መግቢያ » ልዩ ልዩ አንድ » ሰው ውኃ ነው » ሰው ውኃ ነው -6

የትምህርቱ ርዕስ | ሰው ውኃ ነው -6

ውኃ ከላይና ከታች ነው

በሉ እናንተም ሂዱ ፣
እኛም ወደዚያው ነን ፤
ጥንትም መንገደኛ ፊት ኋላ ነው ።

በጥበብ መንገድ የምትሄዱ ፣
በኃይለ ሥላሴ ተራመዱ ፣
አላለቀም ስንቃችሁ ፤
እናንተ በሶ አላችሁ ።

በሶ ለስንቅ የሚሆን ምግብ ነው ። በሶ አላችሁ ከተባሉ ስንቅ አላችሁ የሞት ስጋት የለባችሁም ማለት ነው ። ይህ ሰሙ ሲሆን ወርቁ “በሶ አላችሁ” ወይም በእርሱ አላችሁ ማለት ነው ። ያለነው በእርሱ ነው ፣ የዕድሜ ስንቅ ስላላለቀብን ዛሬን እያየን ነው ። ስንቁ ሲያልቅ መንገደኛው ይሞታል ፣ ሰውም ዘመኑ ሲፈጸም ይሄዳል ። ዕድሜ ከባለጠጋ የማይለምኑት እንጀራ ፣ እግዚአብሔር ያሸከመን ስንቅ ነው ። ይህ ስንቅ ሲያልቅ ማንም አይሞላውም ። ጥበበኛ የሆነ ሰው በሥላሴ ኃይል እንደሚራመድ ፣ ድሉ በጌታ እንደሆነ ያውቃል ። ከፊት የሚሄዱት እየተጫወቱ ፣ በአርአያነትም በዜማም የኋላውን ያጎብዛሉ ። የነፋሱን ኃይል ስለሚሰነጥቁ የኋለኛው ይቀልለታል ፣ ከነፋሱ ትግል ጋር አሸንፈው ዜማ ያቀርባሉ ። ብዙዎቹ ደቃቃ ፣ አሊያም በዕድሜ የገፉ ናቸውና የኋላው ጎበዝ እያፈረ ይከተላቸዋል ። ብዙዎች ሄደዋል ። ደግ ደጉ አልቆ ክፉዎቹ የቀረን ይመስላል ። የፊተኞቹ እምነታቸውም ፣ ቆራጥነታቸውም ፣ የአገር ፍቅራቸውም ፣ የወገን ሰብሳቢነታቸውም እየወቀሰ ያስተምረናል ። ከእነርሱ በላይ ገቢ ቢኖረንም የእነርሱን ያህል መመጽወት አልቻልንም ። መንገደኛ መቀዳደም ወጉ ነው ። ቀደምን ቢሉ እንከተላቸዋለን ፣ ቀደሙን ብንል እንከተላቸዋለን ። አንድ ቤት አለን እዚያው እንገናኛለን ። የሚሰነብት እንጂ የሚቀር በዓለም ላይ የለም ።

ውኃ በደመና ታዝሎ በላይ በሰማይ አለ ፣ በገጸ ምድር ላይ ተንጣሎ ይታያል ። በከርሠ ምድር ተከድኖበት ይገኛል ። ሰውም ጉዞውን ጨርሶ በሰማይ አለ ፣ ራእዩን ለማሳካት በምድር ላይ አለ ። ትንሣኤን እየጠበቀ በከርሠ ምድር ውስጥ ይኖራል ። እነ አብርሃምን ባሰብን ጊዜ ሰማይን እናያለን ፣ ዘመዶቻችንን ባሰብን ጊዜ በምድር ላይ እናያቸዋለን ። የትላንት አበባዎችን የዛሬ አፈሮችን ባሰብን ጊዜ በመቃብር እናገኛቸዋለን ። እነዚያ ሊቃውንት ፣ እነዚያ ቆንጆዎች ፣ እነዚያ ብርቱዎች ለካ የጠፉብን መቃብር ውስጥ ገብተው ነው ! እውነተኛ ትምህርት የሚያስተምሩን የመቃብር ስፍራዎች ናቸው ። የመቃብር ስፍራዎች ታሪክ ይነግሩናል ፣ ታሪክ እንደምንሆንም ያሳምኑናል ።

ሁሉም ወደዚያው ነው ። ሰው መንገደኛ ነው ። መንገደኛ እያረፈ ይጓዛል ። ሰውም ተሹሞ ተሸልሞ መልሶ እስር ቤት ፣ መልሶ ዝቅታ ውስጥ እየገባ ያርፋል ። በሩ ሲከፈት ተመልሶ ይወጣል ። መንገደኛ መንገዱን ጨርሶ ይቀመጣል ፣ ሰውም ዐረፍተ ዘመን ገትቶት በመቃብር ይከተታል ። ውኃ መንገደኛ ነው ፣ ሰውም መንገደኛ ነው ። ውኃ በመንገዱ እያነሰ ይሄዳል ፣ ሰውም በዕድሜው እየደከመ ይመጣል ። ውኃን ሰዎች መንገድ ያስቀሩታል ፣ ሰውም በሰዎች ተሰናክሎ ካሰበበት ሳይደርስ ሊቀር ይችላል ። ውኃ በጋበዙት ስፍራ ጎራ ይላል ። ሳይጠጣ ያጠጣል ። ሰውም በሄደበት ወልዶ ከብዶ ይቀራል ። የተወለደበትን ሳይሆን እንጀራ የበላበትን አገሬ እያለ ይኖራል ። በሰማይ ምስክሮች አሉን ፣ በምድር ወንድሞች አሉን ፣ በመቃብር መምህራን አሉን ። ተስፋን ፍቅርን ፣ ትምህርትን መያዝ የአማኝ መታወቂያው ነው ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ሚያዝያ 7 ቀን 2017 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ