ለጌታችን ስደት ትልቅ ምክንያት የነበረው ሄሮድስ ሥልጣን አፍቃሪ ፣ አስመሳይ ፣ ተንኮለኛ ፣ የሕፃናት ገዳይ ፣ ሃይማኖት ያለው መሳይ ፣ ለሮማውያን ሰግዶ/ምቹ ሆኖ ሥልጣንን ያገኘ ፣ ልጆቹም በእርሱ መንገድ ሄደው የተበከሉበት ሰው ነው ። የካህናት አለቆችና የሕዝቡ ጻፎችም ለጌታችን ስደት ምክንያት ነበሩ ። እነዚህ በንቀት የተሞሉ ፣ ክርስቶስ በቤተ ልሔም እንደሚወለድ ትንቢትን ጠቅሰው እየተናገሩ የሆነውን ለማየት አልሄዱም ። የንጉሡ መደንገጥ ፣ የሰብአ ሰገል መምጣት አልነቀነቃቸውም ። እንዲሰግድለት ሳይሆን እንዲገድለው ትንቢት ጠቅሰው ነገሩት ። የዓለም ሁኔታ ሲለወጥ እነዚህ ካህናት አይደነግጡም ። ከሩቅ የመጡ የእነርሱን መጽሐፍ ሲያከብሩ ብዙም አይገርማቸውም ። ንጉሡን ያስደነገጠ ነገር ምንድነው ( ለማለትም ቸልተኛነታቸው ከለከላቸው ። እየጠቀሱ ነዋሪዎች ነበሩ ። ቅዱስ ማቴዎስ ራሱ አይሁዳዊ ሲሆን ወንጌሉን የጻፈው በቀጥታ ለእነርሱ ነው ። መልእክቱም አልተቀበላችሁትም የሚል ነው ። ስለ ክርስቶስ በመስቀል ላይ በሠራችሁት ስህተት ብቻ ሳይሆን ልደቱም ላይ ያደረጋችሁት ቸልታ ተገቢ አይደለም እያላቸው ነው ። ሰው ራሱንም ለማየት የወንጌል መስተዋት ያስፈልገዋል ። ስህተቱን ያላመነም የክርስቶስ መድኃኒትነት አይረባውም ። መድኃኒት ከእምነት ጋር በጣም የተያያዘ ነው ። መጀመሪያ በሽታን ቀጥሎ መድኃቱን ማመን ያስፈልጋል ።
ሄሮድስ ለመግደል አሰበ እንጂ ተሳክቶለት ጌታን አልገደለውም ። ንቀትና ቸልታ የሞላባቸው የአይሁድ ካህናት ግን በመጨረሻ ጌታን ሰቅለውታል ። ከአላውያን ነገሥታት ፣ ከጨካኝ መሪዎች ይልቅ ክርስቶስን ለመስቀል አቅም ያለን እኛ አገልጋዮች ነን ። አገልጋይ ስንሆን በንቀትና በቸልተኝነት እንዳንያዝ መጠንቀቅ አለብን ። የዚህ ነገር መጨረሻው ክርስቶስን መስቀል ነውና ። የአይሁድ ካህናትን ጥቅስን ያውቃሉ ፣ የሚጠቅሱት ግን ሰዎች ለክርስቶስ እንዲሰግዱ ሳይሆን እንዲገድሉት ነው ። ከእግዚአብሔር የመጣውን ግን ማጥፋት አይቻልም ። ጥቅሶቻችን ዛሬስ የሰላም መሣሪያ ናቸው ወይ ( ብለን መጠየቅ አለብን ። መጽሐፉም ውሾች ይላል በማለት ውሻ ብሎ የመሳደብ ጥሙን የሚያረካ አለ ። በደርግ ዘመን የሚወደድ ጥቅስ ነበር ። “በሦስት ነገር ምድር ትናወጣለች፥ …ባሪያ በነገሠ ጊዜ…” የሚል ነው ። ይህን ጥቅስ የወሰዱት ከምሳ. 30፡21 ላይ ነው ። ይህን ጥቅስ እየጠቀሱ ገዥውን የሚሳደቡ ፣ ለምን ሲባሉ በጥቅስ ውስጥ የሚደበቁ ነበሩ ። የእግዚአብሔር ቃል ለአምልኮተ እግዚአብሔር ብቻ መጠቀስ አለበት ።
በአይሁድ ላይ ዘራቸውን ለማጥፋት ሦስት ጊዜ ያህል ሞት ታውጆ ነበር ። በግብፅ በፈርዖን ፣ በፋርስ በሐማ ፣ በገዛ ምድራቸው በሄሮድስ ሞት ታውጆባቸው ነበር ። ዓላማው መሢሑ የሚወጣበትን ዘር አጥፍቶ የዓለምን መዳን ማስቀረት ነበር ። ሰይጣን የሚዋጋው የሰውን ባለጠግነት ሳይሆን መዳኑን ነው ። ሰብአ ሰገል ሁለት ዓመት ሙሉ በፍለጋ ላይ ነበሩ ፣ የፍለጋ ማብቂያው ክርስቶስን ሲያገኙ ሆነ ። ሰዎች ሰባ ሰማንያ ዓመት አስሰው የሚያርፉት እርሱን ሲያገኙ ነው ። እውነተኛው የሕይወት ምዕራፍ ክርስቶስ ነው ። ድንግል ማርያምና አረጋዊው ዮሴፍ በቤተ ልሔም ለሁለት ዓመታት ያህል የቆዩት በናዝሬት ነዋሪዎች ዘንድ የክርስቶስ ያለ አባት መወለድ ያሥነሣቸውን ትችት ለመሸሽ ነው ። ዮሴፍ ሙያው አናጢ ነበርና የትም ለመቆየት የሚሆን ሙያ ነበረው ። ስለ ክርስቶስ አረጋዊው ዮሴፍም ድንግል ማርያምም በሰማይ መገለጥ አርፈዋል ፣ ናዝሬት ግን ይተራመሳል ። እኛ ዐርፈን ሰዎች ሊተራመሱ ፣ ከተማው ሊያውካካ ይችላል ። ትንሽ መሰወር ተገቢ ሊሆን ይችላል ። ደግሞም ሁሉ ቦታ እንጀራ የሚያበላንን ሙያ መያዝ መልካም ነው ። አናጢነት መቼም ተፈላጊ ፣ የትም ቦታ ሥራ ያለው ሙያ ነው ።
ሰብአ ሰገል ከአሕዛብ ቀዳሚ አማንያን ሆኑ ። በጥበባቸው ሳይሆን በእምነታቸው የክርስቶስ ተከታይ ሆኑ ። ኮከቡ ለጥቂት ጊዜ ቢሰወራቸው ሰው ጥየቃ ገቡ ። ነገሩ ንጉሥ ዘንድ ደረሰ ። ኋላ ላይ ለክርስቶስ ስደት ምክንያት ሆነ ። ምሥጢርን መጠበቅ ተገቢ ነው ። ነገ ሊነገር የሚገባውን ዛሬ ላይ መናገር ራሱን የቻለ ጉዳት አለው ። ምሥጢር ሦስት ነገሮች ይፈልጋል፡- ሰው ፣ ሁኔታና ጊዜ ። ምሥጢር በባለቤቱ ልብ ውስጥ ሳለ ጠባቂው ነው ፣ ከእርሱ ከወጣ በኋላ ግን ካቴና ይዞ የሚከተለው ፖሊስ ነው ። እግዚአብሔር በሁሉ ይምራል ። ሰብአ ሰገል ለጌታችን ያቀረቡት እጅ መንሻ በማግሥቱ ለሚመጣው ስደት የስንቅ መግዣ ነበር ። እግዚአብሔር አስቀድሞ ያዘጋጃል ። ሳይደግስ አይጣላም ይሉታል ። ደግሶ አብልቶ የሚጣላ ምን ዓይነት ወዳጅ ይሆን ! የሚመጣውን አይቶልም ያዘጋጀልን ብዙ ነገር አለ ! ጥንቃቄን በማጣት ፣ ምሥጢርን ባለመጠበቅ ፣ የቤተ ክርስቲያንን ተልእኮ ለማን መንገር እንዳለብን ባለመገንዘብ የመከራ አምጪ ልንሆን እንችላለን ።
የሚገርመው ወደ ስደተኛዋ አፍሪካ ጌታ የዛሬ ሁለት ሺህ ዓመት በፊት መሰደዱ ትልቅ ትርጉም አለው ። አፍሪካውያን በስደት እየባከኑ ነው ። ብዙዎች በራቸውን ይዘጉባቸዋል ። የጌታችን ስደት ለስደተኞች መጽናኛ ነው ። ስደተኞች ሃይማኖት በጠፋበት የሰለጠነው ምድር የሃይማኖትን መልክ እያሳዩ ፣ በረከት እያመጡላቸው ነው ። ስደተኞች በረከቶች ናቸው ። ሰብአ ሰገል የአገርህ ሰው ካልተቀበለህ እኛ እንውሰድህ አላሉም ። የእግዚአብሔር መርሐ ግብር ከሆነ የንጉሥ ወዳጅነትም ሊረዳን አይችልም ። ንጉሥ የቆረጠው እጅ ካለ ይቆጠራል እንዲሉ ከእግዚአብሔር ከሆነ ማጣቱም ማግኘት ነው።
ስደተኛውን ጌታ ፣ ስደተኛይቱን ድንግል ስናስብ ስደተኞችን በማስጠጋት ሊሆን ይገባዋል ። ስደተኞች አካላዊ ፣ ስሜታዊ ፣ ሥነ ልቡናዊ ፣ ሃይማኖታዊ ጫና ይደርስባቸዋል ። ቤተ ክርስቲያን እየናፈቁ ላያገኙ ፣ የሃይማኖት አባት እያማራቸው ብርቅ ሊሆንባቸው ይችላል ። በስደት ምድር ላይ ለኢትዮጵያውያን መጽናኛ የሆኑ አባቶችና አገልጋዮች ሊመሰገኑ ጊዜው አሁን ነው ።
ከእውነት የተሰደድነውን በስደቱ ይመልሰን !
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ጥቅምት 12 ቀን 2018 ዓ.ም.