ቅዱስ እግዚአብሔር አብ አንተ የምድረ በዳው እሸት ፣ የቆላው ፍሬ ፣ የበረሃው ነዶ ፣ ማን ይነካኛል አንተን ተራምዶ !! አብረኸኝ የኖርኸው ፣ አብረኸኝም የምትኖረው አንተ ነህ ። ስለ አምላካዊ ሕግህ ብቻ ሳይሆን አብረኸኝ ስለመኖርህ እንዳላስቀይምህ እርዳኝ ። ሰብአዊ ክብር ይሻራል ፣ አንድነትም በመለያየት ይተካል ። እየበላሁ በምፈራበት ዓለም ፣ ቃልህን እየሰማሁ በምደክምበት ሥጋ ውስጥ ነኝና ምሕረትህ ፈጥና ታግኘኝ ። ለፈጠርካቸው የሰጠኸውን ተቀብያለሁ ፣ የአማኞችም ጸጋ ደርሶኛል ፤ የአሸናፊዎች ሽልማት እንዳያመልጠኝ ያሰጋኛል ። ከዋጋ በላይ ሁኖ ስላልከፈልኩበት ጸጋህ ፣ ከተመን ልቆ በነጻ ስለተለቀቀው ስጦታህ ፣ ከመነገር በላይ ስለሆነው ሱታፌህ/ኅብረትህ ምስጋና አደርሳለሁ ። በዓይናማነት ሳይሆን ድሆችን በማየት ፣ በአለንጋ ጣቶች ሳይሆን ችግረኞችን በማጥገብ ፣ በቄንጠኛ እግሮች ሳይሆን መድረሻን በሚያውቅ አማኝነት ባርከኝ ። ከባሕር መዝገብ ስሜ ሲጠፋ እየደነገጥሁ ከሕይወት መጽሐፍ መታጣት ግን ቀላል እንዳይሆንብኝ እባክህ ልቡናዬን አብራልኝ ። ቅዱስ እግዚአብሔር አብ ሆይ በማመን አባት ብዬ እጠራሃለሁ ። አሜን ።
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 5 ቀን 2014 ዓ.ም.