የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ሲመሽ ይመጣል

ዮሐንስ የተወለደው የዘካርያስና የኤልሳቤጥ ጸሎት መልስ ሆኖ ነው ። አንዳንድ ሰው ለሌላው ጥያቄ ፣ ሌላ ሰው ደግሞ ለሌላው መልስ ይሆናል ። ስንፈጠር ግን ለሌሎች ጥያቄ መልስ ሆነን ተፈጥረናል ። እኛ የሥላሴ ዕቅድ ፣ እኛ የጸሎት መልስ ነን ። በዋጋ ተፈጥረን ያለ ዋጋ መኖርን ማራቅ አለብን ። ዮሐንስ እንደ ተወለደ ወላጆቹ በሕይወት አልቆዩም ። እግዚአብሔር ወደዚህ ዓለም ያመጣን ወላጆቻችንን ተማምኖ ሳይሆን የእርሱን የሚያኖር ክንድ ተማምኖ ነው ። በበረሃም በከተማም መመገብ እርሱ ይችላል ። እስራኤልን አርባ ዓመት በበረሃ የመገበ ፣ ዮሐንስን ሠላሳ ዓመት በበረሃ መገበው ። እርሱ በዘመናት ሥራውን የማይዘነጋ ፣ በራሱ መላ የሚያኖር ነው ። መኖር ምሥጢር ነው ። በማይዘራበት ምድረ በዳ የበሰለ ምግብ ፣ ወጪ በበዛበት ቤት ያለ ገቢ ያኖራል ። ከባለጠጎች ይልቅ ድሆችና ካህናተ እግዚአብሔር በተአምራት እንዴት እንደሚያኖር ያውቁታል ።

የእግዚአብሔርን እጁን ያዩ በክፉ ቀን አይሰጉም ። ትላንትን በጉልበቱ እንደ ኖረ ዛሬን ለመኖር ክብደታቸውን አይመዝኑም ። መኖር በእግዚአብሔር እጅ እንጂ በኪስ አይደለም ። ሄሮድስ በላዔ ሕፃናት ነበር ። የተወለደን የሚያንቅ ፣ የሩቁን እያየ የሚነጥቅ ነበር ። ራስ ወዳድነት ከተወለደ ሕፃን ጋር ያጣላል ። ያልበደሉንን እንድንበድል ፣ ሥጋ የለበሱ መላእክትን እንድንጠላ ያደርገናል ። ጥላቻ ስለበቀለብን ነው ወይስ ሰዎቹ ስለሚጠሉ ነው የጠላናቸው ? ብለን ራሳችንን መጠየቅ አለብን ።

ሄሮድስ እንዳይገድለው ሊያተርፉት ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ወደ በረሃ ይዘውት ሄዱ ። በአገራችን ሕፃናት ሳይቀር ያለቁበት ጥቁር ታሪኮች አሉን ። ልጄ ባደገልኝ ሳይሆን ልጄ አደገብኝ ብለው የሚፈሩ እናቶችን አይተናል ። በላዔ ሕፃናት የሆኑ ጨካኝ ገዥዎችን አስተናግደናል ። ገዳይም ሟችም ኢትዮጵያዊ የሆነው ታሪክ የሚያኮራ አይደለም ። ወንድማማች ተጋድለው በመጨረሻ የሚነገር ድል የለም ። ዮሐንስ በእግዚአብሔር ጥበቃ አደገ ። ለእርሱ መሞት የሰጉት ወላጆቹ ሞቱ ። እርሱ ግን አደገ ።

እስቲ አንተ ታውቃለህ የምንከርምበቱን፣
ሰው ኑሮውን እንጂ አያስብም ሞቱን ።

ዘካርያስና ኤልሳቤጥ ልጅን ለእግዚአብሔር ዓላማ ወለዱ ። አስቀድሞ መጥቶ ቢሆን ይጦረናል ፣ ይቀብረናል ብለው ተስፋ ሊያደርጉ ፣ እንደ አብርሃም በልጅ ትምክሕት ሊወድቁ ይችላሉ ። “ልጅህን ሠዋልኝ” ሳይባሉ በሰላም አለፉ ፣ ዐረፉ ። ከነሃይማኖቱ የሞተ ክቡር ነው ። ዮሐንስ ለምን ተወለደ ? ካልን ለወላጆቹ እግዚአብሔር ከሀሊነቱን ሊያሳያቸው ፣ ጸሎታቸው ያኔ መሰማቱን ሊገልጥላቸው ነው ። ዛሬ በምሽት ያገኙት መልስ ገና በተጋቡ ቀን የጸለዩት ልመና መልስ ነው ። የዘመናት ርዝማኔ ጸሎታችንን የማያስረሳው አምላክ ነው ። የሚጦርም የሚቀብርም እግዚአብሔር ነው ። በእግዚአብሔር ሰፊውን ዘመን ኖሮ ለጡረታና ለቀብር መጨነቅ ከንቱ ነው ። ጉልበት በነበረን ጊዜም የኖርነው በራሳችን ሳይሆን በእግዚአብሔር ነው ። ያለ እግዚአብሔር የዘራ ፣ የዘራውን ያገኘ ፣ የጎረሰ ፣ የጎረሰውን የዋጠ ፣ የበላው የተስማማው ማንም የለም ። ሁሉ በአንተ ነው ….።

ዘካርያስና ኤልሳቤጥ በእግዚአብሔር ያላቸውን ትምክሕት ልጅ አልወሰደባቸውም ። ከልጅ በፊት የሚያውቁትን እግዚአብሔር በልጅ አልለወጡትም ። ልጆች ቢኖረንም ባይኖረንም ፈቃዱ የእርሱ ነው ። ተሰጥተውንም በሞት ሊወሰዱ ይችላሉ ። የሰጠው ከወሰደ ፣ እኛ ባለ አደራዎች እንጂ ባለ መብቶች አይደለንም ። ያስቀመጠውን ንብረት ለምን ወሰደ ? ተብሎ አደራ ሰጪ አይከሰስም ። ከአብርሃምና ከሣራ ጋር የሚመሳሰል ታሪክ በዘካርያስ ቤት ተፈጽሟል ። ጨለማ በእግዚአብሔር ዘንድ እንደማይጨልም ፣ ምሽት እግዚአብሔርን ማየት እንደማይከለክል እናስተውላለን ። እርሱ እንኳ በእርጅናችን በሞታችንም ላይ መሥራት የሚችል ነው ። ከጊዜ ውጭ ነውና የጊዜ ህልፈት አያሰጋውም ። እግዚአብሔርን ስጠኝ በሉት እንጂ ሰዓቱ መርፈዱን አትንገሩት ። ገና በሰማይ ይጋብዘናል እያልን በመሸ ቀን አንጠራጠረውም ። ደግሞም ምሽት ያለው ሕሊና ውስጥ ነው ። “እግዚአብሔር ብርሃኔ ነው” ለሚሉ ምሽት ስጋታቸው አይደለም ። ካልመሸ የእግዚአብሔርን ብርሃንነት አናይምና እንኳን መሸ ። አዳምና ሔዋን በገነት መሸባቸው ፣ በቤተ መንግሥቱ የአትክልት ስፍራ የተደበቀ የመጀመሪያው ንጉሥ አዳም ነው ። ሲመሽ ግን መድኃኔ ዓለም መጣ ። ሲመሽ ይመጣል ፣ ደስ ይበላችሁ !

ገሎ ማሥነሣት ታውቃለህ ፣
ወልድ አብነት አለህ ፤
የሴት ልጅ ነኝ ብለህ ፣
ወልድ በራስህ ተኮራህ ፤
አብ አይበልጥም ወይ አባትህ ?
ተለማኝቱ እናትህ ።

ይቀጥላል

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥር 26 ቀን 2016 ዓ. ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ