እንኳን ለ 2017 ዓ.ም የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!
ከአዳም እስከ ሄኖክ ፣ ከሄኖክ እስከ አብርሃም፣ ከአብርሃም እስከ ዳዊት ፣ ከዳዊት እስከ ሚልክያስ የክርስቶስ ልደት የአበው ተስፋ ፣ የነቢያት ትንቢት ነው ። እነዚህን ሁሉ ቅዱሳን ወክላ ክርስቶስን የተቀበለችው ቅድስት ድንግል ማርያም ናት። የክርስቶስን መምጣት እርስዋም ትንቢት አጥንታ፣ መጻሕፍት አንብባ ብትጠብቅም አምላክን እወልዳለሁ ብላ ግን አስባ አታውቅም ነበር ። ቃሉን ወደምትወደው ድንግል ቃል በሥጋ መጣ። በገብርኤል አንደበት ቃል በቃሉ ተናገራት። ወደ እግዚአብሔር ነፍስዋ በገሰገሰች መጠን አምላክ ወደ እርስዋ መጣ።
እግዚአብሔርን በልብዋ በቃሉና በፍቅሩ ፀንሳው ትኖር የነበረች አሁን በሆድዋ በሥጋ ፀነሰችው። እግዚአብሔር የሰው ልጅ ለመባል የወረደበትን ትሕትና ያስተናገደች እርስዋ ናት። የክርስቶስ መምጣት ብዙዎች በተለያየ ዓላማ ይጠብቁት ነበር። ከሮማውያን ባርነት ነጻ ያወጣናል ብለው አይሁድ ይናፍቁት ነበር። ይህም ሁለት ችግር አለው:- የመጀመሪያው ድኅነቱ ጊዜያዊ መላ ሲሆን ሁለተኛው መላውን ዓለም አይመለከትም እንደማለት ነው ። መላውን ዓለም ከትልቁ ገዥ ከኃጢአት ለማዳን በመጣ ጊዜ በማርያም ማኅፀን ተሰወረ:: ይህን ምሥጢር እርስዋ ብቻ ስታውቀው አጠገብዋ ያለው አገልጋይ ቅዱስ ዮሴፍ እንኳ አላወቀም ነበር። ሔዋን ዓለሙን ወክላ በቆረጠችው ፍሬ የሰው ዘር የሞት ልጅ ሆነ፤ ድንግል ማርያም በተሸከመችው ፍሬ መላው ዓለም የድኅነት ሠራዊት ተባለ። በዓለም ላይ ለአገራቸው የሚሮጡ ሯጮች ድል ለአገራቸው በእነርሱ በኩል እንዲሆን ይመኛሉ፤ የዓለም ሁሉ ድኅነት በድንግል ማርያም በኩል ሆነ:: አምላክ የ ሰው ልጅ ተባለ፣ ድንግልም አምላክን ልጄ ብላ ጠራች።
ለድሆች የምንቆርሰው እንጀራ ፣ የምንቀዳው ጽዋ ለጌታ እንደ ተደረገ ይቆጠራል። ጌታም ለእኔ ያደረጋችሁት ነው ብሎ ይቆጥረዋል። ድንግል ማርያም ግን በተዘዋዋሪ ጌታን አላበላችውም፣ በቀጥታ የድንግልናዊ ወተትን አጠባችው። በነቢያት ላይ በመንፈሱ ቢያድርባቸው ክቡር ተብለዋል፣ በድንግል ማርያም ግን በአካል አድሮባታል፣ ከሥጋዋ ሥጋ ከነፍስዋ ነፍስ ነሥቷል:: ሰው ስለመሆኑ በምድር ላይ ከእርስዋ በቀር ማንም የለውም፣ ምክንያቱም ያለ አባት ተወልዷልና። ጌታን በሕልም በራእይ ብናየው ደስታችን ወደር የለውም። ድንግል ማርያም ግን በአካል አቅፋዋለች። ስፉሕ አምላክ እንዴት በክንዶችዋ ታቀፈ? የፍጥረት መጋቢ እንዴት ጡት ለመነ ? ኪሩቤል መንበሩን ቢሸከሙ አያዩትም፣ የኪሩቤልን ጌታ በእቅፍዋ ውስጥ ያየችው ከኪሩቤል ትበልጣለች። ማኅፀነ ማርያም ከሰማይና ከምድር ሰፋ ፣ ሰማይና ምድር የማይችሉትን ተሸክሟልና።
ሥጋን የፈጠረው ሥጋን ከእርስዋ ወሰደ፣ ነፍስን የሰጠ ነፍሰን ከእርስዋ ነሣ :: የሴት ዓለም የሞት በር ሆንሁ ብሎ እንዳያፍር በድንግል ማርያም የሕይወት መግቢያ ሆነ። አምላክ በወንድ ፆታ ፣ ከሴት ዘር ተወለደ። ወንድ ልጅ ከሴት ዘር ተገኘ። ሔዋን ሞትን ስትፀንስ አጋፋሪው ሰይጣን ነበረ፣ ድንግል ሕይወትን ስትፀንስ አጋፋሪው መንፈስ ቅዱስ ነው። ድንግል እናት ሆነች። ያላገቡ መናንያን ድንግልም አባትም መሆን ይችላሉ። በዚህም ድንግል ማርያም የካህናት አብነት ሆነች ።
ኢሳይያስ በዘመኑ ተጠልቶ በመጋዝ ተሰነጠቀ፣ ዛሬ ማንም አይጠላውም፤ ጴጥሮስ የቁልቁሊት ተሰቅሎ ሞት፣ ዛሬ ማንም አይጠላውም። ሰይጣን ግን እስከ ዛሬ ድረስ ድንግል ማርያምን ይጠላታል። ይህ በእርስዋ ላይ ያለ ጸጋ ትልቅ መሆኑን ያመለክታል። ስለ ሣራ፣ ስለ ርብቃ፣ ስለ ሃና ፣ ስለ ኤልሳቤጥ ቢነገር የማይከፉ ስለ ድንግል ማርያም ሲነገር ይከፋሉ:: ይህ የቀጠለው የሰይጣን ጠላትነት ውጤት ነው ። የድንግል ማርያምን ፍልሰት ስናስብ አምላክ ያከበረውን እንደማይረሳ ፣ ተጠቅሞም እንደማይጥል ዋስትና ነው። ድንግል ማርያም የአምላክ ዙፋን ናት። አምላክ ዙፋኑን አይተውም። ፍልሰታ ለማርያም የአምላክን ታማኝነት ያስተምረናል::
ከእመቤታችን ከቅድስት ድንግል ማርያም ረድኤት በረከት ያሳትፈን!
አማላጂቱ ሆይ ለእኛ ጸልይን፣
መከራና ሥቃይ ኃጢአት ላደከመን።
ነሐሴ 1 ቀን 2017 ዓ.ም.