መልአኩ ገብርኤል በቅድስናው ቅዱስ ይባላል ፡፡ የዙፋን መልእክተኛ ነውና መልአክ ወይም መልእክተኛ ይባላል ፡፡ የሠራዊት አዛዥ ነውና ሊቀ መላእክት ይባላል ፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ ስማቸው ከገነኑ መላእክት ከቅዱስ ሚካኤል ቀጥሎ የሚጠራው ሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል ነው ፡፡ ቅዱስ ገብርኤል ብሥራትን በማወጅ የታወቀ መልአክ ነው ፡፡ በባቢሎን ምርኮ የነበረውን ስለ ሕዝቡ የሚያለቅሰውን የነቢዩ ዳንኤልን የጸሎት መልስ ይዞ የመጣው ፣ ራእዩንም ያብራራለት ቅዱስ ገብርኤል ነው ፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የአምላክ ወዳጅ ፣ የሰው ልጆችም ወዳጅ ነው ፡፡ ሊቀ ካህናት ዘካርያስ መጥምቁ ዮሐንስን እንደሚወልድ የዘመናትን የጸሎት ምላሽ ይዞ የመጣ ፣ እመቤታችን አምላክን እንደምትወልድ ታላቁን የምሥራች ይዞ የደረሰው ቅዱስ ገብርኤል ነው ፡፡ የሰው ልጆችን መዳን ታላቁን የምሥራች ይዞ በመምጣቱና በአዲስ ኪዳን ተደጋግሞ ስሙ በመጠቀሱ መጋቤ ሐዲስ ይባላል፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የሚታወቅበት ንግግሩ፡- “እኔ በእግዚአብሔር ፊት የምቆመው ገብርኤል ነኝ” የሚለው ነው /ሉቃ. 1፡19/፡፡ በእግዚአብሔር ፊት መቆም ታላቅ ባለሟልነትን የሚያሳይ ነው ፡፡ ቅዱስ ገብርኤል የአምላክ ባለሟል ነው፡፡ መላእክት የሰው ልጆች አፍቃሪና ወዳጅ ናቸው ፡፡ ከእነዚህ ወዳጆቻችን አንዱ መልአኩ ገብርኤል ነው ፡፡ ዛሬም የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር መልአኩን ልኮ የነደደውን እሳት ያጥፋልን ፡፡ የመልአኩን በረከት ያሳድርብን ፡፡ …
ለሊቀ መላእክት ቅዱስ ገብርኤል መታሰቢያ በዓል እንኳን አደረሳችሁ ፡፡