የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ

የዲያቆን አሸናፊ መኰንን ገጽ 

ቅዱስ ገብርኤል ሆይ!

እግዚአብሔርን እጅግ በመውደድ የታወቅህ ቅዱስ ገብርኤል ሆይ ፣ ሰውን እጅግ ትወደዋለህ ። የሰባ ዓመት የእስራኤል ግዞት ዓለመ መላእክትን አሳዝኗል ። ለኢየሩሳሌም የምሕረት ጊዜዋን ናፍቋል (ዘካ. 1 ፡ 12)። ከሥጋ ባርነት የነፍስ ባርነት ይጸናል ። የሰባ ዓመት ግዞት ካሳዘነ ፣ 5500 ዘመን በነፍስ ባርነት ላሉ የሰው ልጆች እጅግ ታዝናለህ ። ቅዱስ ገብርኤል ሆይ በሥላሴ መንበር ፊት ስትጠራ ለዳንኤል የነገርከው ሱባዔው መፈጸሙን አስታውሰህ ቀርበሃል ። ትንቢቱን ያመጣ ፣ ሱባዔውን የገለጠ ፍጻሜውንም ያበሥራል ብለህ ጠብቀህ ነበር ወይ ? በታላቁ ዙፋን ከስድስት ወር በፊት ለዘካርያስ የምሥራች ስትቀበል የድኅነት ዋዜማ ላይ እንደሆንን አውቀህ ነበር ወይ ? መልእክተኛው ከመጣ ንጉሡ ይከተላል ። በርግጥም አውቀሃል ። አንተ ቅዱስ መልአክ የ5500 ዘመን የኃጢአት ጅረት የሚቆምበትን ብሥራት እንደምትናገር አላሰብህ ይሆናል ። ታላቁ መልአክ ቅዱስ ሚካኤል ሳይሆን አንተ ይህን የምሥራች ትናገር ዘንድ ተመረጥህ ። እርሱ በሰማይ ትልቅ ውጊያ ያካሂዳል ። የምሥራች እንዳይመጣ ፣ መርዶ ብቻ እንዲሆን የሚሠሩትን ፣ አማንያንን ተስፋ ለማስቆረጥ ፣ በሱባዔ ደጅ የሚጠኑትን “ከንቱ ደከማችሁ” ለማለት የተነሣሡትን ርኵሳን መናፍስትን ይፋለማል ። እርሱ መጋቤ ብሉይ ሁኖ እስራኤል ዘሥጋን ረድቷል ። አንተ መጋቤ ሐዲስ ሁነህ የምሥራችን ለማምጣት ተልከሃል ።

ቡሩክ መልአክ ገብርኤል ሆይ ፣ የዮሐንስ መጥምቅ መወለድ ደስ አሰኝቶሃል ። ደስ ያላለው የደስታ መልእክት ይዞ ሊሄድ አይችልምና ። ከዮሐንስ የሚበልጠው የእግዚአብሔር ልጅ ፣ የሰው ልጅ የሚሆንበት ዜና እጅግ ደስ አሰኝቶሃል ። የዮሐንስን መወለድ ለመናገር ወደ ኤልሳቤጥ ሳይሆን ወደ ዘካርያስ ሄድህ ። ክርስቶስ ግን ያለ ወንድ ዘር ይወለዳልና ወደ ድንግል ማርያም ተላክህ ።

ጨለማው ሰልጥኖ ፣ የሰው ልጅ ሁለት ጊዜ ሞቶ ፣ አንደኛው ሞት በፍርሃት ሁለተኛው ሞት በመቃብር ተጭኖት ነበረ ። ሙሉ ብርሃን ካለበት ሰማይ ላይ የምሥራቹን ፣ የወልድን ሰው መሆን ስትቀበል ነጥቀህ ለመሮጥ ፣ በመለከት ለማወጅ አልጓጓህም ወይ ? ድምፁን ስትሰማ ፣ በሥላሴ መንግሥት የተወሰነውን ስታደምጥ፡- “ተስፋውን የማያጥፍ ፣ ቀጠሮውን የማይሰርዝ” ብለህ እግዚአብሔርን ማመስገን አልጀመርህም ወይ ? በእርሱ ዘንድ ሺህ ዓመት እንደ አንድ ቀን ነው ። አምስት ሺህ አምስት መቶ ዘመንም እንደ አምስት ቀን ተኩል ነው ። ከአምስት ቀን ተኩል በፊት ያለውን እኔም አስታውሳለሁ ። ጌታዬ ግን 5500 ዓመት የዘመን ርቀት ተስፋውን አላዘናጋውም ። ቅዱስ መልአክ ሆይ ታጥቀህ ቆመህ ፣ እጅ ነሥተህ ትእዛዝ ስትቀበል እግዚአብሔር ሰውን እንዴት ወደደው ? ብለህ አልተገረምህም ወይ ? በተደላደለው ሰማይ ብትኖርም በተጎሳቆለው ምድር ላለው ለሰው ልጅ ታዝናለህ ። ፍቅር ያለው የራሱን ምቾት አያስብም ። እኔ ገብቻለሁ ፣ ስለወጣው አልጨነቅም አይልም ።

ቅዱስ መልአክ ሆይ በሰማይ “አዳምን እንፍጠር” ሲባልና “እናድነው” ሲባል ታላላቅ ሁነቶችን ሰምተሃል ። በመልኩ የፈጠረው በወደቀ ጊዜ አሁን ደግሞ ሰው ሆኜ ላድነው አለ ። እግዚአብሔር መልኩን በተፈጥሮ ልኮ ፣ በተዋሕዶ መልኩን ለበሰው ። የንጉሥ ፎቶ መሬት ወድቆ አይቀርም ። ንጉሡ የራሱን መልክ ከመሬት አነሣው ። ትእዛዝ በትእዛዝ ይሻራል ። ተዋሕዶ ግን በመከፈል አይለያይም ። ስለዚህም አንተን የተዋሕዶ ምስክር አደረገህ ። ገብርኤል ሆይ ያንተ ወገን የነበረው መልአክ ወድቋል ። ለእርሱ ሳይሆን ለወደቀው አዳም የምሥራች ተላከ ። በዚህም ደስተኛ ነህ ። ሰማይ ፈቃደ እግዚአብሔር እንጂ የወገን አሳብ የለም ።

ቅዱስ መልአክ ሆይ ፣ ዓለሙ ሁሉ በታላቅ ፀጥታ ውስጥ ሳለ ፣ የሮማውያን ቤተ መንግሥትን ፣ የልዕልቶችን እልፍኝ አልፈህ ወደ አንዲት ገጠራማና ስም የለሽ መንደር ወደ ናዝሬት መጣህ ። በሥጋ ድሀ ፣ በነፍስ ግን ባለጠጋ የነበረችውን ድንግል አገኘህ ። እርስዋ ከንጉሥ ዘር ተወልዳ አሁን ግን በድህነት አለች ። ከአያቱ ባለጠጋ ያልነበረ ድሀ ፣ ከአያቱ ድሀ ያልነበረ ባለጠጋ የለም ። የዳዊት ልጅ እንዲህ በድህነት ስትኖር ፣ በምስጋና ስትቆም አገኘሃት ። አምላክን ለመውለድ ለምና ሳይሆን እርሱ በፈቀደ ከእርስዋ ሰው ሊሆን ወደደ ። ወልዶ የመከነ ልጄ ይለዋል ። እግዚአብሔር የመካኖችም ልጅ ነው ። እርስዋ ግን በባሕርያዊ ልደት ልጄ የምትለው ፣ በእውነት እናቱ ፣ በእውነት ልጅዋ ሆነ ። ቅዱስ መልአክ ሆይ ካንተ የምሥራች ጋር አብ ሊያጸናት መጣ ። መንፈስ ቅዱስ ተዋሕዶውን ሊያከናውን በማኅፀነ ድንግል ሥራ ጀመረ ። ወልድም ሥጋን ከእርስዋ ለበሰ ። የምሥራቹን በጆሮዋ በሰማች ጊዜ “ይሁንልኝ” ስትል አምላክ የዕለት ፅንስ ሁኖ በማኅፀንዋ አደረ ። አንተ የምትሰግድለትን ፣ በፍርሃት በፊቱ የምትቆምለትን እርስዋ በማኅፀንዋ ተሸከመችው ። እግዚአብሔርን ለመሸከም እግዚአብሔር አጸናት ። ጸጋ የበዛላቸውን እናደንቃለን ፣ ባለጸጋውን የወለደችው ድንግል ማርያም ግን ከሁሉ ፍጥረት ከብራለች ። ቅዱስ መልአክ ሆይ ይህን በማየትህ ሁልጊዜ የዳነው ዓለም ያስብሃል ።

ዓለምን ለወደደ ለእግዚአብሔር አብ ፣ ሰው ሁኖ ላዳነን ለኢየሱስ ክርስቶስ ፣ በጸጋው ሙላት ለጎበኘን ለመንፈስ ቅዱስ ምስጋናና ክብር ውዳሴ ይሁን አሜን !

ይቀጥላል
ዲያቆን አሸናፊ መኰንን
ታኅሣሥ 27 ቀን 2016 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ
አዳዲስ መጻሕፍትን ይግዙ

ተዛማጅ ጽሑፎች

መጻሕፍት

በዲያቆን አሸናፊ መኰንን

በTelegram

ስብከቶችን ይከታተሉ