የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቀባሪ በፈጣሪ

ዮሐንስ መጥምቅ የዘወትር ተግባሩ ንስሐን መስበክ ነው ። የንስሐ ሰባኪ የሚያኖረውም የሚቀብረውም ያጣል ። ስለዚህ አገልግሎቱ በዮርዳኖስ ወንዝ ዳርቻ ባለው በምድር በዳ ሆነ ። ሲጠማው ከዮርዳኖስ ወንዝ ይጠጣል ። ሲርበው ፍጹም ደሀ የሆኑ በረኸኞች የሚመገቡትን አንበጣና የበረሃ ማር ይበላል ። ማን ይቀብረኛል ? ብሎ ሲሰጋ ፣ ቀና ብሎ ሙሴ የሞተበትን የናባውን ተራራ ያያል ። “ቀባሪ በፈጣሪ” ብሎ ይደሰታል ። ሙሴ ሚሊየን ሕዝብ መርቷልና ሚሊየን ቀባሪ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል ። መሪ ሲሞት ሁሉም ሊቀብር ይወጣል ። አንደኛው ወሬ ለማየት ነው ። ሁለተኛው በመደንገጥ ቀጥሎ ምን ይከሰት ይሆን ? በማለት ነው ። ሦስተኛ ክፉ እንደሆነ ተመልሶ እንዳይመጣ በመስጋት ነው ። ሙሴ ግን በቁሙ የተወቀሰ ሲሞት የተመሰገነ መሪ ነው ። ብዙ አዋቂዎችና ባለ ራእዮች “ስሞት አትቅበሩኝ” ይሉናል ። ሰውን በቁም አሳቡን መረዳትና ማገዝ ከመቅበር በላይ ነው ። የእግዚአብሔር ሰዎች ለኑሮአቸው እንጂ ለቀብራቸው አልተጨነቁም ። በቀብሩ ድምቀት የተነሣ ሟች ታውቃላችሁ ? አብዛኛው ቀብር አያሌ ሰዎች የሚተዉኑበት መድረክ ነው ። ለሙሴ መርዶ ሚሊየን ሕዝብ ሠላሳ ቀናት አልቅሶለታል ። ሙሴ ግን አንድም ሰው ያልቀበረው ፣ መላእክት ሥጋውን በክብር ያሳረፉት መሪ ነው ። ለቀብራቸው ሥነ ሥርዓት ለሚጨነቁ ሰዎች ትልቅ ትምህርት ነው ።

የሙሴ መቃብር ሰይጣንም አላወቀውም ። አዋቂ የሚመስለን ሰይጣን በፍጡርነቱ እውቀቱ ውስን ነው። የጌታ ሞት ለእርሱ ዘላለማዊ ሽንፈት መሆኑን ቢያውቅ ኖሮ እንዳይሞት ይንከባከበው ነበር ። የሙሴ መቃብር ስለተሰወረበት ቅዱስ ሚካኤልን ለመጠየቅ ሞክሯል (ይሁዳ ቍ. 9) ። ሰይጣን እንኳን ወድቆ ጥንትም መልአክ ሆኖ ሳለ እውቀቱና ኃይሉ ውስን ነው ። ፈሪሀ እግዚአብሔር ሳይሆን ፈሪሀ ሰይጣንን የሚሰብኩ ፣ ለሁሉም ነገር ሰይጣን ነው የሚሉ ሊያስተውሉ ይገባል ። ኃይል የእግዚአብሔር ነው !

ባሕታዊው ዮሐንስ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰው ድምፅ ፣ በመላው እስራኤል ተሰማ ። ዓለምን ፣ ዓለምን በመናቅ ማስጨነቅ ይቻላል ። ዓለም የሚያከብራትን ትንቃለች ፣ የሚንቃትን ትፈራለች ። ከገሊላ እስከ ይሁዳ ፣ ከገበሬ እስከ ዓሣ አጥማጅ ፣ ከጨዋ እስከ ካህን ፣ ከንጉሥ እስከ ወታደር ሁሉም ድምፁን ሰማ ። በቤቱም ፣ በእልፍኙም ፣ በመድረኩም ፣ በቤተ መንግሥቱም ፣ በባሕሩም በየብሱም ተረጋግቶ መቀመጥ አልቻልም ። ጦር ሳይዝ ጦር የያዙትን ያስጨነቀው ባሕታዊው ዮሐንስ መጥምቅ ነው ። አትሮኖንስ ከጨበጡት ፣ በሐር በተጨበጨበ መቅደስ ከሚያገለግሉት ይልቅ በምድረ በዳ የሚጮኸው ሰው ድምፅ ኃይል ነበረው ። ቃሉ ምቾት የማይሰጥ ነው ። የእግዚአብሔር ቃል በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ነው ። ዮሐንስም እንደ ቃሉ በሁለት ወገን የተሳለ ሰይፍ ፣ በሽንገላ ለመያዝ የማይመች ሰው ነበር ። “እግዚአብሔርን የምትወድዱ ምእመናን ….” እየተባሉ በሽንገላ የኖሩ ሰዎች ፣ ኃጢአት ማለት ከእግዚአብሔር ጋር ጦርነት መግጠም መሆን ተረዱ ። መስተዋት ቆሻሻን ስላሳየ አይሰብሩትም ። ዮሐንስን ግን ሰበሩት ።

የተሰበሩት ሁሉ ምናልባት ቆሻሻን ስላሳዩ ሊሆን ይችላል ። መስተዋትን ያመሰግኑታል እንጂ አይሰብሩትም ።

ወደ ዮሐንስ ዘንድ ለመሄድ እመቤታችን አላስፈለጋትም ፣ ንጽሕት ናትና ። ዮሐንስ መጥምቅ ዘመድዋ ቢሆንም እንዴት እንዳደገና የት እንደ ኖረ ልትጠይቅም አልሄደችም ። እርስዋ የተባረከች ፣ ሁሉንም በልብዋ የምትጠብቅ ናት ። በናዝሬት መኖሪያዋ የዮሐንስ መጥምቅን ዝና ሰምታለች ። ልጇ ኢየሱስ የዮሴፍን የአናጢ ሱቅ ከፍቶ እየሠራ ፣ እባክህን ወንበሩን ፣ ጠረጴዛውን አድርስልን እያሉ እየጠየቁት ሳለ የዮሐንስን ዝና እንደ አላዋቂ አድርገው ነገሩት ። እርሱም ዘመኑ እንደ ደረሰ አውቋልና ሱቁን ዘግቶ ፣ እናቱን ተሰናብቶ ዓለሙን በሙሉ ሊያገለግል ወጣ ። ንስሐ የሌለበት ወደ ንስሐ ሰባኪው ሄደ ። ንጹሕ ቢሆንም የዮሐንስን ተግሣጽ ቆሞ ሰማ እንጂ እኔን አይመለከተኝም አላለም ። ንጹሕ ብትሆኑም ተግሣጽ አትናቁ ሲለን ነው ።

በዓለ ጥምቀቱን ስናከብር ወጣቶች በበዓሉ ላይ የዝሙት ማስታወቂያ ፣ የአደባባይ ነውር ሲሠሩ ለንስሐ ማብቃት አለብን ። በቅዱሱ ቀን እንዳይረክሱ መገሠጽ ያስፈልገናል ።

ይቀጥላል

#ዲያቆን #አሸናፊ #መኰንን
ጥር 20 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ