የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ስብከት አንድ ለቅድስት ድንግል ማርያም የተነገረ ብሥራት ቅዱስ ጎርጎርዮስ ገባሬ መንክራት እንደተረከው -1

እንኳን ለበዓለ ብሥራት አደረሳችሁ !
ዛሬ መላእክት ታላቅ የሆነ ምስጋና በደስታና በሐሴት ይዘምራሉ ። የክርስቶስ የመምጣቱ ብርሃንም በአማኞች ላይ በድምቀት ይበራል ። ዛሬ ለኛ የደስታችን ምንጭ ቀን ነው ። የጽድቅ ፀይ የሆነው ክርስቶስ በመካከላችን ብሩህ በሆነ ብርሃን በርቷል የአማኞችንም ልቡና አብርቷል ። ዛሬ አዳም አዲስ የሆነበት በመላእክት ዝማሬ መንገዱን ወደ ገነት ያቀናበት ቀን ነው የመንፈስ ቅዱስ መምጣት ለሰው ታውቋልና ዛሬ ዓለም በመላው በደስታ ተሞልቷል ። ዛሬ የእግዚአብሔር ጸጋና የማይታየው (አምላክ) ተስፋ ከመታሰብ በላይ በሆነው ተአምር ፈሷል ። ለዘመናት ተሰውሮ የነበረውን ምጢርም ለእኛ ግልጥና የሚረዳ አድርጎታል ። ዛሬ ፈጽሞ የማይጠፋው ጸጋ ጉንጉን ተሸምኗል ። ዛሬ እግዚአብሔር በእርሱ በዓል ሴት የሚያደርጉትን እርሱን በንቃት ማድመጥ ደስ የሚላቸውን ሰዎች ቅዱስ የሆነውን ራስ በዘውድ (ለማስጌጥ) ፈቅዷል ። የማይለወጠውንም እምነት የሚወዱትን እንደ ምርጦቹና እንደ ወራሾቹ ይጋብዛል ይጠራል ። ሰማያዊው መንግትም ረቂቅ የሆኑ ሰማያዊ መዘምራን የሚያገለግሉትን መለኮታዊ አገልግሎት ለመምሰል የሚወዱትን ለመጥራት ይፈጥናል ዛሬ “ሰማያት ደስ ይበላቸው ፥ ምድርም ሐሤትን ታድርግ ፤ ባሕርና ሞላዋ ይናወጡ ፤ በረሃ በእርስዋም ያሉ ሁሉ ሐሤትን ያድርጉ ፤ የዱር ዛፎች ሁሉ በዚያን ጊዜ በእግዚአብሔር ፊት ደስ ይላቸዋል ፤ ይመጣልና” (መዝ 95(96)፥11-13) ያለው የዳዊት ቃል ተፈጽሟል ። ዳዊት “ዛፍ” የሚል ቃል ጠቅሷል በተመሳሳይ መልኩ የጌታ መንገድ ጠራጊም እነርሱን እንደ ዛፍ ይናገራል “እንግዲህ ለንስሐ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” (ማቴ 3፥8) ወይም ደግሞ ለጌታ የሚገባ (ፍሬ) አድርጉ (ማለት ነው) ። ነገር ግን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በእርሱ ለሚያምኑት ሁሉ ዘላለማዊ የሆነ ደስታን ቃል ገብቷል ። እንዲህ ብሏልና፡- “አያችኋለሁ ልባችሁም ደስ ይለዋል ፥ ደስታችሁንም የሚወስድባችሁ የለም ።” (ዮሐ. 16፥22)
ዛሬ በፈቃዳቸው ተስፋቸውን እንደ ማተም በክርስቶስ ላይ (ያተሙ) የክርስቲያኖች ዝነኛና ገናና የሆነው በቃልም የማይገለጠው ምጢር በግልጥ ታውጆልናል ። ዛሬ በእግዚአብሔር ፊት የሚቆመው ገብርኤል (ሉቃ 1፥19) “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ” (ሉቃ 1፥28) የሚለውን ደስ የሚያሰኘውን ብራት ይዞ ወደ ንጽት ድንግል መጣ ። እርሷም በልቧ ይህ እንዴት ያለ ሰላምታ ነው ብላ አሰበች ። መልአኩም በፍጥነት እንዲህ አለ፡- “ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና ማርያም ሆይ አትፍሪ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው።”  ስለዚህ ትፀንሻለሽ ወንድ ልጅም ትወልጃለሽ ስሙንም ኢየሱስ ትይዋለሽ ። እርሱም ታላቅ ይሆናል የልዑል ልጅም ይባላል ። ጌታ እግዚአብሔርም የአባቱን የዳዊት ዙፋን ይሰጠዋል በያዕቆብ ቤትም ለዘላለም ይነግል ። ለመንግቱም ፍጻሜ የለውም ። ማርያምም መልአኩን መልሳ እንዲህ አለችው “ወንድ አላውቅምና ይህ እንዴት ይሆንልኛል?” [1] ድንግል እንደሆንሁ እቀጥላለሁን ? የድንግልናን ክብር አላጣምን ? በእነዚህ ነገሮች ግራ እየተጋባች ሳለ ወያውመልአኩ መልእክቱን ጠቅለል አድርጎ በአጭሩ አቀረበላት ንጽት የሆነችውድንግልም እንዲህ አላት፡- “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል” (ሉቃ 1፥35)። በትትና ፣ ጸጋ ከትውልዶች ሁሉ ንጽት ማርያምን ብቻ መረጣት ። እርሷ በሁሉም ነገሮች ውስጥ በእውነት ብልህና አዋቂ እንደሆነች አስመስክራለች። በትውልዶች ሁሉ እንደ እርሷ ያለ ሴት አልተወለደም ። እንደ ጥንቷ ድንግል ሔዋን አይደለችም ። እርሷ (ሔዋን) ግድ የለሽ በሆነ ልቡና በገነት ብቻዋን በዓል እያከበረች የክፋት ሁሉ ፈጣሪ የሆነውን እባብ (ዲያብሎስ) ሳብ ያለማስተዋል ሰማች ። በዚህም በልቡናዋ ሳብም ሳተች ። ያ አታላይ (ዲያብሎስ) ሞት ቀላቅሎ መርዙን ተፋ ወደ ዓለምም አስገባው በዚህም ለቅዱሳኑ ሁመከራ መጣ ። ነገር ግን የመጀመሪያዋ እናት ውድቀት በድንግል ማርያም ብቻ መፍትሔ አገኘ ።
ሆኖም ቅድስት አስቀድማ የላከው ማን እንደሆነ ፣ ስጦታው ምን እንደሆነ መልእክቱን ያመጣው ማን እንደሆነ ሳታውቅ ስጦታውን ለመቀበል ብቁ አልነበረችም ። ቅድስቷ ግራ በመጋባት ከራሷ ጋር ይህን ካወጣች ካወረደች በኋላ መልአኩን እንዲህ አለችው “እንዲህ ባለ መልክ ለእኛ በረከት ከወዴት ነው ያመጣህልን ? ከምን መዝገብ የዓለም ሉል ለእኛ ተላከ ? ስጦታው በእኛ ላይ ያለውን ዓላማ ያገኘው መቼ ነው ? ከሰማይ መጣህ ሆኖም ግን በምድር ትራመዳለህ ! ሰው ትመስላለህ ሆኖም ግን በሚያንጸባርቅ ብርሃን ደምቀሃል።” ቅድስት እነዚህን ነገሮች አሰበች መልአኩም እንዲህ ባለ አመክንዮ የተፈጠረውን ችግር እንዲህ ብሎ ፈታው “መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል ። ማርያም ሆይ አትፍሪ የመጣሁት በፍርሃት ልሞላሽ ሳይሆን ፍርሃትን ለማራቅ እንጂ ። ከእግዚአብሔር ዘንድ ጸጋን አግኝተሻልና ማርያም ሆይ አትፍሪ ። ጸጋ በፈጥሮ ግ አይራምና ጸጋን በተፈጥሮ ግ አትለኪ ። ድንግል ሆይ (የብሉይ ኪዳን) አባቶችና ነቢያት ያላወቁትን አውቀሻል ። ድንግል ሆይ እስካሁን ድረስ ከመላእክት ተሰውሮ የነበረውን ነገር አውቀሻል ። ንጽት ሆይ (በመንፈስ ቅዱስ) የተነቃቁ ዘማሪዎች እንኳን ይሰሙት ዘንድ ያልተገባቸውን ሰምተሻል ። ሙሴ ፣ ዳዊት ፣ ኢሳይያስ ፣ ዳንኤልና ሁሉም ነቢያት ስለ እርሱ ተነበዩ ። እንዴት እንደሚወለድ ግን አላወቁም ።
ኦ! ንጽት ድንግል ሆኖም ግን አንቺ ብቻ እነዚህ ሁሉ ያላወቁትን (ምጢር) ተቀበልሽ የነዚህንም መረት ተማርሽ ። መንፈስ ቅዱስ ባለበት ሁሉም ነገሮች ተስማምተው ይኖራሉ ። አምላካዊ ጸጋ ባለበት ሁሉም ነገር ከእግዚአብሔር ጋር ይቻላል ። መንፈስ ቅዱስ በአንቺ ላይ ይመጣል፥ የልዑልም ኃይል ይጸልልሻል ስለዚህ ደግሞ ከአንቺ የሚወለደው ቅዱስ የእግዚአብሔር ልጅ ይባላል።
እርሱ የእግዚአብሔር ልጅ ከሆነ ከአብ ጋር በባርይ የሚተካከል ከእርሱም ጋር በቅድምና የነበረ እግዚአብሔር ነው ። በእርሱም አብ ሁሉንም መገለጦች በምልአት አካቷል ፤ እርሱ የአብ መልክ ነው በመንጸባረቁም የአብ ክብር ይበራል ። ከዘላለማዊው ምንጭ እንደሚገኝ ልክ እንደዚሁ ሁል ጊዜ ከሚመነጨውና ከሚፈሰው ዘላለማዊና ሕያው ከሆነው የዓለም ብርሃን፣ ዘላለማዊና እውነት የሆነው ክርስቶስ አምላካችን ይወለዳል ። ነቢያት የሰበኩለት ይህ ነው “የወንዝ ፈሳሾች የእግዚአብሔርን ከተማ ደስ ያሰኛሉ” (መዝ 45(46)፥4)። (ደስ የሚያሰኘውም) አንድን ከተማ ብቻ አይደለም ነገር ግን ሁሉንም ከተሞች እንጂ ። አንድን ከተማ ደስ እንደሚያሰኘው መላውን ዓለምም እንዲሁ ያደርጋል ። በእርሷ ዘንድ የጸጋ ሙሉ መዝገብ ነበርና በሚገባ ሁኔታ መልአኩ በመጀመሪያ ቅድስት ድንግል ማርያምን እንዲህ አላት ፡- “ደስ ይበልሽ ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው” (ሉቃ 1፥29) ። ከትውልድ ሁሉ እርሷ ብቻ በሥጋም በመንፈስም ንጽት ድንግል ኖራለች ። ሁሉንም በቃሉ የሚይዘውን እርሷ ብቻ ያዘቸው ። የሚያስደንቀው የዚህች ቅድስት ውበት ብቻ አይደለም ነገር ግን የነፍሷ ውበትም እንጂ ። ስለዚህ መልአኩ አስቀድሞ ሰላምታ ሰጣት “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው። (ሉቃ 1፥29) በምድርም ባል የለሽም።” የቅድስና ጌታ ፣ የንጽና አባት ፣ የያውነት ባለቤት ፣ ነፃነት ሰጪ ፣ የድኅነት ባለቤት ፣ የእውነተኛ ሰላም መጋቢና ሰጪ ከድንግል መሬት ሰውን የፈጠረው ከአዳምም ጎን ሔዋንን ያስገኘው እርሱ ራሱ ከአንቺ ጋር ነው። ይህ ጌታ ከንቺ ጋር ነው ። በሌላ መልኩ (እርሱ) ከአንቺ ተገኘ።
ስለዚህ የተወደዳችሁ ወንድሞቼና እህቶቼ መልአካዊውን ፍጽምና እንውሰድባለን አቅም ሁሉ የሚገባውን ምስጋና “ደስ ይበልሽ፥ ጸጋ የሞላብሽ ሆይ፥ ጌታ ከአንቺ ጋር ነው። (ሉቃ 1፥29) እያልን እንስጥ ። የእግዚአብሔር ጸጋ እርሱ በሚያውቀው አንቺ ላይ ለማደር መርጦሻልና በእውነት ደስ ይልሽ ዘንድ ይገባል ። የክብር ጌታ ባሪያው ላይ አደረ ። “ውበትህ ከሰው ልጆች ይልቅ ያምራል” (መዝ 44(45)፥2) (የተባለለት እርሱ) ውብ ከሆነችው ድንግል ጋር ፣ ሁሉንም ነገር የሚቀድሰው እርሱ ንጽት የሆነችው ላይ (አደረ)። እግዚአብሔር ከአንቺ ጋር ነው ። የመለኮት ሙላት በእርሱ ያለው ፍጹም ሰው የሆነውም ከአንቺ ጋር ነው ። ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የሚያምኑበትን ሁሉ ብርሃን የሚያደርግ የብርሃን ምንጭ (ከአንቺ ጋር ነው።) ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የጽድቅ ፀይ ፣ ንጹየሆነው የይወት አበባ መውጫ ! የሆነው መድኅን ጥዑም መዓዛ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! ሁል ጊዜ የሚያብበው ወይን ፣ የሚያከብሩሽን ሰዎች ነፍስ ደስ የምታሰኚ ጸጋን የተሞላሽ ሆይ ደስ ይበልሽ ! የማይነጥፈውን ፍሬ ያፈራሽልን መልካሟ ምድር በእግዚአብሔር ዘንድ ሞገስን አግኝተሻልና ደስ ይበልሽ !
ይቀጥላል
ታሕሣሥ 22 ቀን 2011 ዓ.ም.


[1] ሉቃ 1፥29
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ