ ሆኖ ዛሬ ላይ ያስጨንቃል ። ሰው በፍቅሩ ፣ በስጦታው ፣ በምክሩ ያረካል ። እንደ ጥላ ዐረፍ የምንልባቸው ፣ ስንራቆት የማናፍራቸው ፣ የልባችንን የምንነግራቸው ፣ ጥበባቸው እንደ ጠል ፣ ትምህርታቸው እንደ ካፊያ ፣ ጨዋታቸው እንደ ማር የሆኑ የሚያረኩ ሰዎች አሉ ። በራሳችን ደስ ባይለን ፣ መኖራችን ጥያቄ ቢሆንብን እኛ ግን የሥላሴ ደስታ ነን ። እግዚአብሔር አንተንና አንቺን ሲያይ ደስ ይለዋል ። ሰው ያልፈጠረውን ልጁን ሲያይ ይደሰታል ፣ የምኖረው ለልጄ ነው የሚል ስሜት ውስጥ ይገባል ። እግዚአብሔር ከዚህ የበለጠ የፈጠረውን በጸጋ ልጅ ያደረገውን ሰውን ሲያይ ይደሰታል ። ሰው ልጁን መልኬ ይለዋል ፣ እግዚአብሔርም በመልኩ ፈጥሮ ፣ አርአያውን አልብሶ ፣ በልጅነት ማዕረግ አንግሦ የፈጠረውን ልጄ ፣ መልኬ ፣ ሉሌ ፣ ዓለሜ ይለዋል ። ልጅ ወላጁን የሚያውቀው ሲያድግ ነው ፣ ካላወቀኝማ ብሎ ወላጁ አይጥለውም ፤ እግዚአብሔርም እስክናውቀው የሚታገሥ አምላክ ነው ። ልጅ የወላጁ ፍቅር የሚገባው ቆይቶ ነው ። እግዚአብሔርም በመውደድ ቀዳሚ ሆኖ እስክንወደው ይጠብቀናል ።

ውኃ ለሁሉ ያስፈልጋል

ውኃ ለሰው ፣ ለእንስሳት ፣ ለእጽዋት ሕይወት ነው ። የከተማው እውነተኛ የጽዳት ሠራተኛ ውኃ ነው ። ሰውም ለሁሉ ያስፈልጋል ። ሁሉ ስለ ሰው ተፈጥሮአል ። ሰው ግን ከእርሱ ለሚያንሱ ነገሮች አልተፈጠረም ። እንስሳቱ ፣ እጽዋቱ ፣ ምድርና ሞላው የሰው አደራ ናቸው ። በዚህ ዓለም ላይ ትልቁ የተፈጥሮ ወዳጅም ጠላትም ሰው ነው ። ዓሦች ባሕርን አይበክሉም ፣ ሰው ግን ሊበክል ይችላል ። አእዋፋት አየርን አይጎዱም ፣ ሰው ግን ሊያበላሸው ይችላል ። ሰው ለሁሉ ያስፈልጋል ። ለሰው ፣ ለእንስሳት ፣ ለእጽዋት መኖር አለብን ። አንተ ሆይ አስፈላጊ ፍጡር ነህ ።

ውኃ ይጠሙታል

ሰው ውኃ ነውና ይናፍቃል ። ሕዋሳቶቻችን በሙሉ ይጠብቁታል ። ዓይናችን መልኩን ማየት ፣ ጆሮአችን ድምፁን መስማት ፣ አፍንጫችን መዓዛውን ማሽተት ፣ እጃችን መጨበጥ የሚፈልገው ሰውን ነው ። ይስሐቅ ልጁን ባሸተተ ጊዜ “የልጄ ሽታ እግዚአብሔር እንደ ባረከው እርሻ ሽታ ነው” አለ። (ዘፍ. 27 ፡ 27) ። እንደ ሰው ያለ ጽጌረዳ ፣ እንደ ሰው ድምፅ ያለ ጣፋጭ ሙዚቃ ፣ እንደ ሰው ያለ ሽቱ በዓለም ላይ የለም ። ወዳጁን የናፈቀ ፣ ለማየት ስእለት የተሳለ “ዓይን ነው ዘመዱ” ይላል ። ደግሞም “በዓይኔ አይቼው ብሞት አይቆጨኝም” ይላል ። የናፈቁትን ያዩ መኖርን ይጠግባሉ ፣ ሞትን በጉልበት ይጋፈጡታል ። ሰው ይናፍቃል ። ተናፋቂ ሰዎች ናችሁና ደስ ይበላችሁ ። ሰው የማይናፍቃችሁ ከሆነ ለዚያ ክፉ ጌታ ለገንዘብ ሰግዳችኋል ማለት ነው ። ናፍቆት የመንፈሳዊ ጤንነት መለኪያ ነው ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
መጋቢት 21 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ