የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቀራጩ ማቴዎስ /2/

/ማቴ. 9፡9-13/
ማቴዎስም ሁሉን ይዞ ሳይሆን ሁሉን ጥሎ ተከተለው ። ሁሉን ይዘው የሚከተሉ በቤተ ክርስቲያን ለሚነሣ ሁከት ምክንያት ናቸው ። ሁሉን ጥለው የሚከተሉ ግን ዓለምን የናቁ ሰላማውያን ናቸው ። ማቴዎስ ሁሉን ትቶ ተከተለ ። ማቴዎስ ሕይወትን ለዋጭ ፣ አድራሻን ቀያሪ የሆነውን መለኮታዊ ጥሪ ሲሰማ ያ የብሉይ ኪዳን ነቢይ ኤልሳዕ ትዝ አለው ። ኤልሳዕ በእርሻ ላይ ሳለ በነቢዩ ኤልያስ በኩል ጥሪ የደረሰው ገበሬ ነው ። እርሱም ከአሥራ ሁለት ጥማድ በሬ ሁለቱን አርዶ ፣ የቁም ተዝካሩን አውጥቶ ፣ ዓለምን ተሰናብቶ እግዚአብሔርን ተከተለ ። 1ነገሥ. 19፡19-21 ። ማቴዎስም ታላቅ ግብዣ አድርጎ ዓለምን ተሰናብቶ ፣ ጌታውን አመስግኖ ለመከተል ፈለገ ። ሲፋታ የሚደግስ የለም ፣ ማቴዎስ ግን ከዓለም ሲፋታ ደገሰ ። ቅድም የምድራዊ መንግሥት ሠራተኛ ነበር ፣ አሁን የሰማያዊ መንግሥት ሠራተኛ ሆነ ። የቀራጭነት ልምድ ለደቀ መዝሙርነት አይረዳም ፤ ጌታ ግን ከአዲስ ይጀምራል ። ሥራውን ብቻ ሳይሆን ዜግነትም ፣ ንጉሥም ቀየረ ። የእግዚአብሔር ጥሪና እውነተኛ ንስሐ ታሪክን ይለውጣል ። በመንግሥቱ የጋበዘውን ጌታ በቤቱ መጋበዝ ፈለገ ። ተጠልቶና ተንቆ ነበርና በቤቱ ቢጤዎቹ እንጂ ደህና የሚባሉ ሰዎች አይገቡም ነበር ። የቀራጮች ማኅበረተኛ ነበር ። ከዚያ ለመውጣት አቅምም ዕድልም አልነበረውም ። ጌታ ግን አዲስ መንገድን አሳየው ። ድኅነተ ነፍስ ብቻ ሳይሆን አእምሮን የማይቆረቁር ተልእኮ ተቀበለ ።

ማቴዎስም ጌታንና ደቀ መዛሙርቱን ብቻ ሳይሆን የከተማዋን ኃጢአተኞችና ቀራጮች ሰበሰበ ። እኔን እንዳዳነ ያድናቸው ብሎ ነው ። የክርስቶስ ማዳኑ ለማቴዎስ ብቻ አልነበረም ። ክርስቶስ ለሁሉ ቢሰጡት የማይቀንስ ሀብት ነው ። ቀራጮች በነፍሴ ለምጻም ነኝ በሚል ሒሳብ ራሳቸውን ያገለሉ ፣ ሰውም ያገለላቸው ፣ ከሌላ ቀራጭ ጋር ካልሆነ ዕድርና እቁብ የሚጠጡ አልነበሩም ።በእያንዳንዱ እንቅስቃሴአቸው ፍርሃት ባይርቃቸውም ክርስቶስን ግን ልበ ሙሉ ሁነው ቀረቡት ። በአንድ መንገድ ከሌላው አይሁዳዊ ጋር የማይሄዱ በአንድ ገበታ ከክርስቶስ ጋር ታደሙ ። ንጽሕናው የሚያሸማቅቅ ፣ ቅድስናው የሚገፈትር አልነበረም ። የእርሱ ንጽሕና የሚያነጻ ፣ ቅድስናውም የሚቀደስ ነው ። አንዳንድ ሰዎች የሚመኙት ቅድስና አለ ፣ እነርሱ በተሳፈሩበት መጓጓዣ ጋኔን የሚጮህ ፣ አጠገባቸው ያለው ሰው ተቃጠልሁ ብሎ የሚሮጥበትን ቅድስና ይፈልጋሉ ። እውነተኛ ቅድስና ግን ኃጢአተኞችን የሚያቅፍ ነው ። የሚያስበረግግና የሚያሸማቅቅ ፣ ኃጢአተኞችን ተስፋ የለሽ የሚያደርግ ቅድስና ከእግዚአብሔር አይደለም ። ኃጢአተኞች ከክርስቶስ ጋር ሲሆኑ ሰላም ተሰማቸው እንጂ ራሳቸው አንሶባቸው አልተረበሹም ። የትላንቱን ለመጣል ጉልበት አገኙ እንጂ እኔ አልድንም ብለው አልፈሩም ። ነገ በብሩህ ታያቸው እንጂ የእኔ ኃጢአት ንስሐ የለው ብለው አልሰጉም ።
እንደ እኔ የታመሙ መኖራቸውን ማሰብ ያጽናና ይሆናል ። መድኃኒቱን ሳገኝ እንደ እኔ የታመሙትን መፈለግ ደግሞ ግዴታ ነው ። ማቴዎስ እንደ እርሱ የታመሙትን ፣ በሰው መካከል እየኖሩ ሰው አልባ የሆኑትን ፣ በአድማ ተገልለው ብቸኛ የሆኑትን ፣ ኃጢአተኞችና ቀራጮች ጠራ ። ጌታችንም እነርሱን ከማቅረብ ውጭ የሚያቀራርብ አሳብ አላመጣም ፣ ከመውደድም ውጭ የማረጋጋት መልእክት አላስተላለፈም ። አጠገቡ ስፍራ ስላገኙ ፣ አብረው ማዕድ ስለቆረሱ “ለካ የሚወደን አለ” ብለው አረፉ ። የሺህዎችን ጥላቻ በአንዱ ፍቅር ሻሩ ። የብዙዎችን ስድብ በእርሱ ማቅረብ ዘነጉ ። የፍቅር ኃይል ከጥላቻ ኃይል በላይ ነው ።
ወግ አጥባቂዎቹ ፈሪሳውያን ይህን ሲያዩ ተበሳጩ ። እነርሱ ኃጢአትን ይወዳሉ ፣ ኃጢአተኛን ግን ይጠላሉ ። ያሉበትን ኃጢአት ላለማሳየት ኃጢአተኞችን ሲያወግዙ መዋል ስልታቸው ነው ። በጣም የሚሰድቡት የኃጢአት ዓይነት እነርሱ የወደቁበት ገደል ነው ። “እኔ የምኖረው ይህን ስህተት ለማጥፋት ነው” በማለት የተሳሳቱት ላይ ሰይፍ ይዘው ይወጣሉ ። እቤታቸው ሲገቡ ግን ያን ስህተት ይፈጽሙታል ። ልዩነታቸው ቀራጮችና ኃጢአተኞች በግልጽ መውደቃቸው ፈሪሳውያን ግን በድብቅ መውደቃቸው ነው ። ፈሪሳውያን ማለት ሐኪም ቤት ከፍተው በሽተኛ አይምጣብኝ የሚሉ መምህራን ናቸው ። መቼም “ትልቁ ድሀ ትንሹን ድሀ አይወደውም” እንዲሉ ትልቁ ኃጢአተኛ ትንሹን ኃጢአተኛ አይወደውም ። ፈሪሳውያንም መመጻደቅ ከሳሽ ያደርጋልና ክስ ጀመሩ ። የክስ ዓላማም የክርስቶስን ወገኖችን ለሁለት መክፈል ነው ። ጥርጣሬን እየፈጠሩ እኛን ብቻ እመኑን ቢሉም እነርሱም አንድ ቀን የዘሩትን ያጭዳሉ ።
“ፈሪሳውያንም አይተው ደቀ መዛሙርቱን፡- መምህራችሁ ከቀራጮችና ከኃጢአተኞች ጋር አብሮ ስለ ምን ይበላል ? አሉአቸው ።” ፈሪሳውያን ያልገባቸው ነገር ጌታ ከቀራጭ ጋር አብሮ መብላት ሳይሆን ከማቴዎስ ጋር አብሮ ሊኖር ነው ። እርሱ ስም ያላቸውን ለመመልመል የመጣ አይደለም ። የኃጢአተኞች ወዳጅ ሁኖ ለኃጢአተኛው ዓለም ንጽሕናን ለማልበስ የመጣ ነው ። ከማቴዎስ በቀር ደቀ መዛሙርቱ እንደ ፈሪሳውያን ሲያስቡ የኖሩ ናቸው ። ይልቁንም ቀናተኛው ስምዖን በመካከላቸው አለ ። “ቀራጭን መግደል ነው” ብሎ የሚያምን ሰው ነበር ። ክርስቶስ የመረጠውን ግን ማን ይገፋዋል ? ይህ ጥያቄ በውስጡ ብዙ ነገሮች አሉት ። “መምህራችሁ” አሉ ። መምህራችን አይደለም ማለታቸው ነው ። ኃጢአተኞችን በገፉበት መጠን ክርስቶስንም ገፉት ። ክርስቶስን አያርፉበትም ፣ ባረፉበት ሰዎች ደግሞ ይበሳጫሉ ። ክርስቶስ መልስ ሁኖ ያላሳረፋቸው ጥያቄ ሁኖ ያብሰለስላቸዋል ። ፈሪሳውያን ጥያቄውንም በቀጥታ ወደ ክርስቶስ አላቀረቡም ። ምን እንደሚመልስላቸው ያውቁታል ። ጥያቄውን ግን ወደ አዳዲስ ደቀ መዛሙርት አቀረቡ ። ደቀ መዛሙርቱም  ክርስቶስ የተቀበለውን ስለመቀበል ብቻ የሚያውቁ ነበሩ ። ለዚህ ጥያቄ መልስ ለመስጠት ገና በእምነት አላደጉም ። ጌታ ግን የጠራቸው ወገኖች ሲከሰሱ አንደበታቸው ነው ። ስለዚህ ለቀራጮችና ለኃጢአተኞች ተሟገተላቸው፡-
“ኢየሱስም ሰምቶ፡- ሕመምተኞች እንጂ ባለ ጤናዎች ባለ መድኃኒት አያስፈልጋቸውም ፤ ነገር ግን ሄዳችሁ፡- ምሕረትን እወዳለሁ መሥዋዕትንም አይደለም ያለው ምን እንደ ሆነ ተማሩ ፤ ኃጢአተኞችን ወደ ንስሐ እንጂ ጻድቃንን ልጠራ አልመጣሁምና አላቸው ።”  የምንባለውን እርሱ ይሰማል። ሰዎች የሚሉንን እርሱ አይለንም ። እርሱ ኃጢአተኞችን ይመለከት የነበረው እንደ ታካሚዎቹ ነው ። ሐኪም በሽተኛው እንዲህ ያለ ሕመም ስለ ተያዘ አይቀየመውም ። እንዲድንለት ብቻ ጥረት ያደርጋል ። ትልቁ የነፍስ ሐኪም ክርስቶስም ኃጢአተኞችን ስለ ማዳን ያስባል እንጂ በበሽታቸው አይሸሻቸውም ። በእርሱ ዘንድም እውነተኛው በሽታ ኃጢአት ነው ። በሽተኞችን በማከም እንጂ በመሸሽ በሽታን ከምድር ማጥፋት አይቻልም ። ጤነኛ ነን ብለው ለሚያስቡ ፈሪሳውያን እርሱ አያስፈልጋቸውም ። ክርስቶስ የመጣውና የሚያስፈልገው ኃጢአተኛ እንደሆኑ ለተሰማቸው ብቻ ነው ። እርሱ ምሕረትን እንጂ መሥዋዕትን የሚወድ አይደለም ። መሥዋዕት ሰው የሚያቀርበው ነው ፣ ምሕረት ግን ሰው የሚሰጠው ነው ። ሰው መሥዋዕት በማቅረብ ደስ እንደሚለው እርሱ ደግሞ ምሕረትን በመስጠት ደስ ይለዋል ። የመሥዋዕት ዓላማውም ምሕረት ለመቀበል ነው ። ፈሪሳውያን በመሥዋዕት ምሕረት ይለምናሉ ፣ ሌላው ምሕረት ሲያገኝ ግን ደስተኛ አይደሉም ። የግብዞች ትልቁ ችግር የእግዚአብሔርን ምሕረት ለግል ኃጢአታቸው መጽናኛ ማድረጋቸው ነው ። ምሕረቱ ለዓለምና ለዘላለም ነው ። ምሕረቱ ለሰፈር አይደለም ፣ ለዓለም ነው ። ምሕረቱ ለዛሬ አይደለም ፤ ምሕረቱ ለዘላለም ነው ።
ያ ቀንም ደስታን ለማጨለም በመጡ ፈሪሳውያን ያልተሸነፈ ብርሃን የበራበት ዕለተ ብርሃን ነበር ። አንዴ እርሱ ይቅር ካለ ማንም መክሰስ አይችልም ። ማቴዎስም ከጌታ ጋር ኑሮውን ጀመረ ። ያላሰበው ቦታ ዋለ ። ቀድሞ ስለ ኃጢአተኝነቱ ብቻ ያስብ ነበር ። አሁን ግን ስለ አዳኙ ታላቅነት ማሰብ ጀመረ ። ክርስቲያን መሆን ማለትም ኃጢአትን ማሰብ አይደለም ፣ እርሱማ ዓለማውያንም ያስቡታል ። መሐሪ ጌታ እንዳለ ማመን እርሱ ክርስትና ነው ። ስለሚጠሉን ማሰብ ሳይሆን ስለሚወደን ጌታ ማሰብ እርሱ ሃይማኖት ነው።
ማቴዎስ ሦስት ዓመት ከሦስት ወር ከጌታ ጋር በዋለበት እየዋለ ፣ ባደረበት እያደረ ቆየ ። የትንሣኤውም ምስክር ሁኖ ከሐዋርያት ጋር ወደ ዓለም ወጣ ። እነዚያ ይጠሉት የነበሩትን አይሁድ ለመካስ ፣ እርሱ ደግሞ በፍቅር ለመመለስ አሰበ ። ስለዚህም ወንጌሉን በሚገባቸው በአራማይክ ቋንቋ ጻፈላቸው ። ክርስቶስ የዳዊት ልጅ መሆኑን በመግለጥ ልባቸውን ወደ ንጉሣዊ ክብር ከፍ አደረገው ። ከሁሉ ቀድሞም በ41 ዓ.ም. ወንጌሉን ጻፈ ። የመጀመሪያው የአዲስ ኪዳን መጽሐፍም የማቴዎስ ወንጌል ነው ። ማቴዎስ ስለ ራሱ ሲጽፍ ጌታ ታሪኩን እንደለወጠለት ገለጸ እንጂ በይገባኛል ስሜት አልጻፈም ። ስለ ራሱ ጥሪ የጻፈውም ዘጠነኛው ምዕራፍ ላይ ነው ። በአሥረኛው ምዕራፍም ከሐዋርያት ዝርዝር ውስጥ ራሱን ሲገልጽ “ቀራጩ ማቴዎስ” አለ ። ትሑት ነበር ።
ማቴዎስ አሁንም ስመ ብዙ ሆነ ። ሲጠራ ደቀ መዝሙር ፣ ሲላክ ሐዋርያ ፣ ወንጌሉን ሲጽፍ ወንጌላዊ ተባለ ። በሰማዕትነትም ገድሉን ስለፈጸመ ሰማዕት ይባላል ። ማርቆስና ሉቃስም ወንጌላቱን የጻፉት ለሮማ ግዛትና ሰዎች ነውና ከቀራጭነት ወንበር ላይ ተነሥቶ የመነነ መሆኑን ጠቅሰው ስሙን ግን ሌዊና የእልፍዮስ ልጅ በማለት ሕይወቱን ከአደጋ ሰውረዋል ። ማቴዎስ ያላሉት ሕይወቱን ለመከለል ፣ የሮማን መንግሥት የከዳ እንዳይባል ነው ። ጽሑፍ የሌላውን ሕይወት ከአደጋ የመከለል ግዴታ አለበት ። ማር. 2፡14፤ ሉቃ. 5፡27። ማቴዎስ የስሙ ትርጉም “የእግዚአብሔር ስጦታ” ማለት ነው ።
ቀራጭን ሐዋርያ ፣ ገንዘብ ሰብሳቢን ነፍስ ሰብሳቢ የሚያደርግ ጌታ የእኛንም ሕይወት ሊለውጥ ይቻለዋል ።
ተፈጸመ
ሰኔ 21 ቀን 2011 ዓ.ም.
ዲአመ 
በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ