የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ስለ እኔ

ለ እኔ መረጃ ሳይሆን ለእኔ መርጃ ጸጋ ያለህ ፣ በታቀደ በረከት የባረከኝ ፣ ሳልፈጠር እንጀራዬን ፣ ገና ሳልታይ መኖሪያዬን ፣ በምድር መኖር ሳልጀምር የሰማይ ቤቴን ያዘጋጀህ ፣ የሚያወርስ ወላጅ ባይኖረኝ መንግሥትህን የምታወርሰኝ ደጉ አባቴ ፣ አንተ እግዚአብሔር ነህና አመሰግንሃለሁ ። ሰው በሰው ሁኖ ይጠቃቀማል ፣ እኔ ግን ያላንተ የምጠራው የለም ። ስብከቴ ያላሳመነውን ሕይወቴ እንዲያሳምነው ተንቀሳቃሽ ዐውደ ምሕረት አድርገኝ ። ሞቴን ስመኝ ንስሐ ገብቼ ፣ ማራናታ ስል ወንጌልን ሰብኬ ፣ መንግሥትህ ትምጣ ስልህ ራሴን ክጄ ይሁንልኝ ። ሁሉ ሊሠራው ያለውን የወንጌል ሥራ አንድ ብርቱ አይሠራውምና ሸክምን ለአንዱ ሰጥቶ ከመመልከት አድነኝ ። ማረፍ እያለ ማለፍን የሚመኝ ትውልድህን በቸር አስብ ። አንተ ጌታዬ አቅፈህ የምትወቅስ እንጂ ከስሰህ የምታባርር አይደለህም ። በፍቅር ደሴት በቤተ ክርስቲያን በጥላቻ እንዳልኖር ፣ በጣዕመ ዜማ የሳብኩትን በጭቅጭቅ እንዳላባርር እባክህ እርዳን ። አገልጋዩ በጣዕም እየሰበከ ፣ በሌሊት እየሮጠ ቢሆንም ምእመናን ካልደገፉት የጨለማን ዘመን ማለፍ አይቻልም ። የዘመን ዕዳም ተከታይ ቀድሞ መሪ የቀረ ጊዜ ነውና የሚቀድመውንና የሚከተለውን አስተካክለው ። የካህኑን የእጅ መስቀል ለመሞት እቀድማለሁ የሚያሰኝ ፣ የምእመኑን የአንገት መስቀል ቀንበር ለመሸከም ዝቅ እላለሁ የሚያስብል አድርግልን ። ሁሉ የሚጫንበት መሪ ዕድሜው አጭር ፣ ሁሉን ይሥራ የተባለ አገልጋይ አፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆኑን አስገንዝበን ። ለወንጌልህ ሥራ የዳር ተመልካች ሳይሆን የመሐል ሠራተኛ አድርገን ። አሜን ።

ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 6 ቀን 2014 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ