የትምህርቱ ርዕስ | ቍጣ -10

የቍጣ ውጤቶች

የለፉበትን ነገር ማጣት

ትዕግሥት ዓመት ሙሉ የካበውን ቍጣ በደቂቃ ይንደዋል ። ለራሱ ልፋት የማያዝን ሰው ቢኖር ቍጠኛ ሰው ብቻ ነው ። ቍጣ የአሁን ወዳጅ ፣ የአሁን ተቆርቋሪ ሲሆን ከደቂቃዎች በኋላ እየከዳን ይመጣል ። የዚያን ጊዜ በሕሊና ችሎት ቀርበን እንዳኛለን ። የያዝነው ኑሮ ብዙ ዋጋ የተከፈለበት ነው ። ቤተሰቦቻችን ፣ ጓደኞቻችን ፣ የሃይማኖት መምህራን ፣ ከሁሉ በላይ ክርስቶስ የደም ዋጋ የከፈለበት ነው ። በነጻ አልኖርንምና እንዲሁ የጨበጥነውን መበተን አይገባንም ። ኑሮ ፣ አገልግሎት ፣ ትዳር የነብርን ጭራ እንደ መያዝ ነው ። ከለቀቁት ጉዳቱ ለራስ ነው ። ማውደም ጥበብ አይፈልግም ፣ ፈንጂም ያፈርሳል ። መሥራት ግን ጥበብና ጊዜ ይፈልጋል ። እዚህ ደረጃ ለመድረስ ብዙ እንቅልፎችን ፣ ብዙ ቀኖችን ሠውተናል ። ወዳጅነታችን ውስጥ የባከነ ጊዜ ፣ ገንዘብ ፣ ምኞት … አለ ። መተው ቀላል ነገር ነው ፣ መግደልም የሚፈልገው መማርን ሳይሆን ብላሽነትን ነው ። ማዳን ግን እውቀት ይፈልጋል ። ለሰው ሕይወት በሽታ መጨረሻው እንዳልሆነ ሁሉ ለግንኙነታችንም ጠብ መጨረሻ መሆን የለበትም ። አክሞና አድኖ መጓዝን መልመድ አለብን ። በሕይወት ዘመናችን ለአንድ ሰው እንኳ ይቅርታ ማድረግን መለማመድ ያስፈልገናል ። መሬት መንቀጥቀጥን የሚያስከትሉ የኒውክለር ሙከራዎች ለቍጣ ቀን የተቀመጡ ናቸው ። በብዙ አገራት ዋሻ ውስጥ የተከተቱ ሰይፎች የሚወጡት በቍጣ ነው ። የዓለማችን አንድ አገር የታጠቀችው መሣሪያ ይህን ዓለም ሊደመስስ ይችላል ። ሰው ለመጥፋት ቅርብ ሁኖ እየኖረ ነው ። የሚወራው ሥልጣኔና ከፍታ ሁሉ መጨረሻው በጦር መሣሪያ መተላለቅ ነው ። ሰው የትኛውም ሥልጣኔው ክፋትን ለማፍጠኛ እንጂ ደግ ነገርን ለመተግበሪያ አላዋለውም ። ዓለማችን የሚበልጠውን ጊዜ ያለ ስጋት ኖራ በዚህ አንድ መቶ ዓመት ግን በገዛ እጅዋ ለመጥፋት የተቃረበች ይመስላል ። ሁለት የዓለም ጦርነቶች በያዝነው ምእት ተከስተዋል ። ሦስተኛው የዓለም ጦርነት እንዳይነሣ በብርቱ ይሰጋል ። ቍጣ ቤታችንን ብቻ ሳይሆን የዓለማችንን ዕድሜ እንዳያሳጥረው መጠንቀቅ ያስፈልጋል ።

ሃይማኖት ከእግዚአብሔር የፍቅር ጠባይ ተለይቶ ሲሰበክ ፣ ጽናት ሳይሆን እክራሪነት ሲኖረው አጥፍቶ መጥፋትን እየጋበዘ ይመጣል ። አንድ ወታደር ለዚህ እስኪበቃ ቢያንስ ሃያና ዐርባ ዓመታት ዋጋ ተከፍሎበታል ። ቍጣ በሚቀሰቅሰው ጦርነት ግን በደቂቃ ሕይወቱ ያልፋል ። የሰው ልጅ ብንከባከበው እንኳ ሟች ነው ። ይልቁንም ሞት የሚባል ተራ እየጠበቅን ሌላውን መግደል አላዋቂነት ነው ። “ታገሡ” የሚሉንን እንደ ፈሪ እየቆጠርን “በለው” የሚሉንን እንደ ጀግና መቍጠር ተገቢ አይደለም ። “በለው” የሚሉን አጠገባችን የሉም ፣ ጥግ ይዘው የሚማግዱን ናቸው ። “ታገሡ” የሚሉን ግን ትርፍና ኪሣራውን ለመመዘን አጠገባችን ያሉ ናቸው ። ሰማዕትነትን የሚሰብኩልን ሰማዕትነትን የሚሸሹ ናቸው ። ብቻ የሠላሳና የዐርባ ዓመት ትዳርን ቍጣ በደቂቃ ያፈርሰዋል ። በአገልግሎት ዘመኔ የ65 ዓመት ትዳር ሲፈርስ አይቻለሁ ፣ በአንዲት የቍጣ ንግግር ፋይሉ ተዘግቷል ፤ የ55 ዓመት ትዳርን ለማሸማገል ተቀምጩ ሳይሳካልኝ ቀርቷል ። ሰዎች አንድ ቀን ቢቀራቸው እንኳ እልሃቸውን አሟልተው መሞት ይፈልጋሉ ። እልህ ጣዖት አምልኮ ነው ። “ዓመፀኝነት እንደ ምዋርተኛ ኃጢአት፥ እልከኝነትም ጣዖትንና ተራፊምን እንደ ማምለክ ነው” 1ሳሙ. 15፡23 ። ምዋርተኛን እንጸየፋለን ፣ አለመታዘዝ ግን ምዋርተኝነት ነው ፣ ጣዖት አምልኮ ኋላ ቀር እንደሆነ እናስባለን ፣ እልህ ግን ጣዖት አምልኮ ነው ። ግጥማችንም እንዲህ የሚል ነው ፡-

አሸዋ ላይ ፈሶ ጤፍ አይታፈስም ፣
ሠላሳ ዓመት ቢቆይ ቂም አይበሰብስም ።

ክብር ፈላጊነታችን ቍጠኛ ያደርገናል ። ስሜን አስተካክሎ ይጠራው ይሆን ወይስ ይስተው ይሆን( በማለት ለመቆጣት ነቅተው የሚጠብቁ አሉ ። ሰው ደካማ መሆኑን ስለማይገነዘቡ ለመቆጣት ቅርብ ናቸው ። እግዚአብሔር አምላካችን መሆኑ ትልቅ ክብራችን ነው ። ሌላው ክብር ሁሉ ሐሰት ነው ። ሰው ከኑሮው ጨርሶ የክብር ቀብር ለማግኘት ፣ በማያየው ነገር ለመደሰት ጥረት ያደርጋል ። የትም ቢቀበሩ የአፈር ፍትግ የለውም ፣ የትኛውም የቀብር ሥነ ሥርዓት ሟችን ቀና አያደርገውም ። ከኑሮአችን ጨርሰን ለሞታችን እንድንጨነቅ የሚያደርገን የክብር ፈላጊነታችን ነው ። አሁን በስማችን ተጠርተን ቀጥሎ ሬሳ የሚል ስም የሚወጣልን ፣ ስማችን በደቂቃ የሚሻር ምስኪን ፍጡራን ነን ። ነብር እንኳ ሲሞት ቆዳውን ትቶ ይሄዳል ፣ እኛ ምን ትተን ለመሄድ አስበናል ? እንደውም ልጆቻችንን የሚያናክስ ንብረት ጥለን እየሄድን ይሆን ? ጠብን አውርሰን እያለፍን ይሆን ( በሥጋ ጨርሰው በነፍስ ሲወቀሱ የሚኖሩ ብዙ መሪዎች አሉ ። ሞተንም እንዳንወቀስ መጠንቀቅ ያስፈልጋል ። ጎዳናው ፣ መንገዱ ፣ ትምህርት ቤቱ ፣ ሆስፒታሉ ፣ የጦር ኃይሉ ፣ እጓለ ማውታው ሁሉ በጃንሆይና በቤተሰባቸው ስም ተሰይሞ ነበር ። አንዱም አልዘለቀም ። ስም ይሻራል ። ልዑል መኰንን መታሰቢያ ዛሬ ጥቁር አንበሳ ተብሏል ፤ የልዕልት ፀሐይ መታሰቢያ ሆስፒታል ዛሬ የጦር ኃይሎች ሆስፒታል ተብሏል ፤ የልዕልት ዘነበ ወርቅ ሆስፒታል ዛሬ አለርት ሆስፒታል ፤ ቀኃሥ ትምህርት ቤት ዛሬ ኮከበ ጽባሕ ተብሏል ። የድሀዎቹ ሐዋርያት በዘመናቸው ስም ያልነበራቸው ግን ዛሬም ቅዱስ ጳውሎስ ፣ ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታሎች በስማቸው አሉ ። ብቻ ነገሡም ጰጰሱም ዓለም ከንቱ ነው ።

ይቀጥላል
የካቲት 25 ቀን 2018 ዓ.ም.

በማኅበራዊ ሚዲያ ያጋሩ
ፌስቡክ
ቴሌግራም
ኢሜል
ዋትሳፕ

ተዛማጅ ትምህርቶች

የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ
የትምህርቱ ርዕስ