የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ስጦታን ሰጠ

 
“ስለዚህ፦ ወደ ላይ በወጣ ጊዜ ምርኮን ማረከ ለሰዎችም ስጦታን ሰጠ ይላል ።” ኤፌ. 4 ፡ 8 ። 
 
ጌታችን ወደ ምድር ወረደ ። ከምድር ሳይለይ ወደ ምድር መጣ ። ምድርን ሳይተዋት ወደ ላይ ዐረገ ። ከሰማይ ሥጋን ይዞ አልመጣም ፣ ወደ ሰማይ ሲወጣም በመለኮትነቱ ብቻ አልወጣም ። ሥጋን ይዞ አልመጣም ፣ ሥጋንም ጥሎ አልወጣም ። ወደ ምድር በመምጣቱ አምላክ ሰው ሆነ ። ሥጋም ከመለኮት ጋር ቢዋሐድ ሰው አምላክ ሆነ ። የሰው ርስት የሆነውን በረትን የወረሰ አምላክ ፣ የመለኮት ርስት የሆነውን ዙፋንን ለሥጋ ሰጠ ። ከላይ ወደ ታች ሲወርድ ከሦስትነቱ አልጎደለም ። ወደ ላይ ሰያርግም በሦስትነቱ ላይ አራትነትን አልጨመረም ። ከላይ ሳይጎድል ፣ ከሥር ሳይጨመር አምላክ ሰው ሆነ ። ፈጣሪ ፣ አምላክ ፣ ያህዌ ፣ አዶናይ ፣ ኤልሻዳይ የተባለው  በለበሰው ሥጋ ኢየሱስ ፣ አማኑኤል ፣ ክርስቶስ ፣ የሰው ልጅ ተባለ ። ወደ ላይ ወጣ መባሉ ሥጋ መልበሱን ያሳያል ። መለኮት ወጣ ወረደ የማይባል ሁሉ በሁሉ ነውና ። እርሱ ወደ ላይ ለመውጣት እስከ መቃብር እስከ ሲኦል መውረድ ነበረበት ። ለእኛም ከፍ የማለት ምሥጢሩ እጅግ ዝቅ ማለት መሆኑን አስተማረን ። ከሕመሙ ፈውስን ፣ ከስብራቱ ጠገንን የሚጠብቀው ዓለም ከሞት ትንሣኤን መጠበቅ ተስኖት ነበረ ። ጌታችን ወደ ላይ በማረጉ ግን ከዝቅታው ከፍታው እንደሚበልጥ አበሰረን ። በርግጥም ከተዋረድነው የምንከብረው ፣ ካጣነው የምናገኘው ይበልጣል ። ወደ ላይ ለመውጣት ግን ወደ ታች መውረድ ሕጉ ነው ። ክብርን አስደሳች የሚያደርገው የተዋረዱበት መጠን ነው ። ሕይወት አንድ መልክ ብቻ ቢኖራት ትሰለች ነበር ። ብርሃንና ጨለማ ናት ። ከጨለማው በኋላ ብርሃን ይከተላል ። 
 
ብዙዎች ወደ ላይ ለመውጣት እልፎችን ረግጠዋል ። የቆሙትም በሌሎች ጀርባ ላይ ነው ። ወደ ላይ ከወጡ በኋላም የጨበጡትን መሰላል ይረግጡታል ፣ ሲከፋም ይገፈትሩታል  ። መሰላል በመጀመሪያ በእጅ ይጨብጡታል ። ከፍ ሲሉ በእግር ይረግጡታል ። መጨረሻ ላይ ጥለውት ይሄዳሉ ። የሚያስታውሱት ለመውረድ ሲቃረቡ ነው ። እየጨበጡ ያለፉትን ሕዝብ የረገጡ ፣ ወተት በቧንቧ እናቀርባለን ብለው ደም በቧንቧ ያቀረቡ ብዙ የዓለም መሪዎች ነበሩ ፣ አሉ ። ያከበራቸውን ሕዝብ የረሱ ፣ በብዙኃን ጀርባ ላይ ወጥተው ብዙኃኑን ትተው ከጥቂቶች ጋር የጨፈሩ አያሌ ናቸው ። ለሞት የፈለጉትን ሕዝብ ለማዕድ ያልጋበዙት ፣ ረስተውት ኖረው መጨረሻቸው ሲቃረብ እንደገና ድረስልን ያሉት ብዙ ናቸው ። “ከታሪክ የተማርኩት ሰው ከታሪክ እንደማይማር ነው” ያለው ሰውዬ እውነቱን ነው ። 
 
ምርኮ የጦርነት መጠናቀቅን የሚያበስር ነው ። ምርኮ ከፊቱ ጦርነትና ድል አለው ። ምርኮ ቀጣዩን ዘመን የሚያበሥር ነው ። ምርኮ ተዋጊዎችና ደጀን ሕዝብ ስጦታን የሚከፋፈሉበት ፣ በጠላት እጅ የነበረውን በራሳቸው እጅ አድርገው ባለጠጋ የሚሆኑበት ነው ። ምርኮ በአንድ ዓይን እያለቀሱ በአንድ ዓይን የሚስቁበት ነው ። በአንድ ዓይን ማለቀሳቸው የተከፈለውን መሥዋዕት ብርቱ መሆኑን ፣ በአንድ ዓይን መሳቃቸው ስጦታውና በረከቱ መብዛቱ ነው ። ያለ ጦርነት ግን ድል የለም ። ጦርነቱ በቀራንዮ ፣ ድሉ በጎልጎታ ፣ ምርኮው በደብረ ዘይት ሽቅብ ወደ ላይ ሲያርግ ነው ። በምርኮ ጠላትን አሰልፈው ይነዱታል ። ጠላት የነበሩትን የአዳምን ልጆች በትከሻው ተሸክሞ ባሕረ ሞትን ያሻገረው ፣ ጠላት የሆነውን የአዳምን ባሕርይ ባሕርዩ ያደረገው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ለዘላለም ድንቅ ነው ። እርሱ የተዋጋው ከዘላለማዊ ጠላቶቻችን ከሲኦል አበጋዞች ጋር ነው ። ምርኮ ለተዋጉት ወታደሮች ነው ። ጌታችን ግን ብቻውን ስለ እኛ ሞተ ። የሞቱ ፍሬ የሆነውን ጸጋ መንፈስ ቅዱስን የሰጠው ለተዋጉት ሳይሆን ለተማረኩት ለሰው ልጆች ነው ። 
 
የማረከው የሰው ልጆችን ሲሆን ስጦታውም የተሰጠው ለሰው ልጆች ነው ። እነግሥ ብሎ ያልሞተ ፣ እከብር ብሎ ያልተዋጋ አምላክ ቡሩክ ነው ። ጌታችን ስለ እኛ ተዋጋ ፣ አሸነፈ ፣ ምርኮን ማርኮ ሲኦልን በዘበዘ ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስንም ሰጠ ። ስጦታንም የሰጠው ለሰዎች ነው ። ይህም ሁለት ፍቺ አለው ። የመጀመሪያው ለሰው ዘር ሁሉ ነው ። በስጦታው አድልኦ የለበትም ። ሁለተኛው ለሰዎች ሰጠ ። ይኸውም በግብራቸው እንስሳት ፣ አራዊትና ውሉደ ዲያብሎስ የሆኑ አሉ ። እርሱ ለሰዎች ስጦታን ሰጠ ። ስጦታን ለመቀበል ሰው መሆን ያሻል ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስን ያገኘነው እርሱ በሞተበት ሥጋ ወደ ላይ ሲያርግ ፣ የተቸነከረ እጆቹንና እግሮቹን እያሳየ በዙፋኑ ሲቀመጥ ነው ። በክብር ዙፋኑ ሲቀመጥ ስጦታ በዛ ። የሰው ኃጢአት ወልድን ሰው አደረገው ፣ የወልድ መክበር ጸጋ መንፈስ ቅዱስን አጎረፈው ። ጸጋ መንፈስ ቅዱስ እንዲለቀቅልን ክርስቶስ በልባችን ዙፋን መቀመጥ አለበት ። 
 
ሁልጊዜ መስጠት ልማዱ ነው ። ሙሉ አካልን የሰጠ ፣ ለዓይን ማየትን የፈቀደ ፣ ከእናት ከአባት በፊት አይቶን በማኅፀን የመገበን ፣ የዛሬዋን ብሩህ ቀን ያደለን ፣ በቀራንዮ ነፍሱን የሰጠን አሁን ደግሞ ባረገ ጊዜ ስጦታን ሰጠን ። በዓለ ሃምሳ ይህን ስጦታ የተቀበልንበት ፣ የቤተ ክርስቲያን ልደት የተከበረበት ቀን ነው ። በበዓለ ሃምሳ የወረደው መንፈስ ቅዱስ ዛሬም በቤተ ክርስቲያን አለ ። በቃለ እግዚአብሔር በምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ፣ በመምህራን እረኝነት በኩል ዘወትር ይባርከናል ። ለበጉ ሰርግም ያቆነጀናል ። 
 
ወደ ላይ የወጣው ኢየሱስ ይመለሳል ። ምን ይዘን እንቀበለዋለን ? እርሱ ሌላም አይሻም ፣ የሰርግ ልብሳችንን ለብሰን እንጠብቀው ። ሰርግ ልብስ ቢለብሱት ክብሩ ለራስ ነው ። ለራሳችን ብሎ ትእዛዙን የሰጠን ቡሩክ ነው ። 
 
በበረከት ዋሉ !
 
 ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
 ነሐሴ 27 ቀን 2013 ዓ.ም.
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ